አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ በቃሉ ዘለቀ የመልቀቂያ ጥያቄ አቀረቡ!

18 Nov

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሆነው ሲሾሙ አንገራግረው የነበሩት የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትና ከጥቂት ወራት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሆነው የተሾሙት አቶ በቃሉ ዘለቀ፣ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰማ፡፡

አቶ በቃሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሹመት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትነታቸው ተነስተው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሆነው ከተሾሙ አራተኛ ወራቸው ነው፡፡

ነገር ግን አቶ በቃሉ ለአራት ወራት የቆዩበትን የኃላፊነት ቦታ በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን፣ ይህም ጥያቄያቸው አዎንታዊ መልስ ሳያገኝ እንዳልቀረ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በሥራቸው ላይ እንደሆኑ ለማረጋገጥ ቢቻልም፣ በጊዜው ከአገር ውጪ መሆናቸው ታውቋል፡፡

አቶ በቃሉ ቀድሞም ቢሆን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኃላፊነታቸው ተነስተው በሹሙት ወደ ብሔራዊ ባንክ የመዘዋወራቸው ነገር የተመቻቸው እንዳልነበር፣ ለእሳቸው ቅርብ የሆኑ ምንጮች ሲገልጹ ነበር፡፡ ሹመታቸውን የሚገልጸውን ደብዳቤያቸውንም ዘግይተው መውሰዳቸውንም ምንጮች ያስረዳሉ፡፡

በማንገራገርም ቢሆን የተቀበሉትን ይህንን ኃላፊነት ለመልቀቅ ለምን እንዳሰቡ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡ በጉዳዩ ላይ ከብሔራዊ ባንክ አካባቢ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ አቶ በቃሉ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ያላቸውን ፍላጎት የሚያመላክት መልዕክት የባንኩ ሠራተኞች እንዲያውቁት ተደርጓል፡፡በመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ሪፎርም መሠረት ተግባራዊ ከተደረጉ ሥራዎች መካከል አንዱ፣ የተቋማቱን ኃላፊዎች በአዲስ መተካት ነው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥና ምክትል ገዥ ከኃላፊነታቸው ተነስተው ወደ ሌላ ቦታ ሲመደቡ፣ አቶ በቃሉም ቀደም ሲል ምክትል ገዥ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትን ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) እንዲተኩ መሾማቸው ይታወሳል፡፡ የባንኩ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ደግሞ የቀድሞውን ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉን ተክተው ተሹመዋል፡፡

አቶ በቃሉ ለዓመታት በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የነበሩትን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ፣ የቀድሞ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክና የአዋሽ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ባጫ ጊና ተክተው ተሹመዋል፡፡

ይህ በመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ላይ የተደረገው ለውጥ በኢትዮጵያ ልማት ባንክም በተመሳሳይ ተግባራዊ መሆኑ አይዘነጋም፡፡

አቶ በቃሉ ለምን ከብሔራዊ ባንክ ገዥነታቸው በመልቀቅ እንደፈለጉ ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አገር ውስጥ ባለመኖራቸው ባይሳካም፣ ከግል ባንኮች መካከል አንዱን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ጥሪ እንደቀረበላቸው በቅርበት ከሚያውቋቸው የባንክ አመራሮች እየተነገረ ነው፡፡

 

/ሪፖርተር

 

 

 

%d bloggers like this: