ቅጥ ያጣ ሙስናና ዘረፋ ሃገራችንን ሊጥላት ነው! ዜጎች በማጋለጡ ይተባበሩ!

27 Dec

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

Credit: Fana

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከውጭ ጭነው የገቡትን ነዳጅ ሳያራግፉ ከሀገር ሊወጡ የነበሩ ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሁለት የነዳጅ ጫኝ (ቦቴ) ተሽከርካሪዎች መነሻቸዉን ጅቡቲ በማድረግ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የጫኑትን ነዳጅ ሳያራግፉ ከሀገር ሊወጡ ሲሉ ነው በቁጠጥጥር ስር የዋሉት።

ተሽከርካሪዎቹ ነዳጁን ወደ አዶላ እና ደባርቅ ከተሞች እንዲያደርሱ የተሰጣቸውን ፍቃድ በመጣስ ከሀገር ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

አንደኛው ተሽከርካሪ 46 ሺህ 700 ሊትር ነዳጅ ወደ ደባርቅ ከተማ እንዲሁም ሌላኛው ተሽከርካሪ ደግሞ 47 ሺህ 59 ሊትር ነዳጅ ወደ አዶላ ነበር የጫኑት።

ሆኖም ግን ከተፈቀደላቸው መስመር ውጪ ከሀገር ለመውጣት በገቢዎች ሚኒስቴር የጉምሩክ ኮሚሽን የጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከአዲስ አበባ በደረሰው ጥቆማ መሰረት መያዛቸው ነው የተገለፀው።

የጉምሩክ ሰራተኞችን ከክልሉ አድማ በታኝ ሀይል ጋር በማቀናጀት ሁለቱንም ተሽከርካሪዎች ጅግጅጋ ከመድረሳቸዉ በፊት ካራማራ በተባለ ቦታ ታህሳስ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 6፡30 አካባቢ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የቅርንጫፉ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ደመላሽ ተሾመ አስታውቀዋል።

ይህን መሰል ህገ ወጥ ድርጊት ለመከላከል መንግሥት ከምንጊዜውም በላይ ጠንክሮ እየሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ ደመላሽ፥ ህዝቡም እያደረገ ላለው ንቁ ተሳትፎም ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም ህገ ወጦችን በንቃት በመከታተል ለህግ እንዲቀርቡ በማድረግ የበኩሉን ሃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም ስራ አስኪያጁ አሳስበዋል።

 

%d bloggers like this: