ጌታቸው አሰፋ በሌሉበት ሊከሠሡ!

13 Apr

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

በአገር ውስጥ ተቀምጠው በሌሉበት መከሰሳቸው አነጋጋሪ ሆኗል!

የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅነንት መሥሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር የነበሩትና ለዜጎች የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሞት ተጠያቂ ናቸው ተብለው  የተጠረጠሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ፤ በሚቀጥለው ሣምንት በሌሉበት ክስ ሊመሰረትባቸው መሆኑን ምንጮች ጠቆሙ፡፡

የቀድሞው የደኅንነት መ/ቤቱ ሃላፊ የነበሩት  አቶ ክንፈ ገ/መድኅን በሞት መለየትን ተከትሎ፣ ከ1993 ጀምሮ በደህንነት መ/ቤት በዋና ዳይሬክተርነት ሲሰሩ የቆዩት አቶ ጌታቸው አሰፋ፤የዛሬ አንድ ዓመት ገደማ  ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ከሃላፊነት ከተነሱ የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የሚሠለፉ ናቸው፡፡ ሰኔ 16 ቀን 2011 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተደረገው የድጋፍ ሠልፍ ላይ ከደረሰው የቦንብ አደጋ ጋር ተያይዞ እጃቸው እንዳለበት እንዲሁም በዜጎች  የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሞት ተጠርጥረው ክሥ ሊመሠረትባቸው መሆኑ ከጥቂት ወራት በፊት ተገልጦ ነበር፡፡

በደኅንነትና መረጃ  መ/ቤት የሥልጣን  ቆይታቸው ወቅት ከመንግሥት እውቅና ውጪ የራሳቸውን እሥር ቤት በመፍጠርና ህጉ ከሚያዘው ፍፁም ተቃራኒ በሆነ መልኩ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጣረሱ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ ትእዛዝ ሰጥተዋል፤በቀጥታም ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩት አቶ ጌታቸው፤ ሌሎች በተመሳሳይ ወንጀል የተጠረጠሩ የቀድሞው የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በፍርድ ቤት ክሥ ቢመሰረትባቸውም፣ እሳቸው ግን የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ከለላ ስለሰጣቸው ሊከሰሱ አለመቻሉን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ  ለፓርላማ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በሕግ የሚፈለጉት አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ የትግራይ ክልላዊ መንግስት የጸጥታ ሃላፊ ሆነው  መሾማቸው አነጋጋሪ ሆኖ ቢቆይም፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል  በቅርቡ ለአዲስ አድማስ በሠጡት ቃለ ምልልስ፤ አቶ ጌታቸው አሰፋ አልተሾሙም ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ አቶ ጌታቸው በወቅቱ  የት እንደሚገኙ የተጠየቁት ዶ/ር ደብረጽዮን፤ ”ተደብቀዋል” ማለታቸው አይዘነጋም:: ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፤ አቶ ጌታቸው አሰፋን ለሕግ ለማቅረብ የክልሉ መንግስት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ለሁለተኛ ጊዜ መጠየቃቸውን ለማወቅ ባይቻልም፣ በሌሉበት ክስ ይመሰረትባቸዋል ተብሏል፤የክሱ ይዘት በትክክል ባይታወቅም፡፡

ምንጮች እንደሚሉት፤ ከጠ/ሚኒስትሩ የግድያ ሙከራ፣ በእስረኞች ላይ ከሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ከሙስና ጋር የተያያዙ ክሦች ሊመሠረትባቸው ይችላል፡፡

 

/Addis Admas

 

 

%d bloggers like this: