Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ National Movement of Amhara
በአዲስ አበባና በዙሪያው ባሉ ከተሞች ዘርን መሠረት ያደረገ ቤት የማፍረስና የማፈናቀል እርምጃ በአስቸኳይ እንዲቆም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ያሳስባል። አብን ማንኛውም ዜጋ በመረጠው አካባቢ ጎጆ ቀልሶ የመኖር ተፈጥሯዊ መብት እንዳለው ይገነዘባል። ይሁን እንጅ «ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው» እየተባለ ከበሮ በሚደለቅበት በዚህ ሰዓት «አዲስ አበባ የእኛ ናት፤ ሌላው ከፈቀድንለት ብቻ ይኖራል» በሚል አክራሪ ቡድን ፊታውራሪነት የሚደረገው የዜጎች መጎሳቆል የሚያሳስበን መሆኑን እያሳወቅን፤ ይህ ነገር በአስቸኳይ የማይቆም ከሆነ ሁሉንአቀፍ ትግል በማድረግ ግፈኞቹን ፊት ለፊት የምንጋፈጣቸው መሆኑን ከወዲሁ እናሳስባለን።
ስለሆነም በለገጣፎና እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞች ጎጆ ቀልሰው በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ «ከእኛ ወገንአይደላችሁም» በሚል አክራሪነት የሚደረገው መፈናቀልና ንብረት ማውደም በዋናነት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና የፌዴራሉን መንግሥት ለተጠያቂነት የሚዳርግ መሆኑ ታውቆ በአስቸኳይ እንዲቆም፥ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችም ተመጣጣኝ ካሳ አግኝተው ሰላማዊ ኑሮ የሚኖሩበት ሁኔታ በመንግሥት ወጪ እንዲመቻችላቸው እየጠየቅን፥ መላው ኢትዮጵያዊያን ከተጎጂዎች ጎን በመቆም እንዲያጽናና እና ግፈኞች ለሕግ እንዲቀርቡ ከአብን ጎን ተሰልፎ ግፊት እንዲያደርግ አበክረን እንጠይቃለን።
የአማራብሔራዊ ንቅናቄ
ቅፅ 1 ቁጥር 14 የካቲት 15/2011 ዓ.ም
አዲስ አበባ፥ሸዋ፣ ኢትዮጵያ