መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ምክክር እንዲደረግ ጠየቀች!

25 Feb

Posted by Ethiopia Observatory (TEO)
 
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንድተተዳደር መደረጓ “ሀገሪቱን ይበልጥ አሳሳቢ በሆነ ውስብስብ ችግር ውስጥ ሊያስገባት ይችላል የሚል ስጋት” እንዳለባት ገለጸች፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት “አዋጁን ማንሳት በሚቻልበት መንገድ ላይ እንደገና እንዲመክርም” ጠይቃለች፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ዛሬ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጿ ላይ ባወጣችው ረዘም ያለ መግለጫ “ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበት ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ ነው” ብላለች፡፡ “የሀገር አንድነት እና የህዝቡ ሰላም ይበልጥ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲገነባ በጋራ መግባባት ላይ መስራት ያስፈልጋል” ስትል ለሚመለከታቸው አካላት ጥሪ አቅርባለች፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ ፕሬዝዳንት ቄስ ዮናስ ይገሱ ጥሪውን በቅድሚያ ለመንግስት መስጠታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

“በቤተክርስቲያኒቱ ደረጃ የእኛ አመራር በሰጠው ውሳኔ መሰረት ይሄንን ጥሪ ለኢትዮጵያ መንግስት፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለሲቪል ማህበራት ሁሉ ጥሪ አቅርበናል። ይሄ የምንፈልገው ሀገራዊ መግባባት ስለሆነ በዚያ አቅጣጫ እንዲሰራ የሚል ነው። ያንን ሀገራዊ መግባባት የሚያደናቅፉ ሁኔታዎች እንዳይኖሩ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ነው ” ሲሉ የመግለጫውን መልዕክት አስረድተዋል።ቤተክርስቲያኒቱ ለኢትዮጵያ መንግስት ባቀረበችው ጥሪ “ሀገሪቱ ለሁለተኛ ጊዜ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር እንድተዳደር መደረጉ የፈነጠቀውን የሠላም እና የመግባባት ተስፋ አደብዝዞ ሀገሪቱን ይበልጥ አሳሳቢ በሆነ ውስብስብ ችግር ውስጥ ሊያስገባት ይችላል” ስትል ስጋቷን ገልጻለች፡፡

“የኢትዮጵያ መንግስት ያሉትን ሁኔታዎች በጥልቀት አጢኖ ቢቻል አዋጁን ማንሳት በሚቻልበት መንገድ ላይ እንደገና እንዲመክር” ስትልም የመፍትሄ ሀሳብ አቅርባለች፡፡ “አዋጁ ስራ ላይ ይዋል ከተባለ ደግሞ በአፈጻጸሙ ወቅት የዜጎች መሠረታዊና ሰብዓዊ ክብር እንዳይነካ ብርቱ ጥንቃቄ እንዲደረግ” ስትል ቤተከርስቲያኒቱ አሳስባለች፡፡ “የኢትዮጵያ መንግስት የሀገሪቱን ሕዝብ ይቅርታ ከመጠየቅም አልፎ በህዝቡ ጥያቄ መሰረት የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት መጀመሩ የሚያስመግነው ነው” ያለችው ቤተክርስቲያኗ መንግሥት ይህንኑ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቃለች፡፡
 
________________________________________________________________________________________________________________________________________________

________________________________________________________________________________________________________________________________________________
 

”መንግስት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እና የሃሳብ ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይትና ድርድር ለማስተናገድ” የጀመረውን እንቅስቃሴም እንዲቀጥል አሳስባለች፡፡ ገዢው ፓርቲም ሆነ መንግስት “ከማንኛውም እቅዱ ይልቅ ለሀገር ሰላም፣ ለህዝቡ ደህንነት እና አንድነት ቅድሚያ እንዲሰጥም” መክራለች፡፡ መንግስት ሀገራዊ መግባባት እንዲኖር “የተለያየ ግንዛቤና አመለካከት አለን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች (ፓርቲዎች)፣ ሲቪል ማህበራት፣ ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የኃይማኖት መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች የሚሳተፉበት የጋራ መድረክ በማመቻቸት ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ” ጠይቃለች፡፡
/Mereja.com
 

%d bloggers like this: