ከ1983 ዓ.ም ወዲህ በተለያየ ምክንያት ከሠራዊቱ የተሰናበቱ አባላት የጡረታ መብት ይከበርላቸዋል ተባለ!

30 Aug

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና የዘመቻ መምሪያ ሃላፊ ጀነራል ብርሀኑ ጁላ (ፋና ፎቶ)

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 24፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በተለያየ ምክንያት ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ከሠራዊት የተሰናበቱ አባላት የጡረታ መብት እንደሚከበርላቸው የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹምና የዘመቻ መምሪያ ሃላፊ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ አስታወቁ።

የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹምና የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ እንዳሉት፥ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ማእረጋቸው ተገፎ ያለጡረታ ለተሰናበቱት ጀነራል መኮንኖች ማእረጋቸው ተመልሶ ጡረታቸው እንዲከበር ተደርጓል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ መነሻ በማድረግ በእነርሱ ብቻ ሳይቆም በተለያየ ሰበብ አስባብ ጡረታቸው ሳይከበር የወጡ በአገልግሎት የነበሩ የሠራዊት አባላት በሙሉ ዶክመንታቸው ተፈልጎ ከተለዩ በኋላ መከላከያ ሚኒስቴር ውሳኔ ሰጥቶ ጡረታቸው እንዲከበር እየተሰራ ነው ነው ብለዋል።

እንደ ጀነራል ብርሃኑ ማብራሪያ፥ በአገልግሎት ጣሪያቸው ለጡረታ የበቁት የቀድሞው ሠራዊት አባላት በሙሉ ሕጋዊ የጡረታ መብታቸው ተከብሯል።

አሁን እየተሠራ ያለው ግን ባለፉት 27 ዓመታት በአገልግሎት ላይ የነበሩትን በዲስፕሊንና በተለያዩ ሰበብ አስባቦች የጡረታ መብታቸው ሳይከበር የቀሩትን ነው፤ ይህም ግለ ማሕደራቸው ተፈልጎ በመሠራት ላይ ይገኛል ብለዋል ጄነራል ብርሃኑ።

ከተጠቀሰው ውጪ የጡረታ መብት ጥያቄዎች እየቀረቡ መሆናቸውና ከአሰራር ውጪ እንደማይስተናገዱ ተመልክቷል።

%d bloggers like this: