የደቡብ ክልል የአደረጃጀት ጥናት አስመልክቶ ሲካሄድ የቆየው ውይይት ባለሰባት-ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ

17 Aug

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 10፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ክልል የአደረጃጀት ጥናት አስመልክቶ ሲካሄድ የቆየው ውይይት ሰባት የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ፡፡

የደኢህዴን ከክልል ውጪ አደረጃጀት አመራሮች መድረክ ባለፉት ቀናት በአዲስ አበባና አዳማ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

በማጠናቀቂያም የጉባኤው ተሳታፊዎች ያወጡት ሰባት የአቋም መግለጫ እና ወቅታዊ ጉዳዮች እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ከክልል ውጪ የደኢህዴን አመራሮች ላለፉት አራት ቀናት ስናካሂድ የነበረውን የግምገማ መድረክ በወቅታዊ ክልላዊና ሀገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮች እንዲሁም በክልሉ በተነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎች ዙሪያ በተጠናው ጥናት ላይ በዝርዝር ተወያይተናል፡፡

የክልሉ መሪ ድርጅት ደኢህዴን የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን አስተባብሮ መምራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በክልሉም ሆነ በሀገር ደረጃ በሁለንተናዊ መስኩ በርካታ የስኬት ታሪኮችን በደማቅ ቀለም መፃፍ የቻለ ድርጅት ነው፡፡

ደኢህዴን በመሪነት በቆየባቸው ዓመታት ብዝሃነት የልዩነት እና የግጭት ሰበብ እንዳይሆን በማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ ብዝሃነትን በብቃት መምራት እንደሚቻል፤ እንዲሁም ህብረብሄራዊ ክልል በመመስረት በተሞክሮነት የሚጠቀስ ስራ የሰራ፤ ህዝቦችን ለአንድ የልማት አላማ በማንቀሳቀስና በማሰለፍ ደቡባዊ የሆነ አዲስ ማንነትና ስነልቦና በመገንባት ሂደት በክልሉ አያሌ የልማት፤ የሰላም፤ የዴሞክራሲ ስኬቶችን አስመዝግቧል፡፡

ደኢህዴን በሀገራችን ኢትዮጵያ በተጀመረው የለውጥ እና የሪፎርም እንቅስቃሴ ሂደት ተዋናይ ከመሆን በሻገር ባለቤትና የግንባር ቀደምትነት ሚና የተጫወተና ይህንን ሚናውን በቀጣይነት ለማጎልበት ቁርጠኝነት የወሰደ ድርጅት ነው፡፡ ይህንንም አቋሙን በተለያየ መንገድ የለውጡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በተግባር እያሳየ ይገኛል፡፡

መሪ ድርጅቱ ደኢህዴን የደቡብን ህዝብ ከጎኑ በማሰለፍ ባለፉት አመታት በሃገር አቀፍ ደረጃና በክልሉ ውስጥ በለውጡ ሂደት የነበውን አኩሪ ሚና በአግባቡ በማስቀጠል በኩል የነበረው ጥንካሬ እንዳለ ሆኖ ጉድለቶችም በስፋት አጋጥመውታል፡፡

በክልልና በሃገር ደረጃ እየገጠሙ ያሉ ችግሮች ለመቅረፍና የክልሉን ህዝብ ጥያቄዎች ለመመለስ ርብርብ በሚያደርግበት ወቅት ከውስጥም ከውጪም በተደራጀ መልክ የድርጅቱን ሚና አሳንሶና አንኳሶ የመመልከት ፤ በለውጡ ሂደት የነበረውንንና አሁንም እያበረከተ ያለውን ሃገራዊ አስተዋፅኦ ከግምት በታች አድርጎ ለማሳየት የመሞከር ችግር እየተስተዋለ መሆኑን አመራሩ አፅንኦት ሰጥቶ ገምግሟል፡፡

ደኢህዴን ካስመዘገባቸው ስኬቶች ባሻገር በርካታ ፈተናዎችን እየተጋፈጠና በፈተናዎች ውስጥ እያለፈ የመጣ ድርጅት ነው፡፡ በተለይም የክልሉን ህዝቦች አንድነትና የጋራ ጉዞ ብሎም የገነቧቸውን እሴቶች የሚፈታተኑ ከድርጅታዊ ዲሲፕሊን መጓደል የሚመነጩ የአመራር ችግሮች እንዲሁም ለደረስንበት መድረክ የሚመጥን መዋቅራዊ ችግሮች ድርጅቱን ባለፉት አመታት ከተፈታተኑት ውስጥ በዋነኝነት ጎልቶ የሚጠቀስ ነው፡፡

በክልሉ ውስጥ ህዝቦችን ለከፍተኛ ቅሬታ ያጋለጡ የኢ-ፍትሃዊነት ፤ያለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌዎችና የጥቅም ትስስሮች ብሎም በአሁን ሰአት በስፋት እያቆጠቆጡ የመጡ የህዝበኝነትና የአክራሪ ብሄርተኝነት አዝማምያዎች እና በተደራቢነት በድርጅቱ ውስጥ እነዚህን ችግሮች በቁርጠኝነት እና በመርህ ላይ ቆሞ ለመታገል ያለ ፅናት እና ዲሲፕሊን መጓደል የፈጠረው ህዝቦችን ለተደራራቢ ቅሬታ ማጋለጡን ብሎም አላስፈላጊ ዋጋ ማስከፈሉን አመራሩ በሃላፊነት ስሜት ገምግሟል፡፡

መሪ ድርጅቱ ደኢህዴን በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥም ሆኖ ከሂደቶቹና፤ ጉድለቶች እየተማረና ፤ከህዝቦች ጋር በዘላቂነት እየተመካከረ ፤ ችግሮችን በብቃት በመሻገር ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ዛሬም የገጠሙት ፈተናዎች ድርጅቱን ሊታደጉ በሚችሉ ብርቱ የህዝብ ልጆች ብሎም በመላው የደቡብ ህዝቦች ርብርብ ነገን የተሻለ ለማድረግ ተስፋ የተጣለበት ድርጅት ነው፡፡

በደኢህዴን መሪነት በህዝቦች አንድነት እና የአብሮነት ጉዞ የተገኘው አኩሪ ታሪክ ብሎም የህዝቦችን መተማመን እየሸረሸረው የሚገኘውን የኢፍትሃዊነት እና የአድሎአዊ አሰራር ፤የጎሰኝነት እና የህዝበኝነት ችግሮች፤ በዋነኝነት በተጠናከረ ድርጅታዊና ህዝባዊ ትግል ብሎም አዳዲስ ሳይንሳዊ አሰራሮችንና መፍትሄዎችን በመተግበር መዋቅራዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታትና አብሮነትን ማስቀጠል እንደሚገባ አመራሩ በትኩረት ገምግሟል፡፡

የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም ከህግ የበላይነት ጋር በተያያዘ በክልሉ እያጋጠሙ ያሉ የሰላምና የፀጥታ ችግሮችን በፍጥነት መቅረፍ እንደሚገባ፤ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ማረጋገጥ እና በፍጥነት ወደ ልማት ስራዎቻችን መመለስ ፤ ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ገምግሟል፡፡

በዚህ ሂደት በክልሉ የታዩ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ሁኔታና የህዝቦችን በሰላም የመኖር ህገመንግስታዊ መብት በመጣስ ህገወጥነት እንዲሰፍን የሚደረጉ ማንኛውም እንቅስቃሴ በማስተካከል የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑንም መተማመን ላይ ተደርሷል፡፡

አመራሩ በግምገማው ህገወጥነት እንዲስፋፋና የዜጎችን በሰላም መኖርና የመዘዋወር መብት አደጋ ላይ የጣለ ድርጊት እንዲፈፀም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሚና የነበራቸው አመራሮች መኖራቸው ሁኔታውን ይበልጥ እንዲወሳሰብ እንዳደረገ የገመገመ ሲሆን በቀጣይነትም በዚህ ድርጊት በተሳተፉ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃና የማስተካከያ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባም ቁርጠኛ አቋም ወስዷል፡:

ድርጅቱ በለውጡ ሂደት ምላሽ የሰጠባቸው በክልሉ ውስጥ ይነሱ የነበሩ የአደረጃጀት ጥያቄዎች ዙርያ የተደረገው እንቅስቃሴ መልካም ጅምር መሆኑን የገመገመ ሲሆን በተለይም በድርጅቱ 10ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ የክልል እንሁን ጥያቄዎችን ለመፍታት የማህበራዊ ሳይንስ ጥናት ዘዴዎችን የተጠቀመ ጥናት ላይ የተመሰረተ (Informed decision) እንደሚያካሂድ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የተደረገው ጥናት ላይ በዝርዝር ተወያይቷል፡፡

ጥናቱ ፍፁም ሳይንሳዊ፤ ገለልተኛና ሁሉንም የሚጠቅም (win win) መፍትሄዎች የተቀመጡበት መሆኑንና የህዝቦችን ፍላጎት ያንጸባረቀ ወደ ትክክለኛ መፍትሄ የሚወስደውን አማራጮች ከጥቅሙና ጉዳቱ ጋር ያመላከተ ከመሆኑም ባሻገር ጥያቄዎቹንም በዘላቂነት ለመፍታት በሚያግዝ አግባብ መመራቱንም አረጋግጧል፡፡
በመሆኑም በዚህ ጥናት ዙርያ ቀጣይነት ያለው የህዝብ ውይይት በማካሄድ ይበልጥ የሚዳብር እና የተሻለ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚገባ አስምሮበታል፡፡

በዚህ ወቅት ከክልል ውጪ በሚኖረውም አገራዊ ሚናም የደኢህዴን አመራርና አባላት ከሌሎች እህት ድርጅቶች ጋር በመሆን የተጀመረው የለውጥ ሂደት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆንና የሃገራችን ህዝቦች ህይወት በተጨባጭ እንዲቀይር ደኢህዴን ሚናውን ማጎልበት እንደሚኖርበት ታይቷል፡፡

በተለይም በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዙርያ በተጀመሩ መጠነ ሰፊ የሪፎርም እንቅስቃሴዎች፤ የህዝቦችን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በሚሰሩ ሁሉን አቀፍ ተግባራት ብሎም ፤የኢኮኖሚውንና የልማት እንቅስቃሴውን ለማሳደግ በተጀመሩ ተግባራት ዙርያ የግንባር ቀደምትነት ሚና በመጫወት የኢትዮጵያውያንን የጋራ ራእይ እውን እንዲሆን የደኢህዴን አመራርና አባላት ሚና ከፍተኛ መሆን እንደሚኖርበት ገምግሟል፡፡

ከዚህም በመነሳት እኛ የዚህ መድረክ ተሳታፊ አመራሮች በወቅታዊ ሀገራዊ እና ክልላዊ ሁኔታዎች እንዲሁም በክልሉ የሚነሱ ተጨማሪ ክልል ሆኖ የመደራጀት ጥያቄዎች ላይ ጊዜ ወስደን በጥልቀት፤ ኃላፊነት በተሞላበትና በሰከነ ሁኔታ የመከርን ሲሆን የሚከተሉትን ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡

1. እኛ የደኢህዴን ከክልል ውጪ ያለን አመራሮች የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ የህዝባችንን ፍላጎት ብሎም የሀገራችንን ትንሳኤ የሚያረጋግጥ በመሆኑ የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎች በተሳካ ሁኔታ እንዲፈጸምና ህዝባችንም ከለውጡ ትሩፋቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያለንን ጊዜ፣ ጉልበት፤ እውቀትና አቅም ሁሉ አሟጠን መጠቀም እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ በዚህም ሂደት ለውጡ እያጋጠሙት ያሉት ተግዳሮቶች እና አፍራሽ አስተሳሰቦች መላው የድርጅታችን አባላትና አመራሮችን እንዲሁም መላውን ህዝቡ አሰልፈን ለመታገል ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን፡፡

2. ድርጅታችን ደኢህዴን በርካታ አኩሪ ታሪኮችን ያስመዘገበ በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ማንነቶችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ጥቅሞችን አጣጥሞ፤ እውነተኛ ህብረብሄራዊ ክልል ፈጥሮ ፤ለጋራ አላማ የመራ የስኬት ተምሳሌት የሆነ ድርጅት ነው፡፡ እንዲሁም በአገራችን ለመጣው የለውጥ ሂደት ጉልህ ሚና የተጫወተ ድርጅትም ነው፡፡

ይህ ሆኖ ሳለ ድርጅቱን መሰረት አድርገው ከውስጥም ከውጪም የሚንፀባረቁ የተሳሳቱና የተንሻፈፉ አመለካከቶች ትክክለኛ ያልሆኑና ድርጅቱን የማይገልፁ ብሎም ከድርጅቱ ጀርባ ሆነው የታገሉና ያታገሉ እልፍ አእላፋትን ክብር የሚነኩ ናቸው፡፡

በመሆኑም እነዚህን ከውስጥም ሆነ ከውጪ ድርጅቱን ለማዳከምና ለመበተን የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን መላውን አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ህዝባችንን አስተባብረን ያለምህረት እንታገላለን!!

3. በክልሉ ውስጥ የሚታዩ የህገወጥነት አዝማማያዎች እና ድርጊቶች በፍጥነት መልክ ሊይዙና የህግ የበላይነት በሁሉም አካባቢዎች ሊሰፍን የሚገባ ሲሆን የዚህ ችግር ዋነኛ መንስኤ የውስጥ ችግሮቻችን መሆኑን ተግባብተናል፡፡

በሂደቱም ከድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ በየደረጃው ያለው አመራር ድርሻ ሰፊ መሆኑም ታይቷል፡፡ ስለሆነም በመብት ጥያቄ ሽፋን የሚደረጉ የትኛውንም ህገወጥ እንቅስቃሴዎች ፤ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችን ስርዓት ለማስያዝ እንዲሁም የህዝቦችን ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ ብሎም የህግ የበላይነትን ማስከበር ለድርድር የማይቀርብ በመሆኑ በዚህ መድረክ ተሳታፊ የሆንን አመራሮች ፤ በዚህ እንቅስቃሴ ዙርያ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅና ፤ህጋዊነትን አስፍኖ የተረጋጋ ክልላዊ ሁኔታን ለመፍጠር በሁሉም አቅጣጫ ጠበቅ ያለ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ስራ እንዲሰራ ቁርጠኛ አቋም ወስዷል፡፡ ለዚህም ተግባራዊነት ሁሉም አመራር የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን እናረጋግጣለን!

4. በክልሉ ህዝባችንን ለከፍተኛ ቅሬታ ያጋለጡ፤ የኢፍትሃዊነት ችግሮች ሲሆኑ በተለይ የመልካም አስተዳደር እና የአመራር ሥርዓታችን ላይ የሚታዩ ጥያቄዎች መሆናቸውን አመራሩ ገምግሟል፡፡

በመሆኑም የኢፍትሃዊነት የመልካም አስተዳደር እና ተያያዥ ችግሮችን በመሰረቱ መፍታት እንደሚያስፈልግ የጋራ መግባባት ላይ የደረስን ሲሆን የሁሉንም ህዝቦች እኩል ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት የማያረጋግጡ አሰራሮች፤ መመርያዎች እና ልማዶች ከማስተካከልም ባሻገር በውስጣችን ያሉ የኢፍትሃዊነት ችግሮችን ለማረም በከፍተኛ ቁርጠኝነት ልንታገል እንደሚገባ በጋራ ወስነናል፡፡

እንዲሁም በውስጣችን እየታየ የሚገኘውን የህዝበኝነት ብሎም የጎሰኝነት ችግሮች ለመቅረፍ መላውን መዋቅራችንንና ህዝቡን በማንቃትና በማሳተፍ ቀጣይነት ያለው ጠንካራ ትግል ለማድረግ በቁርጠኝነት እንነሳለን፡፡

5. በክልል የመደራጀት ጥያቄን በተመለከተ የህዝቦች ህገ-መንግስታዊ መብት መሆኑን አመራሩ ተወያይቷል፡፡ ሆኖም ድርጅቱ ጥያቄዎቹን ለማስተናገድ የመረጠው መንገድ ሁሉንም የሚጠቅምና የጋራ መፍትሄ የሚያመጣ ሲሆን ይህ ዓይነቱ ጥያቄ በአገር ደረጃ አዲስ በሆነበት ሁኔታ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መጠናቱና የህዝቡን ፍላጎት ያማከለ አቅጣጫን መከተሉ ይበልጥ ተአማኒና ትክክለኛ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡

ስለሆነም በየደረጃው መላው ህዝብ ምክክርና ውይይት የሚያደርግበት ሆኖ በአንድ በኩል በጥናቱም የተገኘውን የክልሉ ህዝቦች አንድነት እና የጋራ እሴቶች ባከበረ በሌላ ጎኑ ደግሞ የጉባኤውን ውሳኔ ተግባራዊ ባደረገ መንገድ ለመምራት ተስማምቷል፡፡ ለዚህም ተግባራዊነት በሃላፊነት መንፈስ ለመንቀሳቀስ ቃል እንገባለን!

6. እኛ ከክልል ውጪ የምንገኝ የደኢህዴን አመራሮች እንደ ወትሮው ሁሉ ከኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ጋር በመሆን መርህንና የድርጅት ዲሲፕሊን በጠበቀ መንገድ በሃገራችን የተጀመረው ለውጥ ወደ ላቀ ከፍታ ለማሸጋገር ፤ እየገጠሙን ያሉ ሃገራዊ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት፤ እንዲሁም ከህዝባችን የሚነሱ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎችን ኢህአዴጋዊ አንድነታችን በሚያጠናክር መንፈስ ለመመለስ በጋራ እንደምንሰራ ቃል እንገባለን፡፡

7. እኛ የደኢህዴን አመራሮች በህብረ-ብሔራዊነት ላይ እየተገነባ ያለው የፌዴራል ሥርዓት ይበልጥ እንዲጎለብትና እንዲጠናከር በሂደቱ የታዩ ተግዳሮቶችን በማረም ሀገራችን በደረሰችበት የዕድገት ደረጃ የመድረኩን ጥያቄዎች በሚመልስ አግባብ ለፌዴራል ሥርዓቱ ይበልጥ መጎልበትና ቀጣይነት የምንታገል መሆኑን አቋም ወስደናል፡፡

ከሁሉ በላይ በብሄራዊ ማንነትና በኢትዮጵያዊ አንድነታችን መሃከል ያለውን ተገቢ ሚዛን በማስጠበቅ ህብረ-ብሔራዊ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ለማጎልበትና በህዝቦቿ የጋራ ጥረት ታላቅነቷን ለማረጋገጥ እየተጋች ያለችውን ሃገራችንን ለመገንባት እኛ በየደረጃው የምንገኝ አመራሮች ድርሻችንን ለመወጣት እንዲሁም በፅናት ለመታገል ቃል እንገባለን!

 

 

%d bloggers like this: