በትኩረት ሊታይ የሚገባው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የመስቀል በዓል መልዕክት!

28 Sep

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

“ኢትዮጵያን ታላቅ፣ የበለጸገችና ለሁላችንም እንድትሆን ለማስቻል የያዝነው ዓላማ መሳካቱ የማይቀር እውነት ነው፡፡ ይህን ዕውነት የሚገዳደሩ ኃያላን ይኖራሉ፡፡

ለጊዜው ዝናራቸውን እስኪጨርሱ፣ ጉልበታቸውንም እስኪያፈሱ ድረስ ያሸነፉ ይመስላሉ፡፡ ድምፃቸው እንደ ነጎድጓድ፣ ጩኸታቸውም እንደ ብዙ ፏፏቴዎች የወል ጩኸት ጎልቶ ይሰማ ይሆናል፡፡ እውነታችንን የቀበሩት መስሏቸው ለጊዜው ይደሰታሉ፡፡”

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ማን ያውቃል?

የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ፡፡
ማን ያውቃል?

እንዲል ኢትዮጵያዊው ባለቅኔ – እኛና መስከረም፤ እኛና መስቀልም ዓመት ጠብቀን የምንገናኝ ተነፋፋቂ ባለ ቀጠሮ ነን፡፡

እናም ናፍቆታችንን እንወጣጣ- ፍቅራችንንም እንቀባበል ዘንድ ዓመት ጠብቀን አደባባይ እንወጣለን – ያኔ ደመራ ነው፡፡

የመስቀል በዓል በአደባባይ ከሚከበሩ የኢትዮጵያውያን በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡

ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ይህንን ታላቅ በዓል በዐደባባይ እንድናከብረው ሥርዓት ሲሠሩ ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡

ከበዓሉ ጋር የተያያዙ ሦስት ታላላቅ ሐሳቦችን ሁላችንም እንድንመራባቸው ፈልገው ሳይሆን አይቀርም፡፡

እውነትን ቀብሮ መኖር እንደማይቻል፤ ታሪክ የሚለወጠው በቆራጥነትና በአንድነት መሆኑን፣ አንድ ታላቅ ሐሣብ ኢትዮጵያውያንን እንዲጠቅም ከፈለግን ሐሣቡን ኢትዮጵያዊ ማድረግ እንዳለብን በዓሉ በደመራው ብርሃን ወገግ አድርጎ ያሳየናል፡፡

የክርስቶስን መስቀል የቀበሩት ሰዎች እውነትን ለዘለዓለም ቀብረው ማስቀረት የሚችሉ መስሏቸው ነበር፡፡

ለጊዜው መስቀሉ ከአፈር ሥር ሲቀበር ዓላማቸው የተሳካላቸው መስሏቸው ነበር፡፡

በመስቀሉ ላይ የቆሻሻ ክምር እንዲከመር ሲያደርጉ መስቀሉን ከታሪክ ገጽ ያጠፉት መስሏቸው ነበር፡፡

ይህ ግን የመሰላቸውን መስሎ መቆየት የቻለውና የዋሆችም መስቀሉ ተቀብሮ፣ ተረስቶ፣ ትቢያ ሆኖ ጠፍቷል ብለው እንዲረሱት ያስቻላቸው ዕሌኒ የምትባል ብርቱ እንስት ከተለየ ብርታት፣ ጽናትና የይቻላል መንፈስ ጋር እስክትከሠት ድረስ ብቻ ነበር፡፡

በየዘመናቱ እውነትን ለመቅበር የሞከሩ ነበሩ፡፡ በተንኮል፣ በሤራ፣ በግጭት፣ በክፍፍል፣ በጦርነት፣ በጉልበትና በኃይል እውነትን ለመቅበር ብዙዎች ሞክረዋል፡፡

እውነተኞችን በማጥፋትና በመግደል፣ በማሠርና በማስፈራራት እውነት የምትጠፋ መስሏቸው ብዙ ደክመዋል፡፡

መጻሕፍትን አቃጥለዋል፤ የዕውቀት ቦታዎችን አውድመዋል፡፡

እውነት ግን ብትቀጥንም አትበጠስም፡፡ እውነተኞችን በመግደልና በመቅበር በፍጹም እውነትን ማጥፋት አይቻልም፡፡ እውነትና ተስፋ አብረው የሚሄዱ ናቸው፡፡

እውነተኞች ተስፈኞች ናቸው፡፡

ውሸተኞች ጨለምተኞች ናቸው፡፡

ከእውነት ጋር ያልቆመ ሰው ተስፋ ሊኖረው አይችልም፡፡

ተስፋ እውነተኛ ሰው ብቻ የሚያደርገው መነጽር ነውና፡፡

ተስፋ ባለበት ሁሉ እውነት ትኖራለች — እውነት ባለችበትም እንዲሁ ተስፋ አለ፡፡

መስቀሉን የቀበሩት ሰዎች ሐሰተኞች ስለነበሩ ወደፊት የሚወጣ አልመሰላቸውም፡፡

የመስቀሉ ወዳጆች ግን እውነተኞች ስለነበሩ አንድ ቀን እንደሚገለጥ ያምኑ ነበር፡፡

ለዚህ ነው መስቀሉ የት እንደተቀበረ ከልጅ ልጅ በሚተላለፍ የቃል ትውፊት መረጃውን ለዘመናት አቆይተው ለመስቀሉ አስተርዕዮት ዘላለማዊ ገድል የፈጸሙት፡፡

ኢትዮጵያን ታላቅ፣ የበለጸገችና ለሁላችንም እንድትሆን ለማስቻል የያዝነው ዓላማ መሳካቱ የማይቀር ዕውነት ነው፡፡

ይህን ዕውነት የሚገዳደሩ ኃያላን ይኖራሉ፡፡

ለጊዜው ዝናራቸውን እስኪጨርሱ፣ ጉልበታቸውንም እስኪያፈሱ ድረስ ያሸነፉ ይመስላሉ፡፡ ድምፃቸው እንደ ነጎድጓድ፣ ጩኸታቸውም እንደ ብዙ ፏፏቴዎች የወል ጩኸት ጎልቶ ይሰማ ይሆናል፡፡ እውነታችንን የቀበሩት መስሏቸው ለጊዜው ይደሰታሉ፡፡

በዙሪያችን ያሉትም እውነታችን የተቀበረ መስሏቸው ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡

ይህ ግን የእውነትን ባሕሪይ ካለመረዳት የሚመጣ ነው፡ ፡

እውነትን መገዳደር እንጂ ማሸነፍ፣ መቃወም እንጂ ማጥፋት ፈጽሞ አይቻልም፡፡

የብዙዎች ጩኸት- የሰነፎች ተረትና የአላዋቂዎች ትምክህት ዕውነትን ሊያጠፋት እንደማይችል በጽኑ እናምናለን፡፡

ዕውነት የተቀበረችበትን አመድ እንደ ፍግ እሳት አሙቃ እንደ ገሞራ ትፈነዳለች፤ የተሸፈነችበትን አቧራና የክፋት ቁልል ቅርፊቱን እንደሚሰብር ጫጩት ፈንቅላ ትነሣለች፡፡ ነገ ከእውነተኞች ጋር ናት፡፡

እውነተኞች ዛሬ ጥቂቶች ቢመስሉም ነገ እየበዙ ይሄዳሉ፤ ሐሳውያን ዛሬ ብዙዎች ቢመስሉም ነገ እንደ ስንቅ እያነሡ ይሄዳሉ፡ ፡

====00000=====

 

እውነቱን ለመናገር፣ ሐሙስ ማምሻውን መስቀልን በበዓልነት የመጠበቅ ስሜቴ ደብዝዞ ነበር።

ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ስለበዓሉ አከባበር ፌዴራል ፖሊስ ያወጣው ረጋጭና ደፍጣጭ መገለጫው ነው።

ውስጤ በአንድ በኩል ግርግር ይኖራል፣ የፎከረ መንግሥትም እንዳለፉት ወራት ወደ ማሠር ይሂዳል። ሌላው ሥጋቴ ባንዲራ ይዘው የወጡ እልኸኛ ወጣቶች ይገደላሉ የሚል ፍርሃት ነበር!

ይህም የሃገራችንን ፖለቲካ፡ ወደ ጉልበተኝነት —አሁንም እንደምናየው፣ እንደው እንደው እየሆነ ስለሆነ ከለውጡ ወዲህ በዜጎችና ለውጡን በሚራምዱት ወገኖች መካከል የተገባው ቃል ላልቶ—የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶችን በምክንያታዊነት  መጣሱ ይባባሳል የሚል ፍራቻ ነው ውስጤን ሲገዘግዝ የነበረው!

በመሆኑም ከመተኛቴ በፊት ስሜቴንና ሃገራችን ያለችበትን ሁኔታ ያንጸባርቃል ያልኩትን ሐሙስ ማታ ባለሁበት በፊንላንድ አቆጣጠር 23 ሰዓት ላይ የሚከተለውን ትዊት አድርጌ ቀኔን ዘጋሁ።

 

የደመራ በዓል

እግዚአብሔር ይመሥገን እስካሁን ስማሁት —ከእሥር ውጭ— አንድም ዜጋ  የእምነቱን ምልክት ይዞ በመውጣቱ በፖሊስ አልተገደለም!

ለዚህም የሕዝቡን ጠንቃቃነትና ጨዋነት አደንቃለሁ!

ኢትዮጵያ እስካሁን ቁጥር ሥፍር ልጆቿን ገብራለችና በነዚያው ይብቃችሁ ይበለን! 

አርብ ወደምሽት አካባቢ ዉ ምን እያሉ ነው ብዬ ትዊተሮችን ስፈትሽ ይህንን 👇ተመለከትኩ!  

ዳዊት (አላውቀውም) ያለፈበት ሁኔታ በነበረኝ ስሜት ስቆቃውን ተካፈልኩት! መልዕክቱ ገጼ ሄዶ እንዲሠፍር አደረግሁት!

ከዚህ ባሻገር—በእኔ ዕይታ—የደመራ ምሽት ትልቁ ብርሃን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያስተላለፉት መልዕክት ይዘት ነው።

ከማን ጋር እንደሆነ ገሃድ ባያደርጉም፣ መንግሥታቸው ትልቅ ትንቅንቅ ውስጥ እንደሆነ ዛሬ ይፋ አድርገዋል።

 

አምነውበት ይሁን ወይንም ሕዝቡን ለማረጋጋት፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ይላሉ፦

“ኢትዮጵያን ታላቅ፣ የበለጸገችና ለሁላችንም እንድትሆን ለማስቻል የያዝነው ዓላማ መሳካቱ የማይቀር እውነት ነው፡፡

ይህን እውነት የሚገዳደሩ ኃያላን ይኖራሉ፡፡

ለጊዜው ዝናራቸውን እስኪጨርሱ፣ ጉልበታቸውንም እስኪያፈሱ ድረስ ያሸነፉ ይመስላሉ፡፡ ድምፃቸው እንደ ነጎድጓድ፣ ጩኸታቸውም እንደ ብዙ ፏፏቴዎች የወል ጩኸት ጎልቶ ይሰማ ይሆናል፡፡ እውነታችንን የቀበሩት መስሏቸው ለጊዜው ይደሰታሉ፡፡”

በተለይም መንግሥታቸው ያጋጠሙትን ችግሮች በመደመር፡ እውነትና ትዕግሥት መወጣት እንደሚያስፈልግ ያሠምሩበታል።

ለመሆኑ እነማን ናቸው እነዚህ አደናቃፊዎቻቸው?

በመስቀሉ ፍለጋ የትርክታቸው ማዕከል ያደረጓት ንግሥት ዕሌኒን ነው። ዕሌኒ ጠላቶቿ ከዓላማዋ እንዳያዛቧት ኃይሏን በእነርሱ መዝቀጥ ላይ አለማባከኗን ነው። ለዚህም እንዲህ ያብራሩታል፦

“[ዕሌኒ] በዚያ የመስቀል ፍለጋ ጉዞዋ፣ ክርስቲያኖችንም፣ አይሁድንም፣ ሌላ እምነት ያምኑ የነበሩትንም አስተባብራለች፡፡

መንገዷ የጥበብ እንጂ የመጥበብ አልነበረም፡፡

ጉዞዋ ሁሉንም ለእውነት ለማንበርከክ እንጂ አንዱን ለሌላው ለማንበርከክ አልነበረም፡፡”

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ኤኮኖሚ ውስጥ አስቸጋሪውና ገና ብዙ መፍታት የሚሻው የመደመር ትርጉም ነው! በፖለቲካም ሆነ በኤኮኖሚው መስክ የመደመር ችግር ምንም ተጨባጭ ነገር አለማበርከቱ ነው። ለምሣሌም ያህል በኤኮኖሚው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ቅርሶቿን ወደ ግል ባለሃብቶች ለማሸጋገር ፈጣን ዝግጅት በምታደርግበት ወቅት፣ ምንድነው የመደመር ኤኮኖሚክ ፖሊሲ ምሪት? መልሱ የለኝም!

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዛሬው መልዕክታቸው፥ “አንዴ ከምዕራብ፣ ሌላ ጊዜ ከምሥራቅ አምጥተን፣ ምሥራቁንና ምዕራቡን ለመሆን ጥረን ነበር፡፡ እየቀዳን የምናመጣው ዘር ግን በኢትዮጵያ ምድር ሊያፈራ አልቻለም፡፡” ይላሉ!

መልሳው የሚወስዱን እንደሚከተለው ወደ መደመር ነው፦

“ከምዕራብም ከምሥራቅም አየን፤ በጎ በጎው ወሰድን፤ የራሳችንን ሐሳብ አዋለድን፤ ከኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ፣ ፍላጎትና አቅም ጋር አዋህድን – ኢትዮጵያዊ የሆነ የመደመር መንገድንም ጀመርን፡፡”

በተጨባጩ እንደምናየው ከሆነ፡ ኢትዮቴሌን ለችርቻሮ የሚያበቃ አማካሪ ቡድን ኅዳር 1/2019 ለመቅጠር ማስታወቂያ አውጥተዋል!

ከዚህ ጽሁፍ በፊት ይህ ቅርሶቻችንን ግልጽ ባልሆነ መንገድ ለውጭም ሆነ ለሃገር ውስጥ ባለሃብት የሜተላለፉበት ሁኔታ ቢፈጠር፡ ሃገሪቱ ምን ያህል ተጠቃሚ ትሆናለች ለሚለው አወደ መደመር ጥጋቢ ማብራሪያና አቅጣጫ አይሠጥም። ለምሣሌ አርብ በገንዘብ ሚኒስቴር በተሠጠው መግለጫ ላይ አንድ ጥያቄ ስላለኝ በትዊተር እንደሚከተለው ይፋ አድርጌዋለሁ፦

እውነትን መያዝ፣ ትዕግሥትና ማቀፍ መልካም መርሆች ቢሆኑም፣ በአሁኑ ወቅት ሃገሪቱ በተጨባጭ በተለይም ኤኮኖሚክ ፖሊሲዋን መሬት የረገጠ ማድረግ ያስፈልጋል! ይህ በሚደረግበት ወቅት መደመርም በተጨባጭ መሠረት ላይ የሚያርፍበት ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል!

 

 

%d bloggers like this: