በአገሪቷ የወጡ ሕጎች ተግባር ላይ ባለመዋላቸው የሕግ የበላይነትን ለማስከበር አዳጋች ሆኗል-ምሁራን

1 Dec

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

አዲስ አበባ ኅዳር 22/2011 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ያወጣቻቸው ሕጎች ወደ ተግባር ባለመቀየራቸው የሕግ የበላይነትን ማስከበር አዳጋች እንዳደረገው ምሁራን ገለጹ።

ምሁራኑ ቀደም ሲል በነበረው ሁኔታ ለአገራቷ የሚጠበቅባቸውን ያህል ሙያዊ አስተዋጽኦ አለማበርከታቸውንም ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን እንዳሉት ኢትዮጵያ እስካሁን ያወጣቻቸውሕጎች ሁሉንም ያማከለና ለአተገባበርም ምቹ ናቸው።

ይሁንናሕጎቹ በአግባቡ ተግባራዊ ባለመደረጋቸው በተደጋጋሚ ሲጣሱ ብሎም ሲረሱ ይስተዋላል።

ህጎቹን በወረቀት ላይ ከማስፈር ባለፈ በተግባር ላይ ውለው ህያው መሆናቸውን ማሳየት እንደሚያስፈልግም ምሁራኑ ይጠቁማሉ።

የታሪክ ተመራማሪና የሕግ ባለሙያ ዶክተር አልማው ክፍሌ እንደተናገሩት አገሪቷ እንደ አገር የራሷ የሆነ ሕግ አላት የወንጀለኛ መቅጫ፣ የፍትሐብሄር አላት ይህ ነገር መሬት መውረድ አለበት ዝም ብሎ እንደ ኳስ ብቻ እየተንከባለለ ከዘመን ዘመን መሸጋገር የለበትም  ስር ማብቀል መቻል አለበት።

መለምለም መቻል አለበት ሁላችንም በሱ ጥላ ስር የምንከለል መሆን አለበት ጾታን ብሄርንም ሃይማኖትንም ባማከለ መልኩ ለሁላችንም ጥላ ሊሆን የሚችል ህግ መሆን አለበት እስከዛሬ እንደ ኳስ እየተንከባለለ ነው የመጣው ስር የለውም ስር ማስያዝ ቅጠል እንዲይዝ ማድረግ ያስፈልጋል።” ብለዋል

በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤሌዘር ታደሰ በበኩላቸው ህገመንግስቱ በራሱ በአብዛኛው ጥሩ ነገር ይዟል። ግን ሕገ መንግስቱን እየፈጸምን ነው ወይ ስንል በጣም ትልቅ ክፍተት አለ ብለዋል ።

በአገሪቷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ካለው ለውጥ አንዱ የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች መሆናቸውን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሁሉም ዜጋ ሃላፊነትና ግዴታ መሆኑንም ጨምረው  አንስተዋል።

መንግስት የዴሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር የህግ የበላይነትን ለማስከበር እያደረገ ያለውን ጥረትም አድንቀዋል።

የዴሞክራሲ ተቋማት በቂ ልምድና ችሎታ ባላቸው ሰዎች መመራቱ ደግሞ ሥራውን የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርገውም ነው አስተያየት ሰጩዎች የሚናገሩት።

”ኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ የበላይነት ተከብሮ አያውቅም በታሪክም በምናይበት ጊዜ የመንግሥት የበላይነት ነው በተቋማት ውስጥ የሚታየው የዕዝ ሂደት ነው የዕዝ ውሳኔዎች ነበሩ፡፡ አሁን እነዚህ ተቋማትን ብቃታቸው እየዳበረ አለምአቀፍም አገራዊም ልምድና ችሎታ ያላቸውን ሰዎች እያመጣ እያየን ነው ይህ በዚህ ከቀጠለ መልካም ነገር የምናይ ይመስለኛል።  ” ብለዋል ዶክተር አልማው ክፍሌ

ዶክተር ኤሌዘር ታደሰ በበኩላቸው ስርዓተ አልበኝነት እየሰፈነ የመጣበት ሁኔታ እንደነበር ሕግን ከማስከበር አንጻር በጣም ጥሩ ጅምር ሥራ እየተሠራ እንደሆነ  ጠቁመዋል  

እስካሁን በነበረው ሁኔታ በተለይ የተማረው የሰው ሃይል ለአገሪቷ በእውቀቱና በክዕሎቱ ማበርከት የነበረበት ሙያዊ አስተዋዕኦ የጎላ እንዳልነበርም  ገልጸዋል።

ምሁራኑ ፍትህና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ እስር፣ ከሥራ መታገድና ሌሎች ተጽዕኖ ይደርስባቸው የነበረ በመሆኑ ሙያዊ አስተዋጽኦ ከማበርከት ሸሽተው እንደነበር አስታውሰው አሁን የመጣው ለውጥ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ተናግረዋል።

መንግስት ዴሞክራሲንና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየወሰዳቸው ካሉ እርምጃዎች መካከል የፍትህና የዴሞክራሲ ተቋማትን  በአዲስ መልክ ማደራጀትና አዳዲስ አመራሮችን መሾም አንዱ ነው።

 

 

%d bloggers like this: