በመሬት ነክ ጉዳዮች በጊዜያዊነት አገልግሎት መሥጠት ማቆሙን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ

15 Aug

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከመሬት አስተዳደር ጋር የተገናኙ አገልግሎቶች ለጊዜው መቆማቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ሦስት የሚሆኑ አገልግሎቶችን ነው በጊዜያዊነት ማስተናገድ ያቆመው፡፡
ከነዚህም መካከል የግል ኢንዱስትሪ አልሚዎች የመሬት ጥያቄ አንዱ ነው ተብሏል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ በይዞታ አስተዳደር የሽግግር ግዜ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል የሠነድ አልባና አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድ የተያዙ ይዞታዎች መስተንግዶ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ሦስተኛው መሬት ያልተረከቡ የመኖሪያ ቤት ማኅበራት መስተንግዶ አገልግሎቶች የቅድመ ማጣራት ሥራ እስኪጠናቀቅ ድረስ የማያስተናግድ መሆኑን አሳውቋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ አመራሮችን በአዲስ መልክ አዋቅሮ የሪፎርም ሥራውን እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ለማድርስ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

በዚህም መሰረት የመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች የሪፎርም አካል እንዲሆን አጽንዖት የተሰጠው ጉዳይ ሲሆን በከተማው የሚገኘውን መሬት ኦዲት የማድረግሥራ አንዱ መሆኑንም የከንቲባው ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡

በጊዜያዊነት አገልግሎት የተቋረጠባቸው የመሬት ነክ ጉዳዮች በአጭር ግዜ ውስጥ የቅድመ ዝግጅትሥራቸው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ተብሏል፡፡

%d bloggers like this: