ሕወሃት ሠራዊቱ ከሕዝቡ ጎን ቆሞ ሕገ መንግሥቱን እንዲያስከብር ጥሪ አደረገ! በሕዝብ ጥላቻ የተወጠረው የአንድ ብሄረሰቡ ግንባር ምን ተንኮል ጠንስሶ ይሆን?

13 Feb

በከፍያለው ገብረመድኅን The Ethiopia Observatory (TEO)
 

  ሰኞ ምሽት እጅግ ካስገረሙኝና ገና ተጽዕኖውና ሰለሚያስከትለው ለውጥ ብዙ የምንሰማለት የዕለቱ ግዙፍ ዜና፡ ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በዓመት እሰከ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ለማስታወቂያዎች የሚያጠፋው የእንግሊዙ ዩኒልቨር (Uniliver)፥ በፌስ ቡክ፥ ዩቱብ ወዘተ የሚታዩት ሃሰተኛ ዜናዎች፡ ሕጻናትን ለአደጋ መዳረግ፣ ስም ማጥፋቶችና ሰዎችን ጎጂ የሆኑት ወዘተ — ኩባንያዎች ጭምር ተባባሪ የሆኑባቸውን ነገሮች በመቃወም — ክፍያውን እንደሚያቋርጥ ማሳወቁ ነበር።

  ከዚህ መጠነ ሠፊ ገንዘቡ ብዛት ባሻገር — በኔ አመለካከት — ይህ ውሳኔ ገና ብዙ የሚያራኩት፣ ብዙ ወገኖችን የሚያደማ ይሆናል። በአሠራርና ባህሪ ለውጥም ሊያስከትል የሚችል እርምጃ ይመስለኛል።

  ምናልባትም ሌላው አስገራሚው የዕለቱ ትልቅ ዜና — በኔ ግምት (አዛምጄ ስላየሁት ይሆናል) — ደቡብ አፍሪካ ውስጥ፡ እንደ ዐይን የሚጠበቁትን አንበሣ፡ ዝሆን፡ ዝንጀሮ፡ ወፎች፡ ወዘተ ትላልቅ እንስሣትን ከሚንከባከበው ክሩገር ፓርክ ጭምር እያስገደሉቁና አካላቸውን ከሚነግዱባቸው መካከል፡ አንዱን አቀባባይ ወንጀለኛ ባለፈው ሣምንት ፍጻሜ በአንበሦች መበላቱንና የግለሰቡ የግድያ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችም ከተረፉት የሰውነቱ ቁርጥራጦች ጎን መገኝታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

  እነዚህ ሁለት ነገሮች — በተለይም በሃገሮች ደረጃ — ብዙ ትርጉም ያላቸውና ተምሣሌታቸው በሃገሮች ለውጦች ሲመጡ በሚከተሉት ማዕበሎች ሊመሰሉ ይችላሉ። ለምሣሌ ዩኒሊቨር በሠጠው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የሚከተለው ቋንቋ ይገኝበታል፡

  “2018 is either the year of techlash, where the world turns on the tech giants — and we have seen some of this already — or the year of trust”

  ፌስ ቡክ ባለፈው ሣምንት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ደንበኞች እንደከዱትና ይህም በገበያ ላይ ያለውን ጡንቻ ሸምቀቅ ማድረጉን ማውሳቱ ይታወሳል።

  ፌስ ቡክም ሆነ ሌሎቹ — ለምሣሌ እንደ ጉጉል ዐይነቶቹ — እነዚህን ደንበኞች ለመመለስ መቻላቸው፡ ገቢያቸውና ትርፋቸው የሚቀጥልበት መንገድ በመሆኑ፡ የተጠናከረ ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ማለት ነው። ቀዳሚ ትኩረታቸው የአሠራር፥ የፖሊሲና የሥነ ምግባር ብቻ ሣይሆን፥ ምናልባት ገበያ ውስጥ ለመቆየት ወደፊት የምንመሠክርላቸው የቴክኖሎጂ መሻሻሎችም እንዲያደርጉ ይገደዳሉ።

  በአንጻሩ ግን፡ የለውጥን አስገዳጅነት መቀበል ከማኅበረሰብ፥ ከጤነኛ ሕዝብ፡ ሃገሮችና መንግሥታት የሚጠበቅ ባህሪ ነው — እንደ ሕወሃት ግትርነትና የመጣውን ሁሉ በጎልያድ ሠይፍ እንሠይፋለን ሣይሆን!

  Lions feed on wildebeest (Born Free Foundation)

  የዱር አራዊቱንም ከሚያጠቁት መካከል፡ አንዱ ልማደኛ ጠላት በአንበሶች መቀነሱ በቀላል መታየት የለበትም። ክሩገር ፓርክም ጥበቃውን ያሻሽላል ብለን መገምት እንችላለን። የተሻለ የእንስሣት ጥበቃ አስፈለጊነትም ለተሻለ የጥበቃ ቴክኖሎጂዎች መፈጠር ወይንም የፓርኩ ሠራተኞች በተጨማሪ ሥልጠናው ውስጥ እንዲያልፉ ያስገድድ ይሆናል ማለት ነው!

=====000=====

ከላይ ከተጠቀሱት ያልተለመዱ ምሳሌዎች በመነሳት የምንታዘበው፣ አሁንም የደም ጥማቱ ዕርካታ የሌለው፣ አርዮሱ ሕወሃት ተመሳሳይ ትምህርት እንደማይቀስምና በየቀኑ በይበልጥ ሕዝባችንን በጨፈጨፈ መጠን ሥልጣኑ ሥር እየሰደደ የሄደ ይመስለዋል! በግድያና ሕዝብን በዘር ወይንም ሃብትና ንብረታቸውን ለዘረፋና የራሱን አገዛዝ ዘላለማዊ ለማድረግ ብቻ ስለሆነ፣ ለዚህ ዘላቂ ድጋፍ ሊኖር እንደማይችል የሕወሃት 27ቱ ዓመታት ታሪክና የዓለምም ታሪክ ደጋግሞ አሳይቶናል።

በአንጻሩ የምናየው ግን፡ በየቀኑ ወጣቶቻችን ቢጨፈጨፉም፡ ተስፋ ባለመቁረጥ ነጻነታቸውን ለመጎናጸፍና ዜጎች ሰላማዊ ሃገር እንድትኖረን የሚያደርጉት ትግል ይበልጥ እንደሚጧጧፍና ብዙ ድጋፍም ሊያሰባስብ እንደሚችል ነው።

ሕወሃቶች ዜጎችን እንደፈለጉ ማሠር ቶርች ማድረግ፡ መጭውን ትውልድ ዘር ለማሳጣት ብልት የማኮላሽት ወንጀል ጭምር፡ የዓለም ሕዝብም አብሮን እንዲፋረድ ዘመቻውን ማስፋፋቱ ፍሬያም እንደሚሆን ከወዲሁ መገመት ይቻላል።

ታዲያ በዚህ ረገድ እርስ በእርሱ የሚላተሙ ሲግናሎችን ከመላክ ውጭ፣ ሕወሃት የሃገሪቱን ችግሮች ለመፍታት ፍላጎት ወይንም ብቃት አላሳየም። ሲያቅተውም በሃቅ ላይ በተመሠረተ መንገድ የሃገሪቱን የፖለቲካ ኃይሎች ሙሉ ትብብር መሻት ሲችል፣ የግንባሩ ጥረት ከተራ ሌብነትና አጭብርባሪነት አልዘለለም!

ይህንን በተጨባጭ ምሣሌ ከዚህ በታች እንመልከት!

መከላከያ ሚኒስትሩ አንገታቸውን ለገመድ ማዘጋጀትን መረጡን?

መከላከያ ሚኒስትር ሲራጅ ፈርጌሣ ሰኞ የካቲት 12/2018 ስድስተኛው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቀን አከባበር ላይ ባደረገው የሚከነክን ንግግር፣”በሃገሪቱ ቀጣይነት ያለው ሰላም እንዲረጋገጥ፡ መከላከያ ሠራዊቱ ከሕዝቡ ጋር በመሆን ኃላፊነቱን እንዲወጣ” ጥሪ አድርጓል

ሠራዊቱ ብሔራዊ ጥሪውንና ግዴታውን አልተወጣም የሚለው ንግግሩ ውስጥ የሚመላለሰው ስሞታ ምን ለማድረግ ታስቦ ይሆን የሚለውን ጥይቄ ቢያጭርብን እንደዜጎች ጤነኛና ጠንቃቃ መሆናችንን ብቻ ነው የሚያመልክተው።

በኢትዮጵያ ላይ እስካሁን ምንም ዐይነት ገሃድና ቀጥታ ጥቃት ከውጭ ሳይቃጣባት — አገዛዙ ለፕሮፓጋንዳ ጥቅሙ ራሱ ከፈጠራቸው አዕምሮ ውስጥ ካሉት ጭራቆች ውጭ (boogeyman) — የመከላከያ ሚኒስትሩ ለምን ይህንን ጥሪ ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ እንዳገኘው ግልጽ አይደለም። የሚያስገርመው — ምናልባትም የሃገሪቱን የውስጥ ችግሮችና ወይንም በሥውር የታቀደውን ያጋልጣል በሚል አንደሆን አልታወቀም — ፋናና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንኳ ይህንን
የሚኒስትሩን ጥሪ ትኩረት ሳይሠጡት ቀርተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሕዝቡ በሕወሃት አስተዳደር ላይ በአመጽ መነሳቱን በመሸፋፈን፡ ሚኒስትር ሲራጅ ፈርጌሣ ችግሩን ቀጠናዊ (የአፍሪካ ቀንድ) ለማስመሰል ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም፡ አሳማኝ መሆን አልቻለም። ለዚህም ዋናው ምክንያቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ አመጽ ለመግባት መገደዱ ነው። በሕወሃት የመብት ረገጣዎች፣ ግድያዎች፣ ሃብትና ንብረቶች ዘረፋዎች፣ አስተዳደራዊ በደሎችና አናሳው ቡድን በመንግሥት ሥልጣን ከጨበጠበት ጊዜ ጀምሮ በሥልጣን መባለጉና በተለይም ዘረኝነቱ ሰብዓዊ ክብር-ነክ መሆኑን ዜጎች ለሃያ ሰባት ዓመታት በተደጋጋሚ ሲያማርሩ ቆይተው “በቃ!” የሚሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል — የዩኒሊቨር ወይንም የአምበሶቹ ትዕግሥት ማለቅ ጋር ሊመሳሰል ይችላል!

ይህንንም የበደልና “አፈና በቃኝ ስሜት” ለማሳየት ነው ሕዝቡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተነስቶ ለሕወሃት ወንበዴዎች በሩን ለማሳየት መላው ኅብረተሰብ — ገበሬው፣ ወጣቱ፣ ምሁሩና ሠራተኛው — ከ2014 ጀምሮ ትግሉ የገነፈለው! በነዚህ ባለፉት ሶስት ዓመታትም ትግሉ እየደረጀ እንጂ ለሕወሃት ጭካኔ፣ የመሣሪያ፣ የኃይል ጋጋታና አደገኛ ሴራ መንገድ አልሠጠም! ሕወሃት ከነገ ዛሬ የኢትዮጵያውያንን ልብ በመሣሪያ የማንበርከኩና በገንዘብ ኃይል የመግዛቱን ዕድል እንደ ቀድሞ ቅኝ ገዥዎች ለመያዝ ደጋግሞ ቢሞክርም አልተሳካለትም!

የሕወሃት ዓላም ምንደነው? ሲቪል ማኅበረሰብን ከራስ ጸጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ከታጠቀ ሠራዊትና ዜጎችን በግፍ መጨፍጨፍን ሙያው ካደረገ ሠራዊት ጎን አቀናጅቶ ኅብረተሰቡን መባላት አስቦ ይሆን? ዓላማው ይህ ካልሆነ ተላላኪው ሲራጅ ፈረጌሣ አሁን ያንን ጥሪ ያደረገበት ምክንያት አርኪ መልስ አያገኝም። ሕወሃት ይህንን ቢያደርግ፡ ካለፈና ከአሁኑም ታሪኩ በመነሳት ስንመለከት የሚያስገርም አይሆንም!

የዛሬዎቹ የሕወሃት ባለሥልጣኖች፡ በረሃ ሳሉ ለፈንጠዝያ ያወጧቸውን ተገዳላይ ሴት ጓደኞቻቸው ሲያረግዙ — አቶ ገብረመድኅን አርአያ እንደገለጹት — ከነጽንሱ በመግደል የጀመሩ ግለሰቦች (ቡድን) በመንግሥት ሥልጣንም የሚፈጽሙት የዜጎችንም ደም ማፍሰስ ከዚህ በተለይ መልኩ ሊታይ አይችልም።

ልብና ጆሮ ለነበረውና ላለው ሕዝብ ይህ ጸሐፊ የሚመክረው ሃገራችንን ዛሬ ሕወሃት ከዘፈቃት ችግር ለመወጣት መፍሄው — ይበልጥ ሴራ መጎንጎን ሣይሆን፡ በምንስማማባቸው ጉዳዮች ላይ በማተኮር፡ ፖለቲካዊ መፍትሄዎች መሻት፤ ለሕዝባችን ኑሮ መሻሻልና — በዕጥፍ ቁጥር አደገች እየተባለ ወደኋላ ለተንሸራተተችው ሃገራችን በዕድገት ከሌሎች በታች መሆኗን በመሰወር ከችግሮቻችን ለመላቀቅ አለመቻላችን በቀድምትነት ሕወሃት እንዲቀበል ማድረግ ይገባል።

ሕዝባችን ሕወሃትን ደግፎ ጠላቶቹን የሚያሳፍረው የዕድገቱ መለኪያ የዘወትሩ ማምታታት፣ ፕሮፓጋንዳና ቅዠት ሳይሆን፣ በእያንዳንዱ ቤት — ቢያንስ በቀን ሶስቴ ሲበላ የሚቻልበት ሁኔታ — ቀደምት ተግባር ሊሆን ይገባል። ውሃና መብራት ጠፍቶ የሰው ልጅ ራሱን በሚጠየፍበት ሁኔታ ልማትና ዕድገት ሊሆን አይችልም — ምንም እንኳ በዚህች ደሃ ሃገር የሕወሃት ሰዎች ሁኔታዎች ተሟልቶላችው በአንደኛው የዓለም ክፍል እንደሚኖሩ ሃብታሞች የኣንደኛውን ዓለም ደረጃ እየመኖሩ ቢሆኑም፣ የእነርሱ አኗኗር የአብዛኛው ሕዝባችን ሕይወት አይደለም!

ለዚህ ነው የዓለም ሕዝብ ለሕወሃቶች አመራር፡ አሠራርና ምግባር ድጋፉን መለገሥ የማይችለው! ዛሬ አለንላችሁ የሚሏችሁ ሁሉ ኦባማ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመንግሥት — ብትፈልጉ በአፍጫችሁ ይውጣ ብሎ ሐምሌ 2015 እንደነገራችሁ — በሌሎች ሃገሮች ውስጥ ለሚነሱ እነርሱ ለማይደግፏቸው ግጭቶች ወታደርነት ሥራ እንድታከናውኑላችሁ ብቻ ነው! የእንግሊዝ መንግሥትም ለዚህ ነው — በ2011— አፍንጫችንን በሁለት ጣቶቻችን አፍን አድርገን ነው ከሕወሃት አስተዳደር ጋር የምንሠራው ያለውን አትዘነጉትም:

(“[I]ts approach to political governance presents both substantive challenges to sustainable development and reputational risks to partners!”

ሕወሃት የመረጠውን ወገን አስታጥቆ ሲቪል ግጭት ማባባስ ይሻ ይሆን?

በተለይም ወጣቱ በፀረ-ወያኔ ግንባር ቆርጦ ተሠልፎ እጅግ አያሌ መሥዋዕነት በሕይወቱ፡ የወደፊት ስብዕናውና ዕድሉ እየከፈለ በሚገኘብት ሁኔታ፡ ያንን በመሸፋፈን፡ የምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ የእርስ በእርስ ግጭት፡ “አስከፊ ድህነትና የፖለቲካ ትርምስ” በሚራኮትበት ማጥ ሃገራችንም ሰማጭ እንዳትሆን በማለት ሲራጅ ፈርጌሣ — የሃሣዊ መሣዊ ሥጋት — በማሰማት፡ ሠራዊቱ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ከሕዝቡ ጋር ሆኖ እንዲወጣ ጥሪውን ያቀረበው። ነገር ግን የዚህ መሠሪ ጥሪ ዓላማ በምን መልኩ እንደሚተረጎም፡ የመከላከያ ሚኒስትሩ አልገለጠም።

ሕወሃት እንዲህ ነው ብሎ እንኳ ቢናገር መካድ የማያስቸግረው ድርጅት ስለሆነ፡ የሚያዋጣው በጥሞና አዳምጦና ነገሩን አላምጦ ለማናችው ነገር መዘጋጀት ብቻ ነው!

የመከላከያ ሚኒስትሩ ንግግር ይዘት ለማናቸውም አተረጓጎም ክፍት ከመሆኑ የተነሳ፣ በአንድ በኩል ሕዝቡን በሕገ መንግሥት ጠባቂ ወይንም አስከባሪነት አደራጅቶና አስታጥቆ፡ ሕዝቡን ሊያፋጅ ሊሆን የሚችል ነው የሚል ትርጓሜ ቢሠጠው፣ ብዙ ጥንቃቄ ስለሚያስፈልግ ዜጎች በጥንቃቄ ሁኔታውን እንዲከታተሉ ጥሪ ቢደረግ አስገራሚ ሊሆን አይገባም!

ይህ ካልሆነ በየቀኑ ከፍተኛ የዜጎች ቁጥር በሕወሃት እየተጨፈጨፈ፡ ሚኒስትሩ ለምን ይሆን ሕዝቡ በሕወሃት አስተዳደር ላይ መነሳቱን የሽሸገው? ለምንስ የአካባቢ ሃገሮች ወይንም ቡድኖች በሃገራችን ላይ የተነሱባት ለማሰመሰል ሞክረ ለሚለው ጥያቄ ንግግሩ መልስ አይሠጥም። ምናልባትም ሃገርን መጠበቅ፥ ሕገ መንግሥት ማስከበር በሚል ሽፋን በተወሰኑ ዜጎች አማካይነት፥ የተደራጀና የታጠቀ ኃይል በመፍጠር ከፈራቸው ‘ኃይሎች’ እንዲታደጉት ሕወሃት ሂሣቡን እያሠላ ያለ ይመስላል።

እስካሁን ሠራዊቱ ያከናወናቸው ሥራዎችምን የመከላከያ ባለሥልጣኖች ተራ በተራ ሲዘረዝሩ፣ በቀድምትነት የተነሱት በተለይም የሕዝብና መንግሥት የመሠረተ ልማት አውታሮችን ከሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ከመከላከል እስክ “ሥርዓት አልበኝነትን በመቆጣጠርና የሃገር ዳር ድንበርን ከውጭ ወራሪ ሃይል በመከላከል ረገድ ሥፊ ሥራዎች መሥራቱ” በኢዜአ ተገልጿል።

ሕወሃት የዘለቄታ አገዛዝ አጀንዳውን የሚገልጸው፣ “የጀመርነውን ሕዳሴ ግብ ለማድረስ” በማለት ሲሆን፡ ይህም በመከላከያ ሚኒስትር ሲራጅ ፈርጌሣ ንግግር ውስጥ ሠፋ ብሎ ተገልጿል፤

ሠራዊቱ ኅዳር 29 1987 በአዋጅ መቋቋሙን የተናገሩት የመከላከያ ዩኒቨርሰቲ አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ሀለፎም እጀጉ፥ የተቋቋመው ሠራዊትም ሚዛናዊ የብሄር ተዋፅኦ እንዲኖረው መደረጉን ለትዕዝብት ጠቅሰዋል።

ሕወሃት በዚህ ዕለት ስሜቱን የሚያስተጋቡለት ሰዎች በኢዜአ ቃለ መጠይቅ እንዲካተቱ በማድረግ፣ እነአቶ ሀብታሙ አብርሃ በሠጡት አስተያየት መከናውን ያለበት: “ወጣቱ በአገሪቷ በሚከሰቱ ብጥብጦችና ሁከቶች ላይ እንዳይሳተፍ ከቤት ጀምሮ መሰራት አለበት” በማለት ሕወሃት የፈለገውን አሰምተውታል። ከዚህ ቀጥሎ በምን መልኩ ይከሰታል የሚለው በሂደት የሚታይ ነው!

ከኢቢሲ ቪዲዮ ልብ ብሎ ላዳመጠው ሲራጅ ፈርጌሣ ሠራዊቱን በተዘዋዋሪ መንገድ ሥራችሁን — ግድያውን ማለት ነው — በደንብ አልሠራችሁም ነው የሚላቸው። በዚህች ዕለት ጨረቃ ግን በሃማሬሳ፣ በኦሮሚያ፥ ደባርቅና ደቡብ፣ እንዲሁም ገና ባልሰማናቸው አካባቢዎች የብዙ ዜጎች በሕወሃት ጭዳ ተደርገዋል!

በሕወሃቶችና ቅጥረኞቻቸው የኮድ ቋንቋ ሕገ መንግሥታችሁን ተንከባከቡ ሲባል፣ ትርጉሙ ለሕወሃት ጥቅሞች ቁሙ ማለት ነው!

ምንደነው ኢትዮጵያኖች ምንደነው የሚያስፈልገን?

ኢትዮጵያውያን መቆም የሚገባን ግን ለማናቸውም ዐይነት መንግሥት ሆነ ግለሰብ ሥልጣን መሆን የለበትም። የሚያስፈልገው ሥልጣንን በሕግ ገድቦ የሚያስተዳድር ሕግ፣ መንግሥትና መንግሥታዊ ተቋሞች ናቸው። እንዲሁም የሕዝብ ምክር ቤትና ፍርድ ቤቶች ከሕወሃት ቅጥረኝነት ነጻ መሆን አለባቸው!

በዴሞክራሲያዊ አሠራር፣ የመንግሥት አሠራርን የሕዝብና የመንግሥት ግንኙነት በየወቅቱ መፈተሽ ይኖረበታል።

ከመንግሥትና ምክር ቤቶች ግምግማ ባሻገር የእነዚህንም ለሕዝብ ሃገር ጥቆሞች መቆም፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ጭምር ተሳታፊነት፣ ምሥክርነትና ጥናቶች በየወቅቱ መፈተሽ ይኖርባቸዋል! መንግሥት የሚባልው ቡድን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለዜጎች መብቶች ቅድሚያ እንዲሠጥ ይገደዳል።

እያንዳንዱ ዜጋ ጥቅሙን በሚያይበት ዐይንና መንገድ — እንደዛሬው ሳይሆን — መንግሥትን ሊደግፍና ሊቃወም ይችላል ማለት ነው። በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ሃገር፡ የሕዝብና የመንግሥት ትሥሥርና መራራቅ የሚወሰነው ሕዝቡ በሚያየው የራሱ፡ የቤተሰቡና የማኅበረሰቡ ፍላጎቶች ተግባራዊነትና የመርሆቹ ተቀባይነት ነው!

ሕወሃት ባለፉት 27 ዓመታት ሕወሃት እንዳደረገው፡ ለካድሬዎች ጥናትና ምሥክርነት ክብደት መሥጠት ራስን ጠልፎ ከመጣል አይለይም!

ዜጎች ሕግ መከበር መስሏችው ለሕገ መንግሥቱ ቆመው ኢትዮጵያ ውስጥ ያተረፈልን ነገር ቢኖር፣ ዜግነታችንን መገፈፍ፣ መሬቶቻችንን መነጠቅ፣ ቤቶቻችን በፈለገው ባለሥልን ትዕዛዝ መፍረስና ለሕውሃቶችና ቅጥረኞቻቸው መተላለፍን ነው።

ጋምቤላ ለምን ተደፈረች? በአዲስ አበባ ዙሪያ የነበሩ ገበሬዎች ለምን ከአራሽና አምራችነት ወደ ልመና፣ ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው ወደሴተኛ አዳሪነት እንደተዛወሩ፣ ቀሪውቻችንም በቀቢጸ ተስፋ ነገ ይሻል ይሆናል በማለት ወግኖቻችን ሲዋረዱ፣ ሃገራችን ስትመዘበር ተመልካች ተመልካች ለመሆን ተገደናል!

አሁን ካለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት የተማርነው ነገር ቢኖር፡-

  (ሀ) ተጠራጣሪ መሆንና ከባለሥልጣኖች ቃል ይልቅ ነገሮች/ጉዳዮች በሕግ መሠረት መፈጸማቸውን ማረጋገጥ መሆን አለበት። ሕወሃት በቅርቡ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስበሰባውን ትግራይ ካደረገ በኋላና ወደ ኢሕአዴግነት አዲስ አበባ ላይ ተቀይሮ እንባውን እየረጨ “ጥፋተኛ መሆኔን ተግነዝቤአለሁ” ሲል ከርሞ፣ ተክትሎ የመጣው በወሎና በኦሮሚያ የተጠናከሩ የሕዝብ ጭፍጨፋዎች እንደሆነ አሁንም ለአፍታም መዘንጋት የለብንም፤

  (ለ) በግለሰብም ደረጃ፣ ነፍስ በላው ደብረጽዮንም ይሁን ሌሎቹም ከማጭበርበር ነጻ ባለመሆናቸው፣ ለዜጎች ማንም ምንም ይበል፡ በብሔራዊም ሆነ በአሰተዳደር ደረጃ የሚቀበሏቸው ጉዳዮች በጊዜ ገደብ የታጠሩ፣ በክትትልና አፈጻጸምም ተጠያቂው በየደረጃው መንግሥታዊ ተቋምና ኃላፊዎቹ መሆን ይኖርባቸዋል! ሕወሃት በፖለቲካ እሥረኞች ፍቺ ዞሮ የፈጸማቸው ምግባረ ቢስነቱ ዓለምን ማስገረሙን — ከቀናት በፊት ከቢቢሲ የተወረወረውን ትዕዝብት ሁላችንም ዘወትር ማስታወስ ይኖርብናል።

ሕወሃት እስካሁን ለተደረጉት ጭፍጨፋዎች ክብደት ሳይሠጥና ትዕዛዝ የሠጡትንና ቃታ የሳቡትን ለፍርድ ሳያቀርብ፡ ከኢትዮጵያውያን ጋር ለመነጋገርና ለመደራደር መሻቱ ከተለመደው ደባና ተንኮል ክመፈጸም ውጭ የሚያተርፈው ነገር አይኖርም።

እንደ ዩኒለቨር ዜጎች አንከፍልህም፤ አንገብርልህም ሊሉት ይገባል — ግብር ክፍያቸውን ጭምር በመያዝ። በውጭ ያለን ዜጎች በዚህ ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወት እንችላለን። መታወቅ ያለበት ግን ሕወሃት በተንኮልና በማጭበርበር የተሞላ ስለሆነ፡ በባንኮች የውጭ ምንዛሬ እንደሚሰበስብ ሁሉ፡ ሃገር ውስጥ ሆነው በሥውር የመመንዘሩን (ጥቁር ገበያ) ሥራ እራሱም መሥራት ስለጀመረ (በጌታቸው አሰፋ ቢሮ በኩል)፣ ሃገር ውስጥ በሥውር የሚመነዘረው መንግሥት እጅ አይገባም ብሎ ማመን ስህተት ነው።

ስለሆነም፣ የሕወሃት አሰተዳደርን የውጭ ምንዛሬ ማስራብ ከተፈለገ፥ ፍቱኑ መንገድ ምንም ዐይነት ከረንሲ ሃገር ውስጥ እንዳይገባ ቀዳዳውን ሁሉ መለበድ ነው! ባለፈው ታህሣስ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፥ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ባለበት ወቅት 351 ዐይነት ዕቃዎች መገደኞች ከታክስ ነጻ እንዲያስገቡ መፈቀዱን ምክንያት ማስታወስ ይገባል!

ያ መመሪያም ሶስት ወር እንኳ ሳይሞላው፥ በቅርብ መነሳቱና ዕቃዎቻቸውን ይዘው የመጡ ሰዎች በድንገት ግብር እንዲከፍሉ እየተደረጉ ናቸው!

በአጭር አባባል፡ ከእንግዲህ ኢትዮጵያውያን መቆም የሚገባን ለሕጋዊነትና ለዜጎች መብቶች ቅድሚያ መሠጠት መሆን አለበት። ማናቸውም ዐይነት መንግሥትን ሆነ ባለሥልጣን በሕግ ገድቦ የሚያስተዳድር መንግሥት እስካልመጣ፣ ሕዝቡም በሕግ አፈጸጸምም ሆነ በመንግሥት መ/ቤቶች ሥራ አፈጻጸም በሕግ ላይ በግልጽ መሣተፍና ድምጽ የመሥጠት አሠራር እስከሌለው ድረስ፣ ቀጥሎም የሚሆነው ይኸው የምናውቀው ነው!

ያለፈውን ግማሽ ምዕተ ዓመት ብንረሳው እንኳ፣ ባለፉት ሁለት ወራት ሕወሃትና ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ሕዝብ ጫማ ላይ ተደፍተው ምን ያህል የሃሰት እምባ እንዳነቡና ወዲያውኑ ግን ወሎ ውስጥ ጭፍጨፋውን አፋፋሙት! ብዙ ወገኖቻችን አዛውንት ጭምር እስካሁን የደረሱበት አለመታወቁ ልብ ሊሉ ይገባል!

አሁን ባለንበት ሁኔታ፡ መደማመጡ ጠፍቶ ዜግነትም ለዜጎች ምንም ዐይነት መብቶችና ከበሬታ እንዳያስገኙ ማድረግን ሕውሃት እስከቀጠለ ድረስ፡ ሃገሪቱ አደጋ ላይ መሆኗ መታወቅ ይኖርበታል! ያ ነው የሕወሃቶች የጥፋት ምንጭ — ከነጦር መሣሪያው በክሩገር ፓርክ በእንስሳት እንደተበላው አጥፊና በመሣሪያው ብቻ የተማመነ አተርፍ ባይ አጉዳይ!

በዚህች ሰዓት ሕወሃት እዚያ ክሩገር ፓርክ ውስጥ ነው!
 

%d bloggers like this: