የበጎ አድራጎትና ሲቪክ ማኅበራት አዋጅ ማሻሻያ ውይይት

31 Aug

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO) 

 

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 25፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሥራ ላይ ባለው የበጎ አድራጎትና ሲቪክ ማኅበራት አዋጅ ማሻሻያ ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው።
በአዋጁ ዙርያ እስከ መስከረም 10 2011 ድረስ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚካሄደው ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሯል።
በውይይቱ በሥራ ላይ ያለውን የበጎ አድራጎትና ሲቪክ ማኅበራት አዋጅ ማሻሻል ያስፈላገው አዋጁ ገዳቢ በመሆኑ ነው ተብሏል።
አዋጁን ለማሻሻል የተቋቋመው ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ደበበ ኅይለገብርዔል፥ በስራ ላይ ያለው አዋጅ ነፃነትን ከመፍቀድ ይልቅ ጥብቅ ቁጥጥር ላይ የሚያተኩርና ፍቃድ ከመስጠት ይልቅ ገዳቢ በመሆኑ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙት የሰቪክ ማኅበራትን ዝቅተኛ እንዳደረገው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልፀዋል።
ኮሚቴው ባካሄደው ጥናት ወደ 40 የሚጠጉ ችግሮች እንደተለዩም አስታውቀዋል።
ማሻሻያው ሲቪክ ማኅበራት አዋጅ የመደራጀት መብት የሚያስከብር እንደሆነም ተነግሯል።
የረቂቅ አዋጁ ዋና ይዘትም ማንኛውም የሲቪክ ማኅበር ህጋዊ ከሆነ አካል ያለገደብ ገንዘብ ማግኘት እንዲችልና በማንኛው ህጋዊ ስራ ላይ ተሰማርተው የሚያገኙትን ገንዘብ ለማህበራዊ ልማት እንዲያውሉ የሚፈቅድ ነው።
አገልግሎት ላይ ባለው አዋጅ ሲቪክ ማኅበራት 90 በመቶ ገቢያቸው ከሀገር ውስጥና 10 በመቶ ብቻ ከውጭ ማግኘት እንዲችሉ ገደብ ያስቀመጠ ነበር።
ከዚህ ባለፈ 70 በመቶ ገቢያቸውን ለልማትና 30 በመቶውን ደግሞ ለአስተዳደራዊ ወጪ እንዲያውሉ ገደብ ተጥሎባቸው የነበረ ቢሆንም በማሻሻያው እነዚህ ገደቦች ሙሉ በሙሉ እንዲነሱ ተደርጓል።
እንዲሁም ይህ ማሻሻያ ከፍቃድና እድሳት ጋር ተያይዘው ይነሱ የነበሩ ችግሮችንም ለመፍታት ያስችላል ተብሏል።
የሚቋቋሙት ማኅበራት ያሉበትን ደረጃ በሁለት ዓመቱ በመገምገም ኅልውናቸውን የማራጋገጥ ስራ በማከናወን ፍቃድ እንደሚሰጥና መዘጋት ካለባቸው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲዘጉ ይደረጋል ነው የተባለው።
በማሻሻው የሀገር ውስጥና የውጭ የበጎ አድራጎትና ሲቪክ ማኅበራት ምዝገባ ቀላል ይደረጋል የተባለ ሲሆን፥ ለአለም አቀፍ ተቋመት ልዩ ትኩረት እንደተሰጠም ተገልጿል።
አለም አቀፍ የበጎ አድራጎትና የሲቪክ ማኅበራት ከሀገር ውስጥ ማህበራት ጋር በጋር መስራት እንዲችሉ ትኩረት ይደረጋል ተብሏል።
ማሻሻያው የበጎ አድራጎትና ሲቪክ ማኅበራት ከማንኛውም አካል በህጋዊ መንገድ የሚያገኙትን ገንዘብ መጠቀም እንዲችሉ የሚፈቅደ ነው።
በተጨማሪም የሲቪክ ማኅበራቱ የገንዘብ ዝውውር በባንክ ብቻ እንዲሆንና 100 ሺህ ብር ወጪ በውጭ ኦዲት እንዲደረግ ረቂቅ አዋጁ ያስገድዳል።
%d bloggers like this: