ታማኝ በየነ ኢትዮጵያ ሲገባ በሕዝቡ የተደረገለት ደማቅ አቀባበል ልቤን በደስታ ሲሞላው፣ እንደዜጋ የአብን ማስጠንቀቂያ አሳዝኖኛል!

2 Sep

በከፍያለው ገብረመድኅን The Ethiopia Observatory (TEO)

ታማኝ በየነ ከአሜሪካ ወደ ሃገሩ ሲመለስ፣ በሚዲያ ውጭ ያሉ ለሎች ዜጎች እንደተከታተሉ ሁሉ፣ እኔም በደስታ በሩቁ ሁኔታውን፡ ማለትም ቦሌ አየር ማረፊያ፣ መገዱም ላይና የብሔራዊ ቲያትሩን ሥነ ሥርዓት በአድናቆት ተከታትያለሁ።

ለዓመታት ለሃገሩና ለወገኖቹ መከበር ያደረገውን አስተዋጽዖ ከፍተኛ ዕውቅና በመሥጠት የኢትዮጵያ ሕዝብ (የአዲስ አበባ ሕዝብ) የሞቀ አቀባባል ሲያደርግለት — የሚገባው ስው ነውና— ልቤ ፍንድቅ ብሎለታል። የብዙዎች ወገኖቻችንም ልብ  እንዲሁ በደስታ ተሞልቷል ብዪ አምናለሁ!

ይህ በአንድ በኩል የሚያሳየው፣ በለታዊ ሕይወቱ ሕዝባችን ምን ያህል እንደተሠቃየና በሃገሩም ላይ የደረስባትን ጉስቁልና እንደራሱ ቁስል መውሰዱንና ከዚያ ሥነ አዕምሮአዊ ጫና ራሱን ለማላቀቅ የሚያደርገው ግላዊ ትግልና ጥረት አካል ሆኖ ይታየኛል!

አለበለዚያ እኮ ቅዳሜ በጥዋት ቦሌ ከመሄድ ይልቅ፡ ታማኝ ወር ያህል ኢትዮጵያ እንደሚቆይ ቀደም ብሎ በሚዲያ ተናግሯል። በሚሊኔየም አዳራሽም ፕሮግራም ቅዳሜ አለውና  ሕዝቡ ሊያገኘውና “እንኳን ለሃገርህ አበቃህ! በሠራኸው ሥራ አክብራሃለሁ!” ሊል የሚችልበት ቀዳዳዎች ብዙ ናቸው!

ነገር ግን ሕዝቡ የመረጠው፡ታማኝን እንደሙሽራ ወይንም እንደ አንድ ባለድል ተመላሽ መሪ ነው መቀበል የፈለገው!  ስለተሳካለት እጅግ ተደስቻለሁ!

በተጨማሪም፣ መታወስ የሚገባው ሕዝባችን ውለታ አክባሪ በመሆኑ፡ ያንን ሳይውል ሳያድር ለመክፈል የነበረውን ጕጕት ነው ያየሁት! ጥቂቶችም ሊቀበለው የወጣው ሕዝብ በዛ ብለው መረር ያለ ሂሣብ መሰል ነገር ውስጥ የገቡም መኖራቸውን ሰምቻለሁ። በፈጠራችሁ አምላክ! የዚህ ነገር መብዛትና ማነስ በምንደነው የሚለካው? ሕዝቡ በመሰለው ከበሬታውን ገልጿል! እሰይ ነው ያልኩት፤ ቅጥል ያድርጋችሁ!

አቀባበሉን የሚቃወም ግለሰብ /ቡድን አለን?

ለታማኝ የተሠጠው ከበሬታ ሁላችንንም ሊያስደስተን እንጂ፡ ሊያስከፋው የሚችል ግለሰብ ወይንም ቡድን ይኖራል ብሎ መገመት — በተለይም አማራ ነኝ ከሚል ወገን — ባይሆን ኖሮ አይደረግም ብዬ እከራከር ነበር።

ከሆነ በኋላ ግን የሃገራችን ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ሁላችንም ልንገነዘብና እንደ ሃገር ብዙ ሣይኮሎጂስቶችና ሣይኮአናሊስቶች ልናፈራና የአዕሞሮ ጤንነታችንን በቅርብ ልንከታተል እንደሚያስፈልገን ይሰማኛል!

ለምንድነው እንዲህ የምለው? ዴሞክራሲ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት መንገድ ጀምሯል እየተባለ ስለሆነ፡ ለፖለቲካ ሥልጣን ፉክክር ለመጣ ነው ከሚል ጋር  የተያያዘ አይሰማችሁም?

ዛሬ ሁሉም— ጎረምሣው፡ ወጣቱም ሽማግሌውም— በማናቸውም መንገድ ሸልቅቆ ሥልጣን እጁ ለማስገባት —  ድርጅቱን ዘርግቶ — ሙከራውና ፍላጎቱ ለመኖሩ ምልክቶች ይጠቁማሉ። አንዱ ግራ አጋቢውና ከአማራም ባህል ጋር የሚይሄደው ግን በአማራ ምሁር(ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ) ገና ታማኝ ከአውሮፕላን ሳይወርድ፣ በእንኳን ደህና መጣህ ስም የተዘጋጀለት ዘሐበሻ እንዳስቀመጠው “ማስጠንቀቂያ” ነው!

እገሌ መጣ/ ሊመጣ ነው ሲባል፣ ይህ  ለታማኝ ዶክተሩ የጻፈው ማስጠንቀቂያ ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ውጭ ነው! ምሁሩ ወዳጅህ በመሆኔ እንተም እንደሌሎቹ “እንድታፍር አልፈልግም” ብሎ ሲያበቃ ማስጠንቀቂያ መሥጠት? አዲስ አበባ ወይንም ባሕር ዳር ተገናኝተው አሁን በአየር ላይ የናኘውን መልዕክት እንደ ወዳጅ በግል ሊያስጭብጥ በቻለ ጨዋነት ነበር!

ይህ ባለመሆኑ ሁኔታውን ይህ ምንድነው ያስመሰለው? 

ያላየሁት ነገር ከሌለ በስተቀር፡ በተለይም ሥጋ ያየ አውሬ ይመስል— ታማኝ ከ22 ዓመታት ስደት በኋላ ወደሃገሩ ለመመለስ ገና አየር ላይ ሆኖ —  ‘እቺን ሥጋ እስቲ ትነካትና’ ወይንም ‘እስቲ ድርሽ ትልና’ በማለት በተፋጠጡ እንስሣት መካከል የሚደረግ የሆድ ግብ ግብ  ላይ አንዱ ወገን የመጀመሪያውን እርምጃ በመውሰዱ የተጀመረ አስመስሎታል!

ለመሆኑ ኢትዮጵያ የማን ብቸኛ ሼር ኩባንያ ሆና ነው እንዲህ የሚባለው? ከዚህ እንደሚታየው ግብ ግቡ ለሃገሪቱ ብቻ ሣይሆን በሃገሪቱም ላይ ይመስላል!

ግለሰቡ ካደረገው ተነስቼ ስደመድም፣ በተለይም አማራ የኢትዮጵያ መሠረት ሆኖ ሳለ፡ ይህ ግለስብ ነገ ሥልጣን የመያዝ ዕድል ቢያገኝ በመላ ሃገሪቷ ወይንም በአማራ መንግሥት መሪነት ከመለስ ዜናዊ የከፋ ፈላጭ ቆራጭ አይሆንምን ብለን ብናስብ ያገርም ይሆን? ብሔራዊ አማራ ንቅናቄስ (ብአን) ሃገሪቱን የራሱ ብቸኛ ኩባንያ አድርጎ ይመለከታልን?

ካልሆነ ለምን ይሆን ለታማኝ ከዚህ የሚከተለው አሣፋሪ ከባሕላችን ያፈነገጠ ትዕዛዝ ተቆርጦ ዘሐበሻ እንዲያሠራጭለት የተደረገው?

“..የአማራን ህዝባችንና ለአገራችን ያደረግከውን አስተዋፅኦ እናከብረዋለን:: እስካገኝህ ግን ይጠቅምሃል ብየ ያመንኩበትን አንድ ወንድማዊ ማሳሰቢያ ልስጥህ:: የአማራን ህዝብ/ወጣት ስለኢትዮጵያዊነት እናስተምረው እንደሚሉት የተሸጡ ግለሰቦች ለማድረግ እንዳትሞክር:: ያን ያደረግህ ጊዜ ይህ የሚወድህና የሚያከብርህ ህዝብ እንዴት በቁጣ እንደሚነሳ ብዙ ያከበርናቸው ሰዎች ላይ ደርሶ አይተነዋል:: እንደነዚህ ሰዎች እንድታፍር አልፈልግም::”

ከላይ በነካካኋቸው ምክንያቶች፣ ሃገሪቷ የነማን ሆነችና ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ የዚህ ዐይነት ማስጠንቀቂያ የሚሠጠው የሚል አላስፈላጊ ጥያቄ በዜጎች ጭንቅላት ቢያጭር አይገርመኝም!

%d bloggers like this: