የባለአደራ ምክር ቤት አባላት ከ’መፈንቅለ መንግሥቱ’ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት ቀረቡ

26 Jun

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

የፌደራል ፖሊስ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመሆን በአንድ መዝገብ ስድስት ተጠርጣሪዎችን ዛሬ ፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ የወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

ተጠርጣሪዎቹ አንደኛ በሪሁን አዳነ፣ መርከቡ ኃይሌ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ጌዴዮን ወንድወሰን፣ ማስተዋል አረጋና አቶ ሐየሎም ብርሃኔ ናቸው። ፖሊስ ግለሰቦቹ ፍርድ ቤት የቀረቡት በአማራ ክልል ተፈፀመ በተባለው “መፈንቅለ መንግሥት”ና አዲስ አበባው ግድያ “እጃቸው አለበት፤ በተለያየ ደረጃ ተሳትፎ ያላቸው ስለሆነ ጠርጥሬያቸዋለሁ፤ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለመናድ፤ በሽብር ተግባር ተሳትፈዋል።”  ማለቱን ከተከሳሾቹ የአራቱ ጠበቃ የሆነው አቶ ሄኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ ገልጿል።አቶ መርከቡ ኃይሌና አቶ ስንታየሁ ቸኮል የምክርቤቱ አመራሮች ሲሆኑ፣ አቶ ጌዴዮን ወንድወሰንም የባላደራ ምክር ቤቱ አባል ነው። አቶ በሪሁን አዳነ ጋዜጠኛ ሲሆን፤ አቶ ማስተዋል አረጋ የኮሌጅ መምሕር መሆናቸውን የገለፀው አቶ ሄኖክ፣ አቶ ኃየሎም ብርሃኔ ስለተባሉት ተጠርጣሪ ዝርዝር መረጃ እንደሌለው አመልክቷል።

• የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክርቤት መግለጫ ምን ይላል?

• “የዲሞክራሲ ጥማት የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ መድረሱን ተመልክቻለሁ”

ጠበቃው እንዳሉት ግለሰቦቹ በፀረ ሽብር አዋጅ መሰረት 28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል። ተጠርጣሪዎቹ አደረጉት የተባለው ነገር ተለይቶ በዝርዝር የቀረበ ሳይሆን በደፈናው “በመፈንቅለ መንግሥቱ” ጠርጥሬያቸዋለሁ የሚልና ዝርዝር ያልቀረበበት ነው።

ስለዚህም በመፈንቅለ መንግሥቱ ይህን ይህን አድርገዋል ብለህ በሁሉም ተከሳሾች ላይ አቅርብ፣ በሁለተኛ ደረጃ በዛሬው ዕለት ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን ይዞ ስላልመጣ እኛ ደግሞ የተከበረው ፍርድ ቤት መዝገቡን ይይልን እነዚህን ሰዎች ለመያዝ ምንም የሚያስጠረጥር ምክንያት የለም ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ጠበቃ ሔኖክ ተናግረዋል።

ክስ እንዳልተመሰረተ የሚናገረው ሔኖክ ማስረጃ ሊያሸሹ ስለሚችሉ በማረፊያ ቤት ቆይተው ምርመራው እንዲቀጥል ፖሊስ በጠየቀው መሰረት ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ፖሊስ አደረጉት የሚባለውን ነገር በዝርዝር ለየብቻ እንዲያቀርብ፤ የምርመራ መዝገብ ይዞ ባለመቅረቡም፤ የምርመራ መዝገብ ይዞ እንዲቀርብ በማለት ለሐምሌ 17 ቀጠሮ ትእዛዝ መስጠቱንም ያስረዳል።

ግለሰቦቹ በትክክል መቼ እንደተያዙ ዝርዝሩን ባያውቅም ጥቃቱ ተፈፀመ ከተባለበት ከሰኔ 15 ቀን 2011ዓ.ም በኋላ ሰኔ 17 እና 18 መያዛቸውን ይናገራል።

ተጠርጣሪዎቹ ባህርዳር ሄደው ነበር ? ለሚለው ጥያቄ በሁሉም እርግጠኛ ባይሆንም ከሳምንት በፊት አቶ ስንታየሁ ወደ ባህር ዳር እንደሄደ ባህርዳር የሄዱት በመኪና ሲሆን ባላደራ ምክርቤቱ እሁድ እለት ሊያደርገው ለነበረው ህዝባዊ ስብሰባ እንደነበር ሄኖክ አስረድቷል።

“ፖሊስ እንዳለው በስልክ እየተነጋገሩ ከጉዳዩ ጋር የተገናኘ ነገር ይፈፅሙ ነበር የሚል ጉዳይ አንስቷል። ፖሊስም ሁሉም ባህርዳር ሄደዋል ሳይሆን የሚለው ባህርዳር የሄዱትና ያልሄዱት ተሳትፎ አድርገዋል የሚል ነው”ሲልም አክሏል።

ስድስተኛው ተጠርጣሪ ጄኔራል ሰዓረና ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ ሽኝት ፕሮግራም ላይ “የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ባሉበት ጥቃት ለማድረስ መሳሪያ ይዘው ተገኝተዋል” በሚል ሲያዝ ግለሰቡም የጥበቃ ስራ ስለሚሰራ መሳሪያ እንደያዘ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን አቶ ሔኖክ ይናገራል።

 

/ቢቢሲ አማርኛ

 

 

%d bloggers like this: