ጠ/ሚ ዶክተር አብይና ምክትላቸው ከሃገር መከላከያ ከተለያየ ክፍለ ጦር ከተውጣጡ የጦር ሠራዊት አባላትጋር ተወያዩ!

10 Oct

Posted by The EthiopiaObservatory (TEO)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከሃገር መከላከያ የተለያየ ክፍለ ጦር ከተውጣጡ የጦር ሰራዊት አባላት ጋር ተወያይተዋል።

አባላቱ በነበራቸው ቆይታ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄ ማቅረባቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘይኑ ጀማል ለጣቢያችን ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ጀኔራሉ አባላቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን አግኝተው ጥያቄያቸውን በአካል ለማቅረብ ወደ ቤተ መንግስት ማምራታቸውንም ነው የተናገሩት።

በወቅቱም ሰላማዊ ውይይት ማድረጋቸውንና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለአባላቱ በዚህ መልኩ ወደ ቤተ መንግስት መምጣታቸው ስህተት መሆኑን ነግረዋቸው አባላቱም ስህተቱን ተቀብለዋል ነው ያሉት።
ውይይቱ ከተጠናቀቀ በኋላም አባላቱ ፑሺ አፕ እንዲሰሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከታዘዙ በኋላ የእራት ግብዣ እንደተደረገላቸውም ገልጸዋል።

ከዚህ ውጭ ግን ቤተ መንግስት አካባቢ የነበረው ሁኔታ ፍጹም ሰላማዊ መሆኑንም ኮሚሽነር ጀኔራሉ አስረድተዋል።

አባላቱ ከተጣለባቸው ሃገራዊ ሃላፊነት እና ግዳጅ ጋር ተያያዥ ጥያቄዎችን ማንሳታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

በውይይቱ የመከላከያ አባላት እንደዜጋ ጥያቄያቸው ሊደመጥ እና በተግባር መመለስ እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጠቁመዋል።

መንግስት እንደሃገር የጀመረው የማሻሻያ ስራ በመከላከያ ዘርፉም በተመሳሳይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ተጨማሪ ውይይት በሚፈልጉ ጉዳዮች ዙሪያ መድረኮች ይመቻቻሉ ያሉት አቶ ደመቀ፥ ጥያቄዎችም በቀጣይ መንግስት በጀመረው የለውጥ ጉዞ ደረጃ በደረጃ እንደሚፈቱ አረጋግጠዋል። 

የመከላከያ አባለቱም በውይይቱ ለተነሱ የዘርፉ ችግሮች በሰከነ አግባብ እንዲፈታ እና የተጀመረው የለውጥ ጉዞ እንዳይደናቀፍ ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ዝግጁነታቸውን ማረጋገጣቸወን ነው ፅህፈት ቤቱ ያስታወቀው።

 

ተዛማጅ፡

የዐቢይ አስተዳደር የታጠቁ ኃይሎች በአገር ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ እንደማይፈቅድ በድጋሚ አስታወቀ! ለምንስ ፈቀደ ሲጀመር?

 

%d bloggers like this: