“ለውጡ አሁንም ሕዝባዊ መሠረት” እንደያዘ ነው የሚለው ኢሕአዴግ “ሕዝባዊ መሠረት የሌላቸው ፀረ ለውጥ አስተሳሰቦችም በተቀናጀ መንገድ እየተመሩ በመሆኑ ለለውጡ ተግዳሮት” መሆናቸውን ገለጸ

20 Jan

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

አዲስ አበባ  ጥር 10/2011 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢሕአዴግ/ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ሰላምን፣ የሕግ የበላይነትንና ፍትህን ማረጋገጥ እንዲሁም ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ ማድረግ ቁልፍ ተልዕኮ መሆኑን አስታወቀ።

ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከጥር 7 እስከ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ያካሄደውን መደበኛ ስብሰባ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ግምገማ በማካሄድና አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን የኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ ገልጿል።

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው እንዳስታወቀው፤ በኢትዮጵያ በመስኖ ልማትና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የተቀዛቀዘውን አገራዊ ኢኮኖሚ ለማነቃቃት መረባረብ ይጠይቃል።

ማንኛውም ለግጭትና አለመረጋጋት የሚዳርጉ ሁኔታዎች በግልጽ በመለየት በአስቸኳይ መታረም እንዳለባቸው የጠቆመው መግለጫው፤  ሁሉም የግንባሩ አባል ድርጅቶች በዝርዝር ገምግመው የጋራ ባደረጉት ስምምነት መሠረት በተግባር እንዲመሩ አሳስቧል።

መንግስትሕግን የማስከበር ቁልፍ ኃላፊነቱን በጥብቅ መወጣት እንዳለበት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል።

ከዚህ በፊት ይስተዋሉ የነበሩ ሌብነትና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፈጽሞ እንዳይደገሙ በቂ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ የገለጸው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው፤ ለዚህ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ዝንባሌዎችን በሁሉም የሥራ መስክ እየፈተሹ መጓዝ እንደሚገባም አቅጣጫ አስቀምጧል።

አገራዊ ለውጡ ጥልቅ፣ ሰፊና ትልቅ ተስፋ ይዞ የመምጣቱን ያህል ከተስፋው በተቃራኒ ስጋቶችንም ያዘለ መሆኑን በአፅንኦት ገምግሟል።

ለውጡ አሁንም ሕዝባዊ መሠረት ይዞ በኢሕአዴግ እየተመራ ያለ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ ሕዝባዊ መሠረት የሌላቸው ፀረ ለውጥ አስተሳሰቦችም በተቀናጀ መንገድ እየተመሩ በመሆኑ ለለውጡ ተግዳሮት እንደሆኑ ገልጿል።

ከለውጡ በተቃራኒ ያሉ ኃይሎች ህዝቡን ለማደናገርና ድጋፍ ለማግኘት እንዲያመቻቸው በሕዝቡ ውስጥ ያሉ ብዥታዎችንና በለውጡ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የአመራር ግድፈቶችን እንዲሁም ማንነትንና ሌሎች አጀንዳዎችን ምክንያት በማድረግ ጽንፈኛ አካሄድ በመከተል የራሳቸውን ፍላጎት ለማስፈጸም ሲሉ በዜጎች ህይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስና ዜጎች ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ እየሰሩ እንዳሉ ኮሚቴው ገምግሟል።

እንዲሁም የለውጡ አደናቃፊ ኃይሎች በሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር በመታገዝ ግጭትና መፈናቀል እንዲፈጠር፣ ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር በመሰሉ የኢኮኖሚ አሻጥሮች በመሳተፍ ለውጡን ለመግታት እየተረባረቡ እንደሚገኙም ገምግሟል።

ድርጅቱ በውስጥ አሁንም በለውጡ ምንነት፣ በለውጡ ውስጥ ባለ ሚና እና በወደፊት አቅጣጫዎች ላይ የተሟላ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ፈጥሮ በእኩል ሚዛን እየተጓዘ አለመሆኑን ጠቁሞ፤ የታችኛው መዋቅርም አለመደገፉ እና በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል ያሉ የአካሄድ ዝንፈቶችና የእርስ በርስ መጠራጠር በግልጽ ተነስተው ትግል እንደተደረገባቸው ኮሚቴው አስታውቋል።

በድርጅቱ ያሉ ችግሮች በቀጣይ እንዲስተካከሉ መግባባት ላይ መደረሱን የገለጸው፤ ኮሚቴው እንደ አገርና ህዝብ ያለው አማራጭ ጽንፈኝነትን በማክሰም አንድነቷ የተጠናከረ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ለውጡን ማስቀጠል ላይ መግባባት መፈጠሩን አመልክቷል።

ለውጡ ሁሉን አቀፍና ዘላቂ እንዲሆን በማድረግ በኩል አሁንም ከፍተኛ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ችግሮች እንዳሉ ያነሳው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፤ የለውጡ ዘላቂነት የሚረጋገጠው ሰላምን በመገንባት፣ ፍትህን በማረጋገጥ፣ ዴሞክራሲን በማስፋት፣ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግሩን በመፍታት፣ አገራዊ አንድነትናክብርን በዘላቂነት ማረጋገጥ ሲቻል ብቻ እንደሆነም ገልጿል።

ኢህአዴግን ማጠናከር፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የሲቪክ ማህበረሰብና የምሁራንን አቅም መገንባት፣ የመንግስት ሠራተኛው በእውቀትና በትጋት ላይ ተመስርቶ እንዲሰራ ማስቻል ዋነኛ ተግባሮቹ እንደሆኑ ኮሚቴው አፅንዖት የሰጠው ጉዳይ እንደሆነም ገልጿል።

እንዲሁም ከአጋር ድርጅቶች ጋር ያለውን መደጋገፍ ይበልጥ እንደሚያጠናክርም ኮሚቴው ያስቀመጠው አቅጣጫ ያመለክታል።

ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ያላቸውን ሀብት በሙሉ በማስተባበርና በማቀናጀት መላ ህዝቡን ወደ ልማት ማስገባት ዋና አገራዊ ዘመቻ መሆን እንዳለበት የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ኮሚቴው አስታውቋል።

በዲፕሎማሲው ረገድም የአገሪቷን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ተቀምጧል።

በትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ተማሪዎችና ምሁራን ለውጡን ለመደገፍ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ ፀረ ለውጥ ለሆኑ ቅስቀሳዎች ሰለባ ሳይሆኑ የተጀመረውን ለውጥ የማስቀጠል ሚናቸውን እንዲወጡ በማድረግ በኩል የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት አለመወጣታቸውን ገምገሟል።

ሁኔታውን ለመቀየር የሚያስችሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታውቋል።

መገናኛ ብዙኃን በነፃነት የሚሰሩበት ሁኔታ የተፈጠረና የህዝብ ድምፅ የመሆን ጅምር እንዳላቸው ያወሳው መግለጫው፤ የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክርና የተሻለች አገር ለመገንባት የሚያስችል አተያይ የመፍጠር እና ተዓማኒነታቸውን የሚፈታተን የስርጭት ችግር እንዳለባቸው ኮሚቴው ገምግሟል።

“ለውጡ ያስፈለገው በትናንቱ ለመቆዘም ሳይሆን ወደፊት ለመወንጨፍ ሲሆን መገናኛ ብዙኃን የህዝቡን አተያይ በመቅረጽ በኩል ብዙ ይቀረዋል” ሲል የገለጸው ኮሚቴው፤ በተለይ ማህበራዊ ሚዲያው እየተጫወተ ያለው አዎንታዊ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ አሉታዊ ሚናው እየጎላ በመምጣቱ ከለውጡ ጋር በተዛመደ መልኩ የሚታረምበትን አካሄድ መከተል እንደሚገባ አመላክቷል።

የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከለውጡ ተነስተው በሰላማዊ መንገድ መታገል እንደሚቻል አቋም መያዛቸውንና የጋራ ውይይት መጀመራቸውን አድነቋል።

አንዳንድ ፓርቲዎች ግን ጽንፈኝነትን በመስበክ የቆየውን የህዝቦች አንድነት በመሸርሸርና የህግ የበላይነትን ባለማክበር እየተንቀሳቀሱ እንዳሉ የገመገመ ሲሆን፤ ከዚህ ተግባራቸው በመቆጠብ በሐሳብ ልዕልና እና በውይይት ለመድበለ ፓርቲ ስርዓቱ መጎልበት ገንቢ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።

የድርጅቱ አባላት፣ አመራርና መላ የአገሪቷ ህዝቦች የተጀመረውን ለውጥ በማስቀጠል አገሪቷን ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ለማሸጋገር በሚደረገው ርብርብ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ እንዲሁም ለኮሚቴው አቅጣጫዎች ተፈፃሚነት ያላሰለሰ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አድርጓል።

 

 

%d bloggers like this: