በኢትዮጵያ እየመጡ ያሉ ለውጦችን ለማደናቀፍ እየተሰሩ ያሉ ሴራዎችን የሚመረምሩ ኮሚቴዎች ሥራ ጀመሩ!

28 Jun

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

እየመጡ ያሉ ለውጦችን ለማደናቀፍ እየተሰሩ የሚገኙ ሴራዎችን የሚመረምሩ ኮሚቴዎች ተቋቋሙ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው፤ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ እውቅና ለመስጠት፣ አገራዊ አንድነትን ለመገንባትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን ለመደገፍ በወጣው ህዝብ ላይ ቦንብ በመወርወር ሂደቱ እንዲስተጓጎል ተደርጓል፡፡

ሰላማዊ ሰልፉን ለማደናቀፍ ቦንብ ከመወርወር ጀምሮ ሂደቱ እንዲስተጓጎል  የተደረገ መሆኑን ያስታወሰው መግለጫው፤ በተጨማሪም የኤሌትሪክ ሃይልና የቴሌኮም ኔትወርክ ማጥፋት፣ በተደራጀ አኳኋን የኢኮኖሚ አሻጥር በመስራት የኑሮ ውድነትን እንዲባባስ እና የተለያዩ ህዝባዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የተቋቋሙ ተቋማት አስፈላጊውን አገልግሎት እንዳይሰጡ እየተደረገ መሆኑን ለማረጋገጥ መቻሉንም ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል፡፡

እንዚህን ህገወጥ ተግባራት አጣርቶ ለህግ የሚያቀርብ ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑን ነው ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

ለተልዕኮው ስኬታማነት መላው ሰላም ወዳድ ህዝብ ከኮሚቴው ጎን በመቆም ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ያቀረበው መግለጫው፤ አጥፊዎችን ለፍርድ ለማቅረብ እንዲተባበር ጠይቋል፡፡

ኮሚቴው የደርሰበትን ውጤት ለህዝብ ይፋ እንደሚያደረግም አሳውቋል፡፡

አዲስ አበባ ሰኔ 21/2010/ኢዜአ/

%d bloggers like this: