በከፍያለው ገብረመድኅን The Ethiopia Observatory (TEO)
ከላይ አርዕስቱ የተመለከተው መግለጫ ሙሉ ለሙሉ የዚህን አምድ አዘጋጅ ተቀባይነትና ድጋፍ አግኝቷል!
ይህ መግለጫ —እንደተለመደው አሠራር፡ በመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሣይሆን—ሐሙስ ሰኔ 14/2018 በፌዴራል መንግሥቱ ስም የተሠጠ መሆኑ ልብ ሊሉት ይገባል። በተለምዶና በአሠራርም ይህ ከበድ ላሉ የሃገር ጉዳዮች — ብዙ ሕይወት የቀጠፈ ድንገተኛ አደጋ፡ ወረራ፡ የመንግሥት ለውጥ ወዘተ — የተቆጠበ መሆኑ ሲታሰብ፣ አሁን የመግለጫ ሠጭው ማንነት (ብሔራዊ መንግሥት) ግምት ውስጥ ሲገባ፡ተለምዶዊው ሁኔታ አለመሆኑን ጠቋሚ ነው።
ለእኔ ሁለት ዕይታዎችን አስጨብጦኛል።
ሀ. መግለጫው ስም ባይጠቅስም ለሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ መርዘኛ ሕዝብ፣ ሃገርና መንግሥትን ተጋፊነት ምላሽ ነው። ጠቃላይ ሚኒስትሩ ናቸው የጻፉት ለማለት መረጃ ባይኖረኝም፣ይህን በሕዝቡ፡ በመንግሥታቸውና በሃገሪቱ ስም ክብደት የሚሠጥ ምላሽ እንደመሆኑ: ሌላው ቢቀር ለሕዝብ ከመለቀቁ በፊት ተመልክተው ቡራኬያቸውን ሠጥተውታል የሚል ግምት አድሮብኛል።
ለ. የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሃገሪቱ መንግሥት እንደሌላት በሚመስል ደረጃ፡ የጥቂት ዘረኛ ድርጅታዊ ባለሥልጣኖች ጥቅም ተጓደለ በሚል ቅሬታና የወደፊቱ ጥቅሙ አሳሳቢነትን በሚመለከት ሰኔ 13/2018 ያወጣው መግለጫ ተናዳፊነት ሕግ፡ደንብና ሥነ ሥርዓት የጎደለው በመሆኑ፡ ይህንን ለማጋለጥና መስመር ለማስያዝ የታሰበ መንግሥታዊ መግለጫ ይመስላል።
አሁን ዋናው ኢትዮጵያውያን ልንጨብጠው የሚገባን ሁኔታ፡ ሕወሃት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አመራርና መንግሥት ባለመደሰቱና ዙፋን ገልባጭ አድርጎ ሰለተገነዘባቸው፡ ውስጥ ለውስጥ ሲያካሄድ የነበረውን ተንኮልና ደባውን አደባባይ አወጥቶ፡ ወደ ግልጽ ፍልሚያ ማሸጋገሩን ያመላክታል።
ይህ ለሃገራችን እጅግ አሳሳቢ ችግር ነው። በሕወሃቶች መንግሥታዊ ብቁነት ዕጦትና ዘራፊነታችው የሃገሪቱ ኤኮኖሚ ነፍስ ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ላይ በሚገኝበት ሁኔታ፡ይህንን እያንዳንዱ ዜጋ በጥሞና እየተከታተለ፣ በግሉም ሆነ በሚያመችው መንገድ ኢትዮጵያ ቀጣይዋ ደቡብ ሱዳን እንዳትሆን ለመከላከል እንዲወስን የሚያስገድድ ሁኔታ ፊታችን ተደቅኗል።
ከእጅ ከወጣ በኋላ፣ ለምን ይህ ሁኔታ የሚለውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትረ ሥልጣን መጨበጥ ዋዜማ ጀምሮ የነበረውንና ዛሬም በየአካባቢው የሚታየውን ደም መፋሰስ ጭምር በማቀነባበር ያለውን በማያያዝ ታሪክ ጸሐፊዎች ስለሥልጣን አስካሪነት የሕወሃትን ሰዎች በምሣሌነት ቢያነሷችው የሚከፋ ወይንም የሚገረም ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብሎ መገመት አስቸጋሪ ይሆናል!
ለምን ቢባል፣ሕወሃት በኢትዮጵያ ላይ ከፈላጭ ቆራጭነቱ የሚያፋታው ሁኔታ በሕዝብ ትግል በመፈጠሩና ይህንን ላለመቀበል — በፈረደበት የትግራይ ሕዝብ ስም እየማለ — “ህወሓት እና የትግራይን ህዝብ ለማዳከም እና ለመምታት በተለያዩ መንገዶች ፀረ ትግራይ ህዝብ እና ፀረ ህወሓት እንቅስቃሴ የሚያድርጉ የውስጥም የውጭም ሀይሎች ህዝቡ አምርሮ እንዲታግላቸው የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል” በማለት የጦር ክተቱን አውጇል።
የትግራይ ሕዝብ ታሪካዊ እናት ሃገሩ በጥቂቶች ቀቢጸ ተስፋ እንድትፈርስ፡አጥፊዎቹን ይሰማቸዋል፤ ይቀበላቸዋል የሚል ቅንጣት ሥጋት የለኝም! ሕወሃት የፈጸመባቸው ጭፍጨፋ ሳያንስ የትግራይ ሕዝብ የዜጎች ደም በከንቱ እንዲፈስ ተባባሪ አይሆንም!
የመንግሥት ምላሽ ውስጥ መጀመሪያ ዐይኔን የያዙትና ይህ መግለጫ ለምን እንደተሰጠ ብርሃን የሠጡኝ የሚከተሉት ዋናዎቹ ናቸው፦
“[በያካባቢው] የተፈጠረው ግጭት በምንም መሥፈርት ህብረተሰቡን የማይወክልና የተጀመረው የለውጥ ሂደት ባልተዋጠላቸው አካላት ጠንሳሽነት እየተመራ እንደሆነ ከወዲሁ መገንዘብ ይቻላል”!
“በዚህም ዓለምን ያስደመመ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት በማሰመዝገብ ላይ እንገኛለን ያለው መግለጫው፥ ይህም አገራዊ ጥቅማችንን ከማስጠበቅ አልፎ ቀጠናዊ ትስስር በመፍጠር ረገድ ያጋጠሙንን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በመቅረፍ የህዝቦቻችንን የተከማመሩ ችግሮች ለመፍታት መንግሥት ሌት ተቀን እየተጋ ባለበት በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች ጊዜያዊ ግጭቶች ሲከሰቱ እየተስተዋለ ነው”!
“በመንግሥት የለውጥ መሪነት ከቀውስ ለመውጣት የተጀመረው ጥረት እየሰመረ፣ ነፍጥ አንስተው ሲፋለሙ የነበሩ ወገኖቻችን ሳይቀሩ የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለአገር ግንባታ መሰለፍ በጀመሩበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት የግል ጥቅምን ታሳቢ አድርገው ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚያደርጉትን ሩጫ መግታት ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ወቅታዊ ተግባር ነው”!
በአጭሩ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለ27 ዓመታት እየረገጡ፡ እየዘረፉና እየገደሉ የከረሙት የሕወሃት ነፍሰ ገዳይ ዘራፊዎች፡ የኢሕአዴግን ውሳኔዎች መቃወቻውና በተለይም የቅዋሚያዎቻቸው ምክንያቶች ሠንካላ ከዙፋናቸው ላለመውረድ የሚያደርጉትን ጥረት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳዩ ናቸው!
“አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን አስመልክቶ የኢፌዴሪ መንግስት መግለጫ አውጥቷል።
ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ እና አገራዊ ድባብ ጠብቆ ማስቀጠል የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት መሆን አለበት ብሏል::
በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ እየሰፈነ ያለው ሰላምና መረጋጋት ብሎም እየታየ ያለው አገራዊ መግባባትና የህዝቦች አንድነት የአገራችንን ተሰሚነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት በአፍሪካ ደረጃ ብሎም በዓለም አቀፍ መድረኮች ውጤት እያስገኘ ያለ ስኬት ነው ብሏል መግለጫው።
በዚህም ሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን የምንገኝበትን የአፍሪካ ቀንድ እና የአካባቢውን ወቅታዊ ሁኔታ ከመሰረቱ የሚለውጥ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናችን ይታወቃል።
በዚህም ዓለምን ያስደመመ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት በማሰመዝገብ ላይ እንገኛለን ያለው መግለጫው፥ ይህም አገራዊ ጥቅማችንን ከማስጠበቅ አልፎ ቀጠናዊ ትስስር በመፍጠር ረገድ ያጋጠሙንን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በመቅረፍ የህዝቦቻችንን የተከማመሩ ችግሮች ለመፍታት መንግሥት ሌት ተቀን እየተጋ ባለበት በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች ጊዜያዊ ግጭቶች ሲከሰቱ እየተስተዋለ ነው ብሏል።
አካባቢያዊ ወሰንና ሌሎች መሰል ምክንያቶችን መነሻ በማድረግ ለዘመናት አብሮ በኖረው ህዝቦች መካከል ጥርጣሬን የሚፈጥሩ እና ለግጭት የሚያነሳሱ ሴራዎች መስተዋላቸውን አስታውቋል።
የተፈጠረው ግጭት በምንም መሥፈርት ህብረተሰቡን የማይወክልና የተጀመረው የለውጥ ሂደት ባልተዋጠላቸው አካላት ጠንሳሽነት እየተመራ እንደሆነ ከወዲሁ መገንዘብ ይቻላል ነው ያለው።
ስለሆነም መንግሥት በግጭቱ ምክንያት ለደረሰው ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ በማለት፥ ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቷል።
በድርጊቱ የተሳተፉትን አካላት መርምሮ አስተማሪ እርምጃ እንደሚወስድም አረጋግጧል።
ይህን መሰል ጥፋትና ግጭት ያቀነባበሩት እና ሁከቱን ያባበሱት አካላት ዓላማ አሁን በአገራችን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ማወክ፣ መንግሥት እየገነባው ያለውን አገራዊ አንድነት መናድና በአጠቃላይ አገራችን የጀመረችውን ውጤታማና ፈጣን የሪፎርም እንቅስቃሴ ማደናቀፍ መሆኑ አያጠያይቅም ብሏል መንግስት በመግለጫው።
በመሆኑም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አምርሮ ሊታገለው የሚገባ አደገኛ አዝማሚያ እና ተግባር መሆኑን ተገንዝቦ በጽናት ሊታገልና ሰላሙን መጠበቅ ይገባዋል ብሏል።
በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በክፉውም ይሁን በደግ አብረው በኖሩ ህዝቦቻችን መካከል ግጭት ሊፈጠር አይችልም ያለው መግጫው፥ ይህ በረጅሙ የታሪክ ጉዟችን የተረጋገጠ ሃቅ
ከመሆኑም ባሻገር የህዝቦች ፍላጎት ምንግዜም ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና እንጅ ብጥብጥና ውድመትአይደለም።
በመንግሥት የለውጥ መሪነት ከቀውስ ለመውጣት የተጀመረው ጥረት እየሰመረ፣ ነፍጥ አንስተው ሲፋለሙ የነበሩ ወገኖቻችን ሳይቀሩ የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለአገር ግንባታ መሰለፍ በጀመሩበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት የግል ጥቅምን ታሳቢ አድርገው ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚያደርጉትን ሩጫ መግታት ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ወቅታዊ ተግባር ነው ብሏል።
በመሆኑም መላው ህዝባችን ለዘመናት ሲንከባከባቸው የኖሩትን የሰላም፣ የአብሮነት፣ የመከባበርና የመረዳዳት እትዮጵያውያን እሴቶች በጥቂቶች ሴራ እንዳይሸረሸሩ ነቅተን እየጠበቅን በአገራችን ዘላቂ ሰላም፣ አስተማማኝ ዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ ልማትና ብልጽግና እንድሰፍንና የተጀመረው አገራዊ ትግል ለውጤት ይበቃ ዘንድ የጥፋት ሃይሎችን ዕኩይ ተግባር ነቅተን እናምክን የሚል ጥሪውን መንግስት በመግለጫው አስተላልፏል።”