ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፏን ለውጭ ባለሃብቶች ለመክፈት ፍንጭ የሰጠችበት ጅማሮ

14 Aug

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

 

ሥራውም የተለያዩ ኩባንያዎች የሚያስፈልጋቸውን ግዙፍ ማሽኖች በኪራይ ማቅረብ ወይንም የፋይናንስ ሊዝ አገልግሎት መስጠት ነው።

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 8፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሃብቶች ዘግታው የነበረውን የፋይናንስ ዘርፏን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ከፈት አድርጋለች ያስባለላትን ፈቃድ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መስጠቱ ተሰምቷል።

ኢትዮ ሊዝ ወይንም “ኢትዮጵያን ካፒታል ጉድስ ፋይናንስ አክስዮን ማህበር” ይባላል ይህ ኩባንያ፤ መሰረቱን አሜሪካ ባደረገ “አፍሪካ አሴት” በተባለ ኩባንያ አማካኝነት የተቋቋመ አክስዮን ማህበር ነው።

ስራውም የተለያዩ ኩባንያዎች የሚያስፈልጋቸውን ግዙፍ ማሽኖች በኪራይ ማቅረብ ወይንም የፋይናንስ ሊዝ አገልግሎት መስጠት ነው።

አክስዮን ማህበሩ የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ እንዲህ አይነት አገልገሎት ለመስጠት የሚጠየቁትን የ400 ሚሊየን ብር ካፒታል አሟልቶ ነው የመጀመርያ ደረጃ ፍቃድ የተሰጠው ።

ስለ ኩባንያውና ሊሰጥ ስላሰበው አገልግሎቱ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮ ሊዝ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ግሩም ጸጋዬ አክሲዮን ማህበሩ ዓላማው የካፒታል ቁሳቁስ የሚባሉ ከፍተኛ ማሽነሪዎችን አምጥቶ ማከራየት መሆኑን አስረድተውናል።

ለምሳሌ ለግብርናው ዘርፍ የሚሆኑ ትራክተሮች፣ ኮምባይነሮች፤ ለጤናው ዘርፍ እንደ ኤም አር አይ እና ሲቲ ስካንን የመሳሰሉ፣ በግንባታው ደግሞ ኤክስካቫተሮች፣ የማምረቻ ማሽነሪዎች እና ጀነሬተሮችን የመሰሉ እቃዎችን ከውጭ በማምጣት ለረዥም ጊዜ የሚያከራይ መሆኑን ነው የጠቆሙት።እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚው ከሆነ ኢትዮ ሊዝ በሚያከናውናቸው የማሽን ክራይ አቅርቦቶች በሀገሪቱ በተደጋጋሚ የሚከሰት የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በራሱ በኩል ታሳቢ ያደረገ ነው ።

አክስዮን ማህበሩ በውጭ ሀገር ኩባንያ በዋናነት የተቋቋመ በመሆኑ ባለ አሰራር መሰረት ከሀገር ውስጥ ባንኮች ብድርን ማግኘት አይችልም ።የራሱ ገንዘብ በውጭ ምንዛሬ የሚጠቀመው ነው ።

ስለዚህም የሀገር ውስጥ ማሽን ፈላጊዎች ለኩባንያው ለማሽናቸው በኢትዮጵያ ብር መክፈል ነው የሚጠበቅባቸው ፤ አከራዩ ኩባንያ ደግሞ ከሀገር ውስጥ የውጭ ምንዛሬ ሳይጠይቅ በራሱ የውጭ ምንዛሬ ያቀርብላቸዋል።

ለዚህ ስራው ደግሞ አሁን ላይ ያስመዘገበው ካፒታል ብዙም የሚያወላዳ ባለመሆኑ አሁን ላይ 400 ሚሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገበው ኩባንያው በቀጣይ ሁለት አመታት 200 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያፈስ እና ሁሉም ኢንቨስትመንት የሚመጣውም ከውጭ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

አካሄዱ በተባለው መልኩ ተግባራዊ ከሆነ ሀገሪቱ ባላት የውጭ ምንዛሬ ላይ ተጽእኖ ሳያሳርፍ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልጉ የካፒታል እቃዎችን በግሉ ዘርፍ አጋርነት ማስገባት ይቻላል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ማሽኖችን የሚፈልጉ የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ከፈለጉ ለፈለጉት አለማ ተጠቅመው የሚመልሱበት፤ ካልሆነ ደግሞ በሂደት ባለቤት የሚሆኑበትን ሁኔታንም የሚፈጥር ነው ይላሉ የእቃው የኢኮኖሚ ቆይታ ተሰልቶ የሊዝ ክፍያውን ካጠናቀቀ በኋላ ስሙ ወደ ተከራዩ የሚዛወርበት አማራጭ እንዳለ በማስረዳት።

ኢትዮጵያን ካፒታል ጉድስ ፋይናንስ አክስዮን ማህበር የመጀመርያ ደረጃ ፍቃዱን ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ካገኘ በሁዋላ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? ያልናቸው ዋና ስራ አስፈጻሚው አሁን ላይ ወደ ስራ ግቡ የምትለውን ሁለተኛ የበሄራዊ ባንክ ፍቃድ እየተጠባበቀ መሆኑን በመግለፅ ብዙ ማሽን ፈላጊዎች ከወዲሁ ጥያቄ እያቀረቡ ከተለያዩ ኩባንያዎች ጋርም የመግባበቢያ ስምምነት መፈረሙን አስረድተዋል።

ስራው በውጭ ምንዛሬ እጦትም ሆነ በምንም ምክንያት የካፒታል እቃዎች በመዘግየታቸው ምክንያት የሚፈጠሩ የፕሮጀክት መጓተቶችን እንደሚያስቀርና ትላልቅ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ወደ ስራ ገብተው የስራ እድል እንዲፈጥሩ እንደሚያግዝም አንስተዋል።

 

 

%d bloggers like this: