በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩና የሽብር ጥቃት በሃገሪቱ ለመፈፀም ሲዘጋጁ የነበሩ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

12 Apr

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 4፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩና የሽብር ጥቃት በሃገሪቱ ለመፈፀም ሲዘጋጁ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።

ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ አቶ በርሃኑ ፀጋዬ በሰጡት መግለጫ እንደጠቆሙት፥ በሶስት የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ከተፈፀሙ የሙስና ወንጀሎች ጋር በተያያዘ የተቋማቱን የስራ ኃላፊዎችና ባለሃብቶች ጨምሮ 59 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቀዋል።

አቶ ብርሃኑ በመንግሥት ተቋማትና ፕሮጀክቶች ላይ የተፈፀመ ከባድ ወንጀሎችን በተመለከተ ባለፉት ሶስት ወራት
ምርመራ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህ ምርመራም በወንጀሎቹ የደረሰውን ጉዳትና ተጠርጣሪዎቹ ያደረሱትን ብክነት ተመርምሯል ነው ያሉት።

በብዛት ሙስና ይፈፀማል ተብሎ የሚታመነው በግዢ ሂደት በመሆኑ በመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር አገልግሎት ተቋም ላይ ምርመራ ተካሂዷል ብለዋል።

ይህ ተቋም ላይ በተካሄደው የምርመራ ውጤት መሰረትም ከ400 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዢ ጋር በተያያዘ በጥቅም በመመሳጠር ተጠርጣሪዎቹ በመንግስት ላይ በአጠቃላይ 23.7 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህ ግዥ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎቹ የዳቦ ዕጥረት እንዲከሰት በማድረግ በሕዝብና በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ማድረሳቸው ተነግራል፡፡

ከኮምፒውተር ግዥ ጋር ተያይዞ የቴክኒክ ምርመራ ያለፉ አቅራቢ ድርጅቶ እያሉ ምርመራውን ካላለፉ ተቋማት ግዥ እንዲፈፀም ተደርጓልም ነው ያሉት፡:

በውሃ ስራዎች ኮንስትራክን ኮርፖሬሽን ውስጥ የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች እርስ በርሳቸው በመመሳጠር ከ55 ሚሊየን ብር በላይ ያለ አግባብ በተፈፀመ የብረት ግዢ ውስጥ የተፈፀመ የሙስና ወንጀል መኖሩንም ገልጸዋል።

እንዲሁም የመድሃኒት ፈንድ ኤጀንሲም ከግዥ ስርዓቱ ውጭ የ79 ሚሊየን ብር ግዥ መፈጸሙን አቃቢ ሕጉ አንስተዋል።

 

በአመራሮች ላይ እየተካሄደው ባለው ማጣራት ካላቸው ገቢ በላይ ንብረቶችን አፍርተው እንደተገኙ መረጋገጡንም ነው የተናገሩት።

 

አቶ ብርሃኑ በመግለጫቸው ከፍተኛ የሽብር ጥቃት በሃገሪቱ ለመፈፀም ሲዘጋጁ የነበሩ ቁጥራቸው ያልተጠቀሱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ጠቅሰዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ከሌሎች ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ሽብር የሚፈፅሙበትን ስልት በመቀየስና ቦታ በመለየት ላይ እንደነበሩ አውስተዋል።

ለሽብር ጥቃቱ በዝግጅት ላይ ነበሩ ያሏቸው ተጠርጣሪዎች ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባባር በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አመላክተዋል።

በእጃቸው በተያዙ ሰነዶች መሰረት የሽብር ጥቃቱን ቢፈፀሙ የከፋ ጉዳት ሊያደርሱ ይችሉ እንደነበር ጠቅሰው፥ በተዘጋጁ እና በሂደት ላይ በሚገኙ አዋጆች ዙሪያ ለጋዜጠኞቹ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህ ወቅትም በሀገሪቱ ያለውን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለመከላከል የሚያስችል አዋጅ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

አዋጁ በሃገር አቀፍ ደረጃ ሕጋዊ የጦር መሣሪያ አያያዝን ለማስተካከል የሚረዳ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተለይ በማዘዋወር፣ በመጫንና በተለያዩ መንገዶች በሚሳተፉ አካላት ላይ ከፍተኛ ቅጣትን የሚያስከትል መሆኑን በመጥቀስ።

በተመሳሳይ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃዎችን ሥርጭት ለመከላከል ታስቦ የተዘጋጀው አዋጅ ከሕገ መንግሥቱና ከዜጎች መሰረታዊ መብቶች ጋር እንዳይጣረስ ሆኖ መዘጋጀቱንም ነው በንግግራቸው ያነሱት።

አቶ ብርሃኑ አዋጆቹ የፓለቲካ ምዳሩን ለማስፋት፣ የሰብዓዊ መብትን ለማረጋገጥ እና የስራ አድል ፈጠራን ለማሻሻል እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል፡፡

 

%d bloggers like this: