በምዕራብ ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር መፈታቱን በመከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ አስታወቁ

17 Dec

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

ዋና አዛዡ ሜጀር ጀኔራል አስራት ደኔሮ (ኢዜአ)

አሶሳ ታህሳስ 7/2011 (ኢዜአ) በምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ሲያጋጥም የነበረው የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴ መስተጓጎል ችግር መፈታቱን በመከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ አስታወቁ።

ዋና አዛዡ ሜጀር ጀኔራል አሥራት ደኔሮ ለኢዜአ እንደገለጹት በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልል አጎራባች አካባቢዎች የታጠቁ ኃይሎች የፈጠሩት የጸጥታ ችግር በህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል።

ከዚህ በተጨማሪ ከአሶሳ አዲስ አበባ፣ ከነቀምት አዲስ አበባ፣ ከነቀምት አሶሳ እና ከነቀምት ቡሬ መስመር የንግድና የትራንስፖርት መስተጓጎል ሲያጋጥም መቆየቱን ተናግረዋል።

“ችግሩን ያስከተሉት የታጠቁ ሃይሎች ከሃገር መከላከያ ሠራዊት አቅም በላይ ሆነው አይደለም” ያሉት አዛዡ የብሄራዊ ጸጥታና ደህንነት ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ሰሞኑን የምዕራብ እዝ ሃይል አካባቢውን መቆጣጠሩን አስረድተዋል።

ሠራዊቱ ከሁለቱ ክልሎች ጋር በመተባበር ባካሔደው የተጠናከረ ፍተሻ አካባቢው መረጋጋቱን ገልጸው በአማራ ክልል ከቅማንት አስተዳደር ጋር ተያይዞ የተከሰተው የጸጥታ ችግርም ካለፉት ሁለት ሣምንታት ወዲህ ወደ ሰላም መመለሱን ተናግረዋል።

ለተገኘው ውጤት የህብረተሰቡ ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር ጠቅሰው ሠራዊቱ እስከ ህይወት መሥዋዕትነት እንደከፈለም አዛዡ ጠቁመዋል፡፡

የግጭቶቹ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚደረገውን ጥረት መደገፍ የሰራዊቱ ትኩረት መሆኑን ጠቁመው ከየአካባቢው አስተዳደር ጋር በመቀናጀት ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው መመለስና የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም ሃገሪቱ ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት ድንበር በኩል የሚከሰተውን ህገ-ወጥ የሰዎች እና የጦር መሣሪያ ዝውውር በትኩረት እየተከታተለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

 

%d bloggers like this: