ሰመጉ በኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች የፀጥታ አካላት የመብት ጥሰቶችን መፈፀማቸውን በሪፖርቱ ገለፀ

1 Aug

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

ቢ.ቢ.ሲ. አማርኛ

የሰላሳ ዓመቷ ሩሚያ ሱሌ መስከረም 01 ቀን 2010 ዓ.ም ከጂግጂጋ ተፈናቅላ የመጣች ሲሆን “ራበን ዳቦ ስጡን” የሚል ጥያቄ በማንሳቷ በመከላከያ ሰራዊት አባላት በጥይት ተመትታ ህይወቷ ማለፉን የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ዛሬ ያወጣው ሪፖርት ያትታል።

ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች የተፈፀሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን ከጥር 29 2009 ዓ.ም እስከ ጥር 2010 ዓ.ም ያለውን ጊዜ ይሸፍናል።

በኢትዮጵያ ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በባለፉት ሁለት ዓመታት የብዙዎችን ህይወት ቀጥፏል፣ ንብረት ወድሟል እንዲሁም የሀገሪቷን ህልውናም አደጋ ላይ ጥለውታል።

በተለይም በኦሮሞና በኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔር ተወላጆች መካከል ያለው ግጭት እጅጉን ተባብሶ እና መልኩን ቀይሮ ወደ ጥቃት በመቀየር አስከፊና አስፈሪ ደረጃ ላይ ደርሷል።

•    በርካታ ሰዎች ከሞያሌ በመሸሽ ወደ ኬንያ ገብተዋል

•    በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ድንበር ግጭት የገዳ ስርዓት መፍትሔ ለምን አላመጣም?

ከግጭቱም ጋር በተያያዘ ሰላምን ሊያስከብሩ የተሰማሩ የመከላከያ ሰራዊት፣ በልዩ ፖሊስና የፀጥታ አካላት በሰብዓዊ መብት ጥሰት በቀጥታ ተሳታፊ እንደሆኑም ሪፖርቱ ያትታል።

ብዙዎችን በመግደል፣ አስገድዶ በመድፈር፣ በዝርፊያና በማሰቃያት ተሳታፊ ናቸው በማለትም ይወነጅላቸዋል። ደብዛ የማጥፋት ወንጀሎች በሁለቱም ክልሎች መፈፀማቸውን ጠቁሟል

በሁለቱ ክልሎች በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶችም እንደተደፈሩ ሪፖርቱ አስቀምጧል።

ከነዚሀም ውስጥ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ዓመት ተማሪ የነበረች አንዲት ሴት በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ለሶስት ከመደፈር በተጨማሪ፣ በዱላ እንደተደበደበችና በጩቤ እንደተወጋች ሪፖርቱ ጨምሮ ያትታል።

የደረሱት የሰብዓዊ መብት ጥቃቶች ለመስማት የሚዘገንኑ ሲሆን ከዚህም ውስጥ በአምስት ወታደሮች የተደፈረችና ለ28 ቀናትም በፊቅ ተራራ ላይ የታሰሩ ሴት ይገኙበታል። በስለት ታርደው የተገደሉ፣ በእሳት ተቃጥለው የሞቱና ከዚሀም በተጨማሪ የሶስት ዓመት ህፃን ልጅም እንደተገደለም ሪፖርቱ ጠቅሷል።

ተቋሙ በልዩ መግለጫው ላይ ወደ 30 በሚጠጉ የሁለቱ ክልል አጎራባች ወረዳዎች በተደረገ ማጣራት ከ500 በላይ ዜጎች መገደላቸውንና በመቶዎች የሚቆጠሩ ለአካል ጉዳት እንደተዳረጉ አስታውቋል።

በዚሀም ምክንያት በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳት ላይ ያሉ ሲሆን የሰመጉ ባለሙያዎች በሚያነጋግሯቸው ወቅት በተደጋጋሚ ራሳቸውን እየሳቱ ይወድቁ ነበርም ይላል።

ከማንነት፣ ከአስተዳደርና ከድንበር ይገባኛል ጥያቄ ጋር በተያያዘ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል በሚገኙ በተነሱ ግጭቶች ምክንያት ከሁለቱም ክልሎች የተፈናቀሉት ዜጎች ቁጥር ከአንድ ሚሊየን በላይ እንደሚበልጥም ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እና OCHA3 በጋራ ያወጡት ሪፖርት ያሳያል።

የችግሩን አሳሳቢነትም የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ቢንያም አባተ ይናገራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ቃሎች የተገቡ ቢሆኑም ወደ ተግባር ሊቀየሩ እንደሚገባም ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።

በጥቃቱና በግጭቱ እጃቸው ያለበት አካላትን ተጠያቂ ከማድረግ ጀምሮ በቂ ትኩረትና ዘለቄታዊ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ አቶ ቢንያም እንደ መፍትሔ የሚያስቀምጡት ነው።

ሰመጉ የተጎጂዎች ቁጥርና ጉዳት መጠኖችን በዘረዘረበት ባለ 55 ገፅ ልዩ ሪፖርቱ ፤ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፍትሄ እንዲሰጣቸው ፣ለወደፊቱም እንዳይደገሙ የመከላከል ርምጃ እንዲወሰድ ፣ጉዳት የደረሰባቸው ካሳ እንዲከፈላቸውና ተጠያቂዎችም ለህግ እንዲቀርቡ ጥሪ አቅርቧል።

%d bloggers like this: