“ሕገ መንግሥት የሚፈርሰው በጋዜጠኛ ጽሑፍ ሳይሆን በመንግሥት ወይም በሕዝብ ነው”— የሕገ መንግሥት ባለሙያ

4 Aug

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

 

“ሕገ መንግሥቱ የመጻፍ፣ የመናገርና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አጎናፅፎ እያለ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ግን መንግሥትን ማማት እንደማይችል ተደንግጎ እንደሚገኝ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ የሚንቀሳቀስ አካል በሞት እንደሚቀጣ ደንግጎ ቢገኝም፣ ፓርላማው ግን በሞት የሚያስቀጣ መሆኑን በሌላ አዋጅ ሕግ አድርጎ ማውጣቱንም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እኔ የፓርላማ አባሎቻችንን የምጠይቀው ጥሩ ሕግ ማውጣት ቢቸግራቸው፣ መጥፎው ሕግ ከማውጣት እንዲቆጠቡ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሕግ ከመውጣቱ በፊት ሁለትና ሦስት ጊዜ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ ማንኛውም የሕግ ባለሙያ በሥራና በልምድ ዕውቀቱን ካካበተ በኋላ፣ ማሰብና ዓላማ ማድረግ ያለበት አገር የምትመራበትን ሕግ መጻፍ ነው “!

—አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ

“ማንም ሰው ምንም ዓይነት ሥልጣን ቢኖረው ለድርጊቱ ተጠያቂ የማይሆንበት ምክንያት [የለም]”!

— የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ

 

ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አንድ ጋዜጠኛ በጻፈው አንድ ወይም አሥር መጣጥፍ ሳይሆን፣ በመንግሥት ወይም በሕዝብ መሆኑን አንድ የሕገ መንግሥት ባለሙያ ተናገሩ፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ የፍትሕ አካላት ጥምረት ‹የሕግ ተገዥ ነኝ›› በሚል መሪ ቃል፣ ለአንድ ወር የሚያደርገውን ጉባዔ ሲከፍት በእንግድነት ተጋብዘው በተናገሩበት ወቅት ነው ይህንን ያሉት፡፡ ባለሙያው እንደገለጹት፣ አንድ ጋዜጠኛ የጻፈው ዘገባ ከአንድ ዓመት በኋላ አስከስሶታል፡፡ የተመሠረተበት ክስም ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ የሚል ነው፡፡ ሕገ መንግሥት ግን አንድ ጋዜጠኛ በጻፈው አንድም ይሁን አሥር መጣጥፍ ሊፈርስ እንደማይችል፣ በጋዜጠኛ መጣጥፍ የሚፈርስ ከሆነ ሕገ መንግሥት አለመሆኑን፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በጋዜጠኛ መጣጥፍ ቀርቶ ጫካ በገባ ኃይል እንኳን ማፍረስ ቀላል እንዳልሆነና የኢትዮጵያ ዓይነት ሕገ መንግሥት ሊፈርስ የሚችለው፣ በመንግሥት ወይም ‹‹ሥልጣን የሕዝብ ነው›› ስለሚል በሕዝብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ችግሩ የሕግ አውጪው ወይም ፓርላማው መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያው፣ ሕግን ለመንግሥት መሣሪያነት እንዲጠቅም በማድረግ በጣም አስገራሚ ሕጎችን እንዳወጣ አስረድተዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ የመጻፍ፣ የመናገርና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አጎናፅፎ እያለ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ግን መንግሥትን ማማት እንደማይችል ተደንግጎ እንደሚገኝ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ የሚንቀሳቀስ አካል በሞት እንደሚቀጣ ደንግጎ ቢገኝም፣ ፓርላማው ግን በሞት የሚያስቀጣ መሆኑን በሌላ አዋጅ ሕግ አድርጎ ማውጣቱንም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እኔ የፓርላማ አባሎቻችንን የምጠይቀው ጥሩ ሕግ ማውጣት ቢቸግራቸው፣ መጥፎው ሕግ ከማውጣት እንዲቆጠቡ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሕግ ከመውጣቱ በፊት ሁለትና ሦስት ጊዜ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ ማንኛውም የሕግ ባለሙያ በሥራና በልምድ ዕውቀቱን ካካበተ በኋላ፣ ማሰብና ዓላማ ማድረግ ያለበት አገር የምትመራበትን ሕግ መጻፍ ነው ሲሉ አቶ ሙሉጌታ አሳስበዋል፡፡

እሳቸው በውጭ አገር የቆዩ የሕግ ባለሙያ ቢሆኑም መንግሥት አሁን የሕግ ባለሙያዎች ሕግ እንዲጽፉ በማድረጉ፣ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር ሆኖ እየተሻሻለና እየተጻፈ በሚገኘው ሕግ ውስጥ እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው የፍትሕ ተቋማትን በተናጠል እያነሱ በሰጡት አስተያየት፣ ፖሊስን አስቀድመዋል፡፡ አንዳንድ የፖሊስ ሠራዊት አባላት የሚፈጽሙት ተግባር በጣም የሚያሳዝን መሆኑን ጠቁመው፣ ‹‹ፖሊስ እንዴት ሰውን አይረዳም?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ፖሊስ ሕዝብን የማገልገል ተቀዳሚ ተግባሩ በመሆኑ መርዳት እንዳለበትና ሌሊትም ሆነ ቀን በተሽከርካሪ እየተዘዋወረ አለኝታነቱን ማሳየት ተገቢ መሆኑን አክለዋል፡፡

አንድ ቦታ ላይ ጉዳት ሲኖር ፖሊስ እንደማይገኝና ቆይቶ ቢመጣም ከዕርዳታው ይልቅ ማዋከቡ እንደሚብስ ጠቁመው፣ ፖሊስ የሚታየው በድንገት መንገድ ዘግቶ ‹‹ተፈተሽ›› ሲል፣ ‹‹ለምን?›› ሲባል ደግሞ፣ ‹‹አላውቅም ወደዚያ ተሻገር የራስህ ጉዳይ›› ሲል ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ከሕዝቡ ጋር ተባብሮና ተስማምቶ አገልግሎቱን ማሳየት እንዳለበት፣ ሁሉም የኅብረተሰብ አካል በቀላሉ ሊይዘው የሚችልና የማይረሳ ስልክ ቁጥር በማስተዋወቅ፣ አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

ሌላው የሕግ ባለሙያው አቶ ሙሉጌታ ያነሱት ዓቃቤ ሕግን በሚመለከት ሲሆን፣ ዜጎች ያጠፉትን የወንጀል ዓይነትና የሚከሰሱበትን የሕግ ድንጋጌ ሳይለይ እንዲታሰሩ ማድረጉን በምሳሌ አስረድተዋል፡፡ዞን ናይን (ዞን 9) የሚባሉ ወጣቶች ‹‹ሕገ መንግሥቱ ይከበር›› የሚል መጣጥፍ ሲጽፉ፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ ተንቀሳቅሰዋል›› ተብለው ተጠርጥረው 28 ቀናት እተጠየቀባቸው ታስረው ከከረሙ በኋላ፣ ዓቃቤ ሕግ ሐሳቡን ቀይሮ በደረቅ ወንጀል መጠርጠራቸውን በመግለጽ ክስ እንደመሠረተባቸው አስረድተዋል፡፡ ‹‹ለምን መጀመርያውኑ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ለይቶና መርምሮ፣ በየትኛው የሕግ ድንጋጌና አንቀጽ እንደሚከሳቸው አውቆ አልከሰሳቸውም?›› በማለት ጠይቀው፣ ዓቃቤ ሕግ የሚጠይቅበትን ሕግ እንኳን እንደማያውቅ አስረድተዋል፡፡  ከላይ ከጠቀሱት በተጨማሪ የሕግ ባለሙያውን ያስገረማቸው ጉዳይ፣ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከተሞች በተፈጸመ ግድያ የተጠረጠሩ ሰዎች ታስረው ጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው በታመመ፣ ሆስፒታል በገባና ሊሞት ትንሽ ጊዜ በቀረው የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ መሆኑ ነው፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ሰፊ ውይይት ተደርጎበት፣ ተሻሽሎና ከፍተኛ ለውጥን አካቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ለመፅደቅ በመጠባበቅ ላይ እያለ፣ በሞተ ሕግ ተጠርጣሪዎችን ማሰር ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የሞተ ሕግ መጥቀስ ያስፈለገው ለረዥም ጊዜ እንዲታሰሩ ተፈልጎ ነው? ወይስ ሃያ ስምንት፣ ሃያ ስምንት ቀናት እያስፈቀዱ አስሮ ለማስቀመጥ? ወይስ ሞት እንዲፈረድባቸው ተፈልጎ?›› የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ ሞት ለማስፈረድ ከተፈለገም የተለያዩ ድንጋጌዎች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ዳኞች ዝም ብለው መፍቀድ የለባቸውም ብለዋል፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉን ከመጥቀስ መጨረሻ የሌለው የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ መጠየቅ እንደሚቻል ጠቁመው፣ ምንም ይሁን ምን ሁሉም በአግባቡና በሕጉ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ በመጨረሻ አስተያየት የሰጡት ስለፍርድ ቤቶችና ዳኞች አሠራር ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግና ፖሊስ አንድ ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት ይዘው በመቅረብ 14 ቀናት ለተጨማሪ ምርመራ ሲጠይቁ፣ አንድ ዳኛ ‹‹ለምን?›› ብሎ መጠየቅ እንዳለበትና አሳማኝ ባልሆነ ነገር ሙሉውን መፍቀድ እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት ‹‹ልማታዊ ዳኛ›› የሚባል ነገር እንደነበር የጠቆሙት የሕግ ባለሙያው፣ ዓቃቤ ሕግና ዳኛ አንድ ላይ ተቀምጠው የሚገማገሙበት ሥርዓት እንደነበር አስረድተዋል፡፡

‹‹ዓቃቤ ሕግ እከሌ የተባለውን ተከሰሽ ዋስትና አትስጠው እያልኩህ ፈቀድክለት፤›› በማለት ቅሬታውን በማሰማት፣ ዳኛው ሒሱን ውጦ ይቅርታ እንዲጠይቅ ይደረግ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

ዳኛ ከምንም ነገር ነፃ ሆኖ ማሰብ እንዳለበት፣ ተጠርጣሪን ውሸታምና አጭበርባሪ አድርጎ ከማሰብ ይልቅ ዓቃቤ ሕግ በማስረጃ እስሚያረጋግጥበት ድረስ ‹‹ነፃ›› አድርጎ ማሰብ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ አለበለዚያ ፍርድ ቤቶች የሕዝብን አመኔታ እንደሚያጡ በቅርቡ የታየ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ማረሚያ ቤቶችን እሳቸው ወህኒ ቤቶች ብለው እንደሚጠሯቸው የገለጹት አቶ ሙሉጌታ፣ እንዴት አሳዛኝ ነገር ይፈጸምባቸው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ሌላው ሌላው ቀርቶ አንዲት ልጇ የታሰረባት እናት ከክፍለ አገር ድረስ ተጉዛ መጥታ አንድ የማረሚያ ቤት ፖሊስ ‹‹አይቻልም›› ሲላት የሚሰማትን ሁሉም ተሳታፊዎች እንዲያስቡት ጠይቀዋል፡፡ ‹‹መታወቂያ ረስታ ሊሆን ይችላል፣ ወይም ሰዓት ረፍዶባት፣ ወይም ዝም ብሎ፤›› ብለው፣ ይኼ ተገቢና የሕግ መሠረትም እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ አንድ ተጠርጣሪ በቤተሰቡ፣ በጓደኞቹ በጠበቃውና በሃይማኖት አባቱ እንዲጠየቅ የሰጠውን መብት ማሳጣትም ሕግን አለማክበር መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡ የዛሬ ባለሥልጣናትን፣ ‹‹እባካችሁ እባካችሁ፣ ዕድሜ ልካችሁን በሥልጣን ላይ እንደማትኖሩ እወቁት፤›› ካሉ በኋላ፣ አንድ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ሥልጣን ላይ የነበሩ ባለሥልጣን፣ በወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ግራና ቀኝ የሚባለው ግራ ሲገባቸው፣ ‹‹ይች አገር ወዴት እየሄደች ነው?›› በማለት የጠየቁት ለሁሉም አስተማሪ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

 

/ሪፖርተር

 

 

%d bloggers like this: