በጅግጅጋ የሶማሊያ ባንዲራና መገንጠልን የሚቀሰቅሱ ባነሮች በብዛት እየታተሙ ነው ተባለ! ኮማንድ ፖስቱ ማስጠንቀቂያ ሰጠ!

15 Aug

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

(ኢሳት ዜና ) ነሐሴ 08 ቀን 2010 ዓ/ም  በሥፍራው ያሉ የኢሳት ወኪሎች ባደረሱን መረጃ መሠረት፣ ቀደም ሲል አብዲ ኢሌ ያደራጃቸው ሄጎ እተባሉ የሚጠሩት ቡድኖች፤ ትናንትና በጅግጅጋ ከተማ የመንግሥት መኪኖችን ጭምር በመጠቀምና የኦብነግን ባንዲራ በማውለብለብ ብጥብጥ ለመፍጠር ሞክረዋል።

እነዚሁ ቡድኖች ክልሉን ለማረጋጋት ከተሰማራው የመከላከያ ሠራዊት ጋር ግጭት መፍጠራቸውን ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊት በመሣሪያ ኃይል የበተኗቸው ሲሆን፣ በተኩስ ልውውጡ በፖሊስ መኪና ላይ የኦብነግ ባንዲራ ሰቅሎ ሲያሽከረክር የነበረ የሂጎ አባል ቆስሏል። የሶማሌ ልዩ ፖሊስ ሰሞኑን በሐረርጌ በከፈቱት ድንገተኛ ጥቃት 41 ሰዎች መገደላቸው ይታወቃል።

ምንጮች እንደሚሉት ከሂጎዎ ጋር የተፋጠጠው መከላከያ ብቻ አይደለም። ህዝቡም የቡድኑ አባላት እየፈጸሙት ያለውን ህገወጥ ተግባር ለመመከት ባለ በሌለ አቅሙ እየታገላቸው ነው። በትናንትናው ዕለት ሕዝቡ ከሂጎዎች ጥቃት ድንጋይ በመወርወር ራሱን ሲከላከል መከላከያ ሰራዊት ወደቦታው ደርሶ ግጭቱን ቢያበርድም፣ ሂጎዎቹ በፍጥነት በመኪና ከአካባቢው ተሰውረዋል።

አዲስ የተቋቋመው የክልሉ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ጄነራል ሀሰን፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ ራሱን ሂጎ ከሚባሉት በመለዬትና የቡድኑን አባልሥርዓት አልበኝነት በማውገዝ የለውጡን ሂደት እንዲያግዝ አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት ወደ አምስት በሚደርሱ እና በአብዲ ኢሌ ደጋፊዎች የሚመሩ ማተሚያ ቤቶች “ኦብነግን ለመቀበል” በሚል የሶማሊያ ሪፐብሊክ ባንዲራ እየታተመ ነው። ይሕ እየተደረገ ያለው፤ የልዩ ፖሊስ አዛዥ አብዱራህማን ወንድም እና የሂጎ መሪ በሆነው በአብዱላሂ ትዕዛዝ ነው ይላሉ ምንጮቹ። ከባንዲራውም በተጨማሪ መገንጠልን የሚቀሰቅሱ እጅግ በርካታ ባነሮች እየታተሙ መሆናቸው ተመልክቷል።

ጉዳዩ ያስቆጣቸው የኮማንድ ፖስቱ ኃላፊዎች ኦብነግ ይህን ስርዓት አልበኝነት ያውግዝ ሲሉ አሣስበዋል። የኮማንድ ፖስቱ ኃላፊዎች አክለውም “እንዲህ ያለውን ሁኔታ አንታገሰውም” በማለት አስጠንቅቀዋል።

የኮማንድ ፖስቱ ኃላፊዎች ከህዝቡ ጋር ባደረጉት ውይይትም ፣ በአብዲ ኢሌ ደጋፊዎች እየተሰራጨ ያለውን ይህን ፕሮፖጋንዳ በጋራ በማውገዝ የተገኘውን ሰላም እና የለውጥ ተስፋ እንዳይቀለበስ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ቆመው እንደሚታገሉ አረጋግጠዋል።

የሃገር ሽማግሌዎችና የክልሉ ምሁራንም በግጭቱ የተጎዱትን መልሶ ለማቋቋም እየሠሩ ሲሆን የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያኖችም ተመልሰው እንዲሰሩ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።

%d bloggers like this: