የሁመራ ወረዳ አስተዳደር የፌደራል መንግስት ተወካዮች በአማርኛ እንዳይናገሩ ከለከለ! በጓሮ በር ሃገር የመገንጠል ሀ፡ ሁ…

16 Mar

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 
መጋቢት 07 ቀን 2010 ዓ/ም (ኢሳት ዜና) የሁመራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ ከፌደራል መንግስት ተወክለው ባለሃብቶችን በብድር ጉዳይ ለማወያየት የሄዱ ባለስልጣናት በአማርኛ ስብሰባ እንዳይመሩ ከልክለዋል።

መጋቢት 5 /2010 ዓ.ም በሁመራ ከተማ አስተዳደር አዳራሽ ከፌደራል መንግስቱ የተወከሉ አቶ አማኑኤል ተስፉ የተባሉ ግለሰብ ስብሰባውን በአማርኛ ሲመሩ የወረዳው አስተዳደሪ “በአማርኛ ስብሰባ ማድረግ አይቻልም። ስብሰባው በቋንቋችን ነው መደረግ ያለበት” በሚል ስብሰባው በአማርኛ እንዳይመራ አድርጓል።

ቀድሞ የጎንደር ክፍለ ሃገር ግዛት የነበረው ሁመራ፣ በኢህአዴግ ዘመን ወደ ትግራይ እንዲካለል ቢደርግም፣ አብዛኛው ህዝብ አማርኛ ተናገሪ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በጎንደር በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ተሳትፈሃል በሚል ታስሮ የሚገኘው የወጣት ተስፋ ማንዴ አውደው ሃብትና ንብረት ተዘርፎ ለአንድ የህወሃት ደጋፊ የሆነ ባለሃብት ተሰጥቷል።

የወልቃይት አካባቢ ተወላጅ የሆነው ወጣት ተስፋ፣ 60 የቀንድ ከብቶችን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶቹም ተዘርፈው ለባለሃብቱ ተሰጥቷል። ወጣት ተስፋው በ2008 ዓም በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ወታደር ገድለሃል ተብሎ የታሰረ ሲሆን፣ እስካሁን ምንም አይነት የሰው ወይንም የሰነድ ማስረጃ ሊቀርብበት አልቻለም።

አቦጥር በተባለ አካባቢ ያርሰው የነበረው ሰፊ መሬት ተወስዶ በቅፅል ስሙ ዲዛ ለተባለ የህወሓት ባለሃብት ተሰጥቷል። ባለሀብቱ የወልቃይት ተወላጆችን በማሳሰርና በማስገደል እንደሚሳተፍ የአካባቢው ተወላጆች ይገልጻሉ። በወልቃይትና አርማጭሆ ውስጥ ሰፋፊ መሬቶች ያሉት ይህ የህወሃት ወኪል ባለሃብት፣ ተገቢውን ግብር የማይከፍል ከመሆኑም በተጨማሪ የአካባቢውን ባለስልጣናት እያስጨነቀ እንደሚገኝ ምንጮች አክለው ገልፀዋል።
 

%d bloggers like this: