ራሱን ኮማንድ ፖስት ብሎ የሚጠራው ቡድን በኦሮምያ ክልል አመራሮች ላይ እርምጃ እየወሰደ ነው

8 Mar

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 
(ኢሳት) የካቲት 29 ቀን 2010 ዓ/ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሰበብ በማድረግ ራሱን ኮማንድ ፖስት ብሎ የሚጠራው ቡድን በኦሮምያ ክልል ፖሊሶችና አመራሮች ላይ የሚወስደውን እርምጃ ቀጥሎበታል።

እርምጃው በኦህዴድ ላይ ከፍተኛ አደጋ ደቅኖበታል። በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ በተለይን በለገጣፎ አካባቢ ተመድበው ይሰሩ የነበሩ የኦሮምያ ፖሊስ አባላት ምሽት ላይ በድንገት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን፣ በወረዳው ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ አመራሮች መታሰራቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በለገጣፎ 3 የአጋዚ ወታደሮች በኦሮምያ ፖሊሶች ጥቃት ከተፈጸመባቸው በሁዋላ፣ ትናንት ፖሊሶችን የመከታተል እርምጃው ተጠናክሮ እንደነበር የገለጹት ምንጮች፣ ምሽት ላይ በርካታ ፖሊሶች ተይዘው ወደ እስር ቤት ተወስደዋል።

ፖሊሶችን የማባረርና የማሰር እርምጃው በሰንዳፋ፣ ገላን፣ ሆለታ፣ ቡራዩ፣ ሱሉልታ፣ ወለጋ፣ ሃረር፣ መቱና ጂማ የቀጠለ ሲሆን፣ ከዚህ በተጎዳኝ የቄሮ አባላት ናቸው የተባሉ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ተይዘው ታስረዋል።

የአይን እማኞች እንደገለጹት ታርጋ ያላቸውና የሌላቸው፣ የቤትና የመንግስት መስሪያ ቤት መኪኖች እንዲሁም የጤና ጥበቃ አምቡላንሶች ሳይቀሩ በምሽት የታፈሱ ወጣቶችን ይዘው ወደ አልታወቀ ስፍራ ወስደዋል። እርምጃው በኦህዴድ ላይ የተቃጣ ዘመቻ ተደርጎ ተወስዷል።

የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታርያት የሆኑት አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ የሰዎችን መያዝ ቢያረጋግጡም፣ ኦህዴድ ግን እስካሁን መግለጫ ከመስጠት ተቆጥቧል። በተለይ ከቄሮ ጋር አብረው ይሰራሉ የተባሉት የድርጅቱ አባላት እየተያዙ መታሰራቸው፣ አጠቃላይ የኦህዴድን መዋቅር የማፍረስ ዘመቻ ተደርጎ እየተቆጠረና በአባላቱ ላይ ብዥታ እየፈጠረ ነው። በሌላ በኩል የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህርና ታዋቂው ጸሃፊ መምህር ስዩም ተሾመ መታሰሩ ታውቋል።

ስዩም ስለአገዛዙ ምንነት በድፍረት በመጻፍ እንዲሁም ምሁራዊ ትንታኔዎችን በመስጠት ይታወቃል። የተለያዩ ማስፈራሪያዎች ሲደርሱት የነበረው ስዩም፣ በኦሮምያ የተጠራው የ3 ቀናት የስራ ማቆም አድማ እንደተጠናቀቀ በወታደሮች ተወስዶ ታስሯል። ሰሞኑን ወታደራዊ አዛዦች እያስወሰዱ ባለው እርምጃ የ10 ልጆች አባት የሆኑት አቶ ድጋፌ ደንዴናን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፣ ብዙዎችም ቆስለዋል። የአጋዚ ወታደሮች ሱቆችን እየሰበሩ በመግባት ንብረት መውሰዳቸውንም የአይን እማኞች ይገልጻሉ።
 

%d bloggers like this: