ግንቦት7 ስለአንድነት አፍራሽ ሕወሃቶች ከሠነዘረው አወዛጋቢ አስተያየት ይልቅ ሕዝቡን ባዳመጠ በጣም በበጀው!

4 Feb

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

የግንቦት7 አባል አይደለሁም። የማናቸውም ድርጅት — ሃገር ውስጥም ከሃገር ውጭ — የአባልነት ካርድ የለኝም። በተለይም ወሎ ውስጥ ባሉ ዜጎቻችን ላይ ሕወሃት የፈጸማቸውን ጸረ-ሕዝብነት፣ በኢትዮጵያዊነቴና ለኢትዮጵያ ከበሬታና አንድነቷ ባለኝ ቀንዓዊነት ብቻ ሰሞኑን ግንቦት7 በሠጠው አወዛጋቢ መግለጫ ዙርያ ያመነታሁበትን አስተያየቴን አሁን ሠንዝራለሁ።

ነገር ግን በተለይ ግንቦት7 የነገይቱ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ አካል ለመሆን ቢችል ደስታዬ ከፍተኛ እንደሆነ ግንቦት 14/2016 በጽሁፍ ገጼ ላይ እንደሚከተለው አሥፍሬ ነበር:-

    “Mr. Keffyalew Gebremedhin is not an advocate of position of any particular political party. As non-affiliated individual, not belonging to any political party at home and abroad, his sympathy to AG7 is nothing more than sympathy to the views it articulates for a democratic Ethiopia.”


በሌላ በኩል ደግሞ፣ “TEO is an independent medium, promoting ideas and views beneficial to Ethiopians, and the cause of a peaceful world and the equality of all human beings.” እንዲታወቅ እሻለሁ!
 
ነገር ግን ለግንቦት7 በተለይም ፕሮፌ ብርሃኑን በዲፕሎማቲክ ሥራ ኒው ዮርክ በነበርኩባቸው ዓመታት ስለተዋወቅንና ስለተወዳጀን፣ ያንን ያህል መሥዋዕትነት ክፍሎ ከምቾት ወደ ትግል በመግባቱ ብቻ ሳይሆን፣ ለአስተሳሰቡና ጭንቅላቱ ከፍተኛ ከበሬታ አለኝ።

በተመሣሣይ መንገድም፣ ግንቦት7 የግለሰቦች ስብስብ እንጂ ስህተት የማይሠራ የመላዕክት ድርጅት ነው ብዪ አምኜ አላውቅም። ለዚህም ነው የካቲት 1/2018 ግንቦት7 ከትህዴን ጋር የሠጠው መግለጫ ዓላማ የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅና ለማስከበር መሆኑን በመግለጫው የጠቀስው እንዳለ ሆኖ፣ አያሌ ኢትዮጵያውያን የተሰማቸው ቅሬታ እኔም ዘንድ በሬን ያንኳኳው።

በጽሁፍ ግን መልስ እሰጣልሁ የሚል ሃሣብ አልነበረኝም — ከብዙ አስተያየቶች መካከል የአንዳንዶቹን — በተለይም የነአቶ ጌታቸው ሽፈራውን፣ አበበ ቦጋለና አሁን ደግሞ የነዓምን ዘለቀን አስተያየቶች በማንበብ የራሴን ወደ መጻፉ እስከተገፋፋሁ ድረስ!

የሁለቱ ድርጅቶች ማለትም ግንቦት7ና ትህዲን መግለጫ የሚከተለው ክፍል — ኢትዮጵያውያን በአንድነት ስም ዘወትር መረገጥና መገደልን ለመቋቋም የተደረጉትን ጥረቶች ጽዋ ፈንታቸውን የሳቱ በማስመስል የቀረበው አላግባብ ‘ግሠጻ’— ክፉኛ ይጎረብጣል። ሌላው ወገን ያልተመኘውን አንድነት ትግራዊ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ናቸው መግፋትና መንከባከብ ያለባቸው የሚለው አስተሳሰብ ጤነኛ ካለመሆኑም በላይ፣ ግብዙ ሕወሃት ሃገር ማፍረስን እንደ ፖለቲካ መሣሪያውና መደራደሪያው እንደሚጠቅምበት በተደጋጋሚ ዐይተናል።

ይህ መሆኑ እየታወቀ፣ ሁለቱ ድርጅቶች ክሠጡት መግለጫ ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፦

    “ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተነሱ የጸረ ወያኔ እንቅስቃሴዎች የበቀል እርምጃ እየተወሰደባቸው ካሉ የህወሃት ካድሬዎች በተጨማሪ ከህወሃት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ያልነበራቸው ሰዎችም የጥቃቱ ሰለባ እንደሆኑ መስማት እየተለመደ መጥቶአል። የዚህ አይነት ጥቃት እንዳይደርስ መከላከል የሚኖርብን ኢፍትሀዊ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ለዘላቂ ሰላማችንና አንድነታችን አደጋ ስላለው ጭምር ነው። ሰዎች ከህወሃት ጋር በመወገን የሠሩት ወንጀል ሳይለይ የሚወሰደ እንዲህ አይነት እርምጃ የሚያመለክተው ህወሃት በሥልጣን ዘመኑ ሁሉ ‘የትግራይ ህዝብና ህወሃት አንድ ነው” ብሎ ያካሄደው ቅስቀሳ ሰለባ መሆናችንን ነው። ይህ እንዲሆን ከተፈቀደ ደግሞ ህወሃት ሥልጣን ከእጁ የሚያመልጥ ከሆነ ህዝባችንን እርስ በርሱ ለማባላት የሚፈጽመውን ጥፋት የሚያሳካበት ዕድል መፍቀድ ስለሚሆን ለአገርና ለወገን የሚቆረቆር ቅን ዜጋ ሁሉ ይህንን አደገኛ ሁኔታ የማስቆም ግዴታ ይኖርበታል።”

ኢትዮጵያ የብዙ ብኄረሰቦች ሃገር ሆና ሳለ፡ ሕወሃቶች ራሳቸውን አንግሠው፡ ሳይነኩም ተነካን የሚሉበት ሁኔታ እየተበራከተ መጥቷል። ወልድያ ላይ በኳስ ጫወታ ስም በቪድዮ እንደተመለከትነው ትንኮሳውና የስድቡ ጋጋታ ከእነርሱው ነው የመጣው። መቱም እንዲሁ። የስለላ ድርጅቱ አባላት የሠሩትን ማስታወስም ይገባል። ተጽዕኖው ከኃይል ጋር ተዛምዶ፡ በአካባቢው ከነበሩ ኢትዮጵያውያን የነበረው ምላሽ ራስን በመከላከል ላይ ያተኮረ መሆኑ ይታወሳል። ከዚህ በፊትም አዲግራት ዩኒቨርሲቲ አንድ የኦሮሞ ተማሪ ዶርሚታሪ ውስጥ ታፍኖ መገደሉን እናስታውሳለን። ለሃገሪቷ ዘብ ቆሜያለሁ የሚለውም የሕወሃት ጦር የትግሬዎች ማስከበሪያ እንጂ የዜጎቻችን መጠበቂያ ካወቅን ዓመታት አልፈዋል።

አሁን ፊታችን የተጋረጠው ምርጫ ሃገር እንዳትፈርስ ወይንስ የዜጎች ዘወትር መረገጥ ሊሆን ነው። አብረን ከመኖራችን የተሻለ ምርጫ አለመኖሩ ግልጽ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን መሻታቸው የመዘረፋቸውና የውርደታቸው ምንጭ የለበትም ብዪ አበክሬ አምንበታለሁ!

አቶ ነዓምን ዘለቀ የሠጠው ማብራሪያ “ፍጹም ሰው እንደሌለ ሁሉ ፍጹም ድርጅት ሊኖር አይችልም” ብሎ ሲጀምር የቅን ድርጅት አሠራርና አካሄድ መሆን ያለበት ይኼ ነው ብዪ ነበር። ነገር ግን የጀመርኩትን ሳልጨርስ — ማብራሪያው ጥሩ ጎኑ ቢያይልም — ስህተት ነው ብሎ የተቀበለውን እንኳ ወደመተው ያጋድላል። በአንቀጽ 8 ስምንት ባስቀመጠው — ማለትም “8. የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ምንም ሳይደርስባቸው ገና ከጅምሩ በጠላትነት ፈርጀውት ከወያኔ ይልቅ ዱላቸውን በሙሉ ጊዜና ህይል ሳይቆጥቡ ለዚህ የጎንዮሽ ልፊያና ጠለፋ የሰጡ፣ ነገር ግን ለዚህ ውስብስብና ብዙ አቀበትና ቁልቁለት ለበዛበት ትግል ምንም ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ የማያደርጉ ግለሰቦችና ቡድኖች ማህበራዊ ሚዲያውን አጨናንቀውት እያየን ነው” ይላል።

በሌላ አባባል የአቶ ነዓምን አባባል ካነሳሱ ደስ ያሰኝን በመንጠቅ — ሌሎችን ወደ መናከስ ሲያቀና — ለእነርሱ ሲባል ነው እንዴ ይህ የስህተት ማረሚያ የመስለው መግለጫ የቀረበው የሚል ቅሬታ አሳድሮብኛል። ግንቦት 7ን በምክንያትም አለምክንትያት የሚጎነትሉት እንዳሉ አውቃለሁ። ለእነርሱ እኮ የተለየ መግለጫ በማቅረብ ሁኔታውን መዋጋትና ይህኛውን ስህተት ብሎ — በእርግጥ ስህተቱን ካመነበት — ለአሁኑ አያሌ ዜጎችን ቅር ያሰኘው ጉዳይ ላይ ብቻ ራሱን መወስን ቢችል የአቶ ነዓምንና የድርጅታቸውን ጥረት ፍሬያማ ያደርገው ነበር።

የአቶ ነዓምን አቀራረብ በተዘዋዋሪ አቋማችን ትክክል ነው የሚለውን መልሱን ለስለስ ባለ ቋንቋ ጠንከር አድርጎ እንደሚከተለው ያሠምርበታል።

“ለትግሉም ቀናኢ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የዚህ መሰሪ አካሄድ ሰለባ ላለመሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግና፡ በስሜት ሳይሆን በአምክንዮና ለትግሉ የሚጠቅመውን፡ የወያኔን ፋሽታዊ አገዛዝን የሚያስጨንቀውና የሚያዳክመውን፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ለድል የሚያደርሱ፣ የሚያበቁ ፣ ለሀገራችን ኢትጵዮጵያ ትንሳኤን የሚያፋጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል። በሰከነ አእምሮ ማሰብ የሚያስፍልግበት ስሱ ወቅት ስለሆነ፡ ቆም ብለን፡ ትንፋሽ ወስደን በረጅሙና ከፊታችን በተደቀነው ተግባሪዊ ትግል ላይ አይናችንን እንዳናነሳ ማድረግ ያስፈልጋል። ጥንቃቄ እንዳርግ በሚል በትህትና ለማሳሰብ እወዳለሁ” የሚለውን መደምደሚያ ሳነብ፣ ስለተፈጸመው ስህተት መነጋገራችን ያስገኘውን ውጤት መገንዘብ አልቻልኩም!

በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከኛም በላይ ማሾውን ከፍ ያደረግን ኢትዮጵያዊ አናሊስትነት ላሳር ከሚሉት በተለየ መንገድ፡ እዚያው ችግሩን እየተጋፈጠ፡ በነጻ ኅሊና አቶ ጌታቸው ሽፈራው ያቀረበው የሰላ ትችት ጆሮ ሊሠጠው የሚገባ ነው። ይህም ግንቦት7 የወደፊቷ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ግንባታ ትግል መሪ ለመሆን የሚታገል እንደመሆኑ በእርሱና በሕወሃት መካከል ያለውን መሠረታዊ ልዩነት — ፈራ ተባ በማለት ሳይሆን – በግልጽ ልያሠምርበት ይገባል እላለሁ!

ጌታቸው በከፈለው መሥዋዕትነት፡ በሚያሳየው የዓላማ ጽኑነትና እራሱን የቁንጅና ውድድር ውስጥ ሳያስገባ ለኢትዮጵያ እሥረኞች ድምጽ በማድረጉ፡ ወደራሱ ስቦኛል። ለዚህም በጣም አመስግነዋለሁ! በዚህ አስተያየቱ ደግሞ ብዙ ቁም ነገሮችንና ሃቆችን ከዚያው ከአዲስ አበባ በማናቸውም ጊዜ ወያኔዎች ሊያፍኑት በሚችሉበት ቦታ ሆኖ ለእምነቱ መዋጋቱ እንዳከብረው አድርጎኛል።

የእርሱስ የቅሬታ ድምጽ ምን ሆነ?
 

%d bloggers like this: