ኦዲፒና ኦነግ ሳይደማመጡ የሚመክሩ መምሰላቸው በጊዜ ማብቃት አለበት!

21 Dec

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

የኦሮሞ ዴሞመራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ታህሳስ 20/2018 አሰቸኳይ ስብሰባ አክሂዶ፣ “ማንኛውም የፖለቲካ ፉክክር በጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ሊሆን ይገባል” የሚል መግለጫ አውጥቷል።

በዚህም መግለጫው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በብዙ መሥዋዕትነት የተገኘውን ድል ለማስቀጠል የፖለቲካ ፉክክር በሰላማዊ መንድ መካሄድ እንዳለበት አሥምሮበታል

የአሁኑ የኦዲፒ መግለጫ ኮስተር ያለና ”በሕዝብ ትግል የተቀዳጀነው ድል በጠላት ሴራ ለሰከንድም ቢሆን አይደናቀፍም፤ ወደ ኋላም አይመለስም” አባባሉ ለፍጥጫ የተደረገውን ዝግጅት የሚያውጅ ይመስላል።

ኦነግ በበኩሉ እስካሁን ከተሰማው በላይ ቅላጼውን እያካረረ የሚያነሳው ጉዳይ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት የተደረስው ስምምነት በመንግሥት በኩል አልተከበረልኝም የሚለው ነው።

ከኦዲፓ አስቸኳይ መግለጫ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ኦነግ የራሱ የሆነ ነጻ ግዛት አለው የሚል ዕወጃ ተደርጎ ነበር። ዛሬ ደግሞ አባሎቻችን ሰሞኑ ታሥረውብናል የሚል ሮሮ አቶ ዳውድ ኢብሳ አሰምተዋል።

በሌላ በኩል ግን ኦነግ ውስጠ ግንዛቤው ሸብረክ እያለ ራሱን ከመንግሥት እኩል አድርጎ የሚመለከትና በአጭር ቆይታው በዚህ ዙርያ ብዙ ሲናገር ተደምጧል። በተለይም ከኛ ጋር ሳይመከር ይህ ያ ተደረገ አቶ ዳውድ ኢብሳ ሲናገሩ ይሰማል። ገና ከመጀመሪያው በትጥቅ መፍታት ዙሪያ ‘ማን ማንን ያስፈታል’ አባባላቸው አያሌ ኢትዮጵያውያንን እንዳስቀየመ እሳቸውም ሳይሰሙ አይቀሩም።

መንግሥትም በፈለገውና ቦታና ወቅት፣ የሃገሪቱ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነቷ እንዳይደፈር አስፈልጊ ሆኖ ባግኘበት ወቅት፣ በሕጉ መሠረት ሠራዊቱን የማዝ መቱን አቶ ዳውድ ኢብሳ ከእርሳቸው ጋር አለምክክር መደረጉን በምሬት ማንሳታቸው በቅንዓት የሚያዩት አስመስሏቸዋል!

እሳቸው ግን ዛሬም፥ ከፍተኛ የሆነ የመንግስት ሠራዊት በባሌ፣ በጉጂና በወለጋ ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ አደረገ ብለው የመንግሥትን ሥልጣን ለመገደብ የሚሻ እሮሮ አሰምተዋል።

የትኛው ሃገር መንግሥትና ዜጎች ናቸው  አንድ ነፃ አውጭ ግንባር ነኝ ባይ የታጠቀ ኃይል ሃገራቸው ውስጥ ነጻ ወታደራዊ ሥልጠና ክልል አለኝ ሲል በፈንጠዝያ ሊመለከቱ  የሚችሉት?

ነገሮች እንደዚህ ቀኝና ግራ በሚሥፈነጠሩበት ወቅት፡ ዛሬ እንዳደረጉት አቶ ዳውድ ኢብሳ  ደግሞ ቀዝቀዝ ይሉና “የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በክልሉ ሰላም እንዲኖር ቁርጠኛ አቋም ካለው ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን” ያሰማሉ!

እስከመቼ ነው እንዲህ መንግሥትና ኦነግ የሚንገታገቱት— በተለይም በምዕራቡና ደቡቡ የሃገራችን ክፍሎች— ሕዝቡ በፍርሃትና ለጭፍጭፋ ተጋልጦ እያለ? የጡንቻ ፖለቲካ አስከፊ በሆነ መልኩ ለምን ለሥልጣን መደራደሪያና በር ከፋች ተደርጎ ሲወሰድ ተውኝ የፈለገኝኝን ላድርግ ይባላል ወይ?

ለአቶ ዳውድና የኦነግ ጓዶቻቸው ታስቦ ነው መሰለኝ፡ የኦዲፒ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሃገሪቱ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የመጠላላትና የአፈሙዝ ፖለቲካ በውይይትና ሰላማዊ እንዲቀየር ኢትዮጵያ ውስጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻሉን እንደገና ማስታወስ ያስፈለገበት!

ለዚህ የአቶ ዳውድ መልስ፡ “ትላንት የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ/ኦዴፓ/ጦርነት የሚመስል አዋጅ አውጆብናል…ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ዛሬ የወጣው መግለጫም ይህንኑ ያጠናክራል” ነው።

ይባስ ብሎም፣ አቶ ዳውድ “ሠራዊታችን ጥቃት አይፈጽምም” ያሉት የኦነጉ ሊቀመንበር “ራሱን እንዲከላከል ግን ትዕዛዝ ሠጥተናል” ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሁላችን ናትና ሌላውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ድርሻ እንዳለው አቶ ዳውድ ኢብሣ ልብ ሊሉ ይገባል!

ልብ የሚሉ ከሆነ፣ ዛሬ ከሶስት አሥርታት ባርነት በኋላ፣ ዛሬ ሕዝባችን የሚሻው ሙሉ ነፃነቱንና በሰላም ወጥቶ መግባትና ኑሮውን ማሻሻል ነው እንጂ የሥልጣን ጥመኞችን ፍላጎት ለማርካት አይደለም!

 

%d bloggers like this: