ዴሞክራሲያዊ መብት በኢትዮጵያ ‘ለውጭው ዓለም መታያ እንጂ ሥራ ላይ አልዋለም’—ምሁራን

11 Aug

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

 

ነሃሴ 5/2011 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት እውን እንዲሆን የሃሳብ ነጻነት ከገደብ ሳያልፍ መተግበር እንዳለበት ምሁራን ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ በሕገመንግስቱ አንቀፅ 29 የተቀመጠው ሀሳብን የመግለፅ ዴሞክራሲያዊ መብት ላለፉት ዓመታት “ለውጪው ዓለም መታያ እንጂ ስራ ላይ አልዋለም” ይላሉ።

ከአንድ ዓመት ወዲህም ለውጡ  ከመጣ  በኋላ ግን በተወሰነ ደረጃ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጅማሮ ማሳያ የሚሆን የምህዳር መስፋት እየተስተዋለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር እዮኤል ዳንኤል፤ በኢፌዴሪ ህገመንግስት ውስጥ በመርህ ደረጃ ዜጎች ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሀሳባቸውን የመግለፅ መብት አላቸው ብለዋል።

በአንቀፅ 29 መሰረትም ማንኛውም ዜጋ ሀሳቡን በማህበራዊ ሚዲያም ይሁን በሌላ መንገድ ያለ ቅድመ ምርመራ የማስተላለፍ መብት የተሰጠው ቢሆንም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሲባል ግዴታዎችም መቀመጣቸውን ነው የሚጠቅሱት።

አሁን ላይ ሰዎችን የማዋረድ እና ሰብዓዊ ክብርን ዝቅ የሚያደርጉ  መልዕክቶች እየተሰራጩ መሆኑን ያነሱት የህግ ምሁሩ፤ ድርጊቱ ህገመንግስታዊ ድንጋጌን የተላለፉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይህም የዴሞክራሲያዊነት መገለጫ ሳይሆን ፅንፍ የረገጠ፤ ከባህል ያፈነገጠ የእሴት መሸርሸርን የሚያሳይ ነው ይላሉ።

መንግስት ብዙ ጊዜ እርምጃ ሲወስድ ለራሱ ያዳላል ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፤ በህገመንግስቱ የተጻፈው እና ስራ ላይ የሚውለው ላላፉት ዓመታት ሲጋጭ እንደነበርም አንስተዋል።

ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ ዴሞክራሲያዊ መብት አተገባበር በቂ ደረጃ ላይ አለመድረሱን የተናገሩት ፕሮፌሰሩ፤ ጋዜጠኞች ነጻ እንዳልወጡና ሚዛናዊ እንዳልሆኑ የሚያንጸባርቁ ዘገባዎችን ሲሰሩ ይስተዋላል ብለዋል።

የተወሰኑ መገናኛ ብዙሃን እና ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያሉ ሰዎች ደግሞ “እንደ ኳስ ሜዳ ደጋፊ የኔ ቡድን ይህን አለ፤ ያ ቡድን እንዲህ ሆነ፤ እያሉ ቤንዚን እያርከፈከፉ ነው” ብለዋል።

ሚዲያዎቹና ግለሰቦቹ ከዚህ ድርጊታቸው ታቅበው አዎንታዊ ጉዳዮች እንዲጠናከሩና ህዝቡ የሚጠቅመውን ሀሳብ እንዲያገኝ  በነጻነት ስም ገደብ ሳያልፉ  በሚዛናዊነት መስራት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

“የፖለቲካ ሃይሎችን የሚያቀራርብ ብሔራዊ መግባባት አለመፈጠሩ ለዴሞክራሲ ፀር ከመሆኑም ባለፈ እርስ በእርስ እየተጠላለፍን ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

መምህር እዩኤል እንዳሉት ደግሞ ብሔራዊ ጥቅምና ሀገራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥል፣ ወጣቶችን ወደ ጥፋት የሚመራ ይዘት ያላቸው ጽሁፎች በህገመንግስቱ ተከልክለዋል።

በአሁኑ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት የሞቱ ሰዎች ሳይቀር ቤተሰባቸውን በጣም ሊጎዳ በሚችል ደረጃ ሀሳቦች ስቀርቡ እንደሚስተዋል ገልጸው፤ ይህ ከህግ ባለፈ ከባህልና ከማህበራዊ የሞራል እሴቶች ያፈነገጠ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለያዩ መንገዶች እየተንጸባረቁ ላሉ የእርስ በእርስ ግጭትና ጥላቻ  መነሻ አንዱን ጨቋኝ ሌላውን ተጨቋኝ በማድረግ ሲነገር የኖረው ትርክት ነው ብለዋል።

ፕሮፌሰር መረራ በበኩላቸው በተጻፈው እና ስራ ለይ በሚውለው መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳይኖር ጋዜጠኞች፣ መንግስት እና ሌሎች ህግን የሚያስከብሩ አካላት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል።

የጥላቻ ሀሳብ የበዛበት የፖለቲካ ሂደት ሀገርን የመበታተን እና የእርስ በእርስ እልቂት ያስከትላል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ከንጉስ  ሀይለስላሴ የመሪነት ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጥላቻ፣ መጠላለፍና መገዳደል የበዛበት መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ እዩኤል እንዳሉት አንደኛውን ማህበረሰብ ወዳጅ፣ ሌላውን እንደ ጠላት ፈርጀው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ  ሃይሎች ከሚያራርቅና ከሚያጋጭ ፕሮፓጋንዳ መራቅ አለባቸው።

“እነሱ እንዲህ አድርገውን ነበር አሁን ደግሞ ተራችን የኛ ነው ይህን ማድረግ አለብን የሚል ቅኝትን በማስወገድ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ የፖለቲካ ጉዞን ማድረግ ይበጃል” ይላሉ።

ሰብዓዊ ክብርን የሚነካ፣ ባህልን የሚያንቋሽሽ መግለጫ እና መልዕክትን ለመከላከል  በስራ ላይ ያለውን የወንጀለኛ መቅጫ ህግና እየተረቀቀ ያለውን የፀረ ጥላቻ ህግ ወደ ተግባር ማስገባት አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል።

ደሞክራሲን እየተለማመደች ባለች ሀገር ውስጥ መንግስት ሆደ ሰፊና ታጋሽ መሆን አለበት ያሉት የህግ ምሁሩ፤ “ሰዎች በጻፉ ቁጥር ቅድመ ምርምራ ከማድረግና  ያለ አሳማኝ ማስረጃ” ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠብም መክረዋል።

ሀገሪቱን እየመራ ያለው መንግስት ለዴሞክራሲ ስርዓት መገንባት ካለፉት ችግሮች በመማር ከኢትዮጵያ ህዝብና ከፖለቲካ ሃይሎች ጋር ተቀራርቦ መነጋገር እንዳለበት ነው  ፕሮፌሰር መረራ የሚመክሩት።

መንግስት “ትችቶች ሲቀርቡበት በአትንኩኝ ባይነት ለማፈን እና ለማሰር መሞከር” እንደሌለበት የመከሩት ፕሮፌሰር መረራ ቅድሚያ ለህዝብና ለሀገር ጥቅም እንዲሰራም ነው የጠየቁት።

የተሻለ የፖለቲካ ስርዓት እንዲፈጠር በርን ክፍት በማድረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን በሀቅ መጀመር እንደሚያስፈልግ ተናግረው፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ሃይሎችም ከማን ምን እንደሚጠበቅ በመለየት ለሀገር ግንባታ ጠቃሚ ተግባር ማከናወን እንደሚገባቸው ነው የመከሩት፡፡

%d bloggers like this: