የእኩልነት ዘመን ጅምር!                 ብሔራዊ ድኅንነት መ/ቤትን ከፖለቲካ ወገንተኝነትና ዘረኝነት የማጽዳት እርምጃ!

17 Jul

Posted byThe Ethiopia Observatory (TEO)

“ተቋሙ የሚፈራ ሳይሆን የሚወደድና የሚከበር እንዲሆን ይሰራል ያሉት ጀነራሉ ለዚህም አመራሮችና ባለሙያዎች ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ እንዲሠሩ አሳስበዋል።”

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆኑ ብሄራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሠራተኞች ከፓርቲ አባልነት መውጣት አልያም ተቋሙን መልቀቅ እንዳለባቸው የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ጀነራል አደም መሀመድ ገለፁ።

ዳይሬክተር ጄኔራል አደም መሃመድ (ፋና ፎቶ)

ብሄራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳና ለሕዝብ የቆመ እንዲሆን የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ተቋሙን ከፓለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ከማድረግ ባሻገር ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሰራበትና የሚሳተፍበት ይደረጋል ብለዋል።

ጀነራል አደም ይህን ያሉት ለሶስት ቀናት የሚቆይ አዲሱን አመራር የሚያስተዋውቅና የሪፎርም ስራዎች ላይ ውይይት የሚደረግበት መድረክ በአዲስ አበባ ሲጀመር ነው።

በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር በሀገሪቱ ፈጣን ለውጥና ፈጣን እድገት እየተመዘገበ በመሆኑ ከዚሁ ጋር የሚሄድ ተቋም መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

መንግስት በተቋሙ ላይ አዲስ ሀገራዊ ሃላፊነት በመጠላሉ አለም አቀፋዊ የመረጃ ትስስርና ፍሰት ጋር እራሱን አዋህዶ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

ሀገሪቱ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ፣ በፈጣን የፓለቲካ ለውጥና የሁኔታዎች መለዋወጥ ላይ ትገኛለች ያሉት ጀነራሉ ተቋሙ ከለውጥ ጋር የሚራመድ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።

የተቋሙ ሰራተኞችም መብታቸውን የሚረዱና አለም አቀፍ ጉዳዮችን በመረዳት የሚተነትኑ መሆን እንዳለባቸው በመግለፅ ሕዝብን ከውጭና ከውስጥ አደጋ ለመከላከል አቅም ማሳደግና ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በአሁን ወቅት ከመንግስት በተሰጠው አቅጣጫና በሕዝብ ጥያቄ መሰረት ተቋሙን የሕዝብና የሃገር ማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም ተቋሙ ኢትዮጵያዊነትን ከትውልድ ወደ ትውልድ ማሻገር ዋና ተግባሩ እንዲሆን ይደረጋል ሲሉ ጀነራል አደም መሀመድ አስታውቀዋል።

ተቋሙ በአገልግሎት ማሻሻያው በተሰጠው ሀላፊነትና ስልጣን መሰረትና የፖለቲካ ወገንተኝነት ሳይኖረው ኢትዮጵያውያንን እኩል ማገልገል እንዲችል እየተሰራ ነው።

ህብረተሰቡም መረጃዎች በሚያቃብልበት የተቋሙ ባለሙያዎች ስጋት ሳይሆን አለኝታ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ከባድና ትልልቅ ግዳጆችን ለመወጣትና ለመስራት ተቋሙ አቅሙን ለማሳደግ የአደረጃጀት ማስተካከያ እንደሚያደርግም ጀነራል አደም አስታውቀዋል።

ተቋሙ የሚፈራ ሳይሆን የሚወደድና የሚከበር እንዲሆን ይሰራል ያሉት ጀነራሉ ለዚህም አመራሮችና ባለሙያዎች ህግና ስርዓትን ተከትሎ እንዲሰሩ አሳስበዋል።

 

%d bloggers like this: