የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታና ስለችግሮቹ ዶር ዳንኤል በቀለ የሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫ

23 Jan

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

ጥር 14 ቀን 2012 ዓ.ም አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወር የሥራ ክንውን ሪፖርት ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡

በዚህ ሪፖርት በዋነኝነት ኮሚሽኑን በአዲስ መልክ ለማዋቀርና ለማደራጀት እየተወሰዱ ስላሉት የሽግግር ወቅት የለውጥ እርምጃዎችና የአፈጻጸም ስልቶች ለምክር ቤቱ አስረድቷል፡፡

በተለይም የተቋሙን የአቅም ውስንነት ለማሻሻል፣ የሕግ ማዕቀፍ ክፍተቶችና ተግዳሮቶችን ለማስወገድ እየተዘጋጀ ስለሚገኘው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ፣ ስለ አዲስ ኮሚሽነሮች አመራረጥ፣ እንዲሁም የኮሚሽኑ የበጀት/ፋይናንስ እና የሰው ሃብት አስተዳደር ነፃነት አስፈላጊነት ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ስለ ወቅታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ እና ስጋት በአሁኑ ወቅት የተሟላ ሪፖርት ለማቅረብ ባይቻልም ዋና ኮሚሽነሩ የሚከተሉትን ነጥቦች ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡

1. በሀገራችን ኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ተጨባጭ ውጤቶች አስገኝቷል፡፡ በሌላ በኩል የለውጥ ሒደቱ የገጠሙት ውስብስብ ተግዳሮቶችና እንቅፋቶች የሰብዓዊ መብት ቀውስ ፈጥረውበታል፡፡ በብሔር ማንነትና አልፎ አልፎም በሃይማኖት መስመር የተካረረ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፤ የአመጽ ግጭት እየቀሰቀሰ በከተማም በገጠርም፣ በጐዳናም በመንደርም በሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶች ሳይቀር ዜጐች በአሰቃቂና አስነዋሪ መንገድ ተገድለዋል፣ ተደፍረዋል፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ከመኖሪያቸው፣ ከሥራቸው፣ ከትምህርታቸው ተፈናቅለዋል፤ እንዲሁም እጅግ ብዙ የህዝብና የአገር ንብረት ወድሟል፡፡ መሳሪያ የታጠቁ ቡድኖች ሰዎችን በሃይል አግተዋል፣ ገድለዋል፡፡ የመንግስት ሰራተኞች፣ የውጭ አገር ዜጎች፣ ወንድና ሴት ወጣት ተማሪዎች እና ሕጻናት ሳይቀሩ የዚህ ሰለባ ሆነዋል፡፡

የዚህ ሁኔታ የስር ምክንያት የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን በመሆናቸው፣ መንግሥትና ይህ ምክር ቤትም በተለይ ለፖለቲካዊ ችግሮች በአገርና ሕዝብ የሠላም ፍላጎት እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች መከበር ላይ የተመሰረተ አገራዊ መፍትሔ መሻቱን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ጥረቱን ሊቀጥል ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላው የምርመራ ስራ የአጥፊዎችን በሕግ ፊት ተጠያቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

በሌላ በኩል ሀገራችን አሁን ከምትገኝበት ልዩ የሽግግር ሁኔታ አንጻር ሰላምንና ደህንነትን ማስፈን የሁሉንም ወገኖች ድርሻ ስለሚጠይቅ እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሰብዓዊ መብቶችን ማክበርና ማስከበር የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጐች ኃላፊነት ስለሆነ፤ በተለይ የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎቻቸው ትልቅ ሚና እና ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ስለዚህም የአመጽ ተግባሮችን በግልጽ በማውገዝና ደጋፊዎቻቸውን ወደ ሁከትና ብጥብጥ ከሚገፋፋ ተግባርና ንግግር ተቆጥበው በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንዲሰሩ ያስፈልጋል፡፡

2. የአመጽ ግጭት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ችግሩ እንዳይባባስ በመከላከልና አንጻራዊ ሠላምና መረጋጋት መልሶ በማስፈን በተለይ የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ሃይሎች በሕይወት መስዋእትነት ጭምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በአንጻሩ አንዳንድ አካባቢዎች በፌዴራልም ሆነ በክልል የፀጥታ ሃይሎች የፀጥታ ማስከበር ሒደት ውስጥ ዜጐች ከሕግ ውጭ ለሞት፣ ለእስርና እንግልት የተዳረጉበት ሁኔታም በመኖሩ፤ የሕግና ሥርዓት ማስከበር ከፍተኛ አስፈላጊነት የመኖሩን ያህል፤ በከፍተኛ ጥንቃቄና የሃላፊነት ስሜት ሊተገበር ያስፈልጋል፡፡

በአዲሱ የፖለቲካ ምዕራፍ ከተሰጡት የማይረሱ ቃል ኪዳኖች ውስጥ አንዱ “ሳይጣራ እስር የለም” የሚለው ትክክለኛ የሕጋዊነትና የሰብዓዊ መብት መርህ ነው፡፡

በአንዳንድ የወንጀል ሁኔታዎች እንዲሁም በበቂ ሕጋዊ ምክንያት በተወሰነ መልኩ ተጠርጣሪዎች በእስር ሆነው ጉዳዩ የሚጣራበት የሕግ አግባብ መኖሩ ቢታወቅም፤ ዋነኛ የአሰራር መርሁ ከላይ እንደተገለጸው ከእስር በፊት ምርመራን በተሟላ መልኩ ማጠናቀቅና ከክስ ሒደት በፊት ያለውን የተጠርጣሪዎች እስር (Pre-Trial Detention) መከላከል ወይም በከፍተኛ መጠን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡

3. በሀገራችን በአዲስ መልክ ለተጀመረው ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ለውጥ (Political Transformation) ራዕይ፤ ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች ማክበርና ማስከበር የተልዕኮው ማስፈጸሚያ መሣሪያም ዓላማም ነው፡፡

ሆኖም በተለይ ከፖለቲካ ተሳትፎ መብት ጋር ተያያዥ የሆኑት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብት ከዋና ከተማችን አንስቶ በክልሎችም ውስጥ አልፎ አልፎ አለአግባብ የመደናቀፍ ሁኔታ ስለተከሰተ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥት ኃላፊዎች ይህን አዝማሚያ አጥብቀው ሊከላከሉና ችግር ሲከሰትም የተፋጠነ መፍትሔ እንዲሰጡ ያስፈልጋል፡፡

በአንጻሩ ኃላፊነት የጎደለው የመደበኛም ሆነ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የጥፋት መሳሪያም ሊሆን ስለሚችልና አሳሳቢ ምልክቶችም በመታየታቸው የሚዲያ ባለሙያዎችና የማህበራዊ ሚዲያ ዘጋቢዎችና ፀሐፊዎች በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንዲሰሩ ያስፈልጋል፡፡

4. የሀገራችንን አዲስ የለውጥ እርምጃ ዕውን ለማድረግ ልዩና ታሪካዊ ሚና ለነበራቸው ወገኖች የኢትዮጵያ ሕዝብና ወዳጆች የሰጡት ተገቢ ዕውቅናና አክብሮት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ሊረሳ የማይገባው ሐቅ ይህ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን በብዙ መልኩ ሰፊ መስዋዕትነት የከፈሉበት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድልና ዕድል እንጂ የተወሰኑ ሰዎች ወይም ቡድኖች ብቻቸውን የፈጠሩት፣ ወይም ለብቻቸው ባለቤት የሚሆኑበት ስላልሆነ፤ ሁላችንም በእያንዳንዱ ግለሰብ ደረጃ ድሉንና ዕድሉን ልንጠብቅ፣ ችግሮቻችን በመተባበርና በመተጋገዝ ልንቀርፍ፣ ሰላም ልማትና ዲሞክራሲ ለሀገራችን ለማምጣት መብት እና ኃላፊነት አለብን፡፡ ሁሉም ሰው ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶችን የማክበርና የማስከበር ግዴታና ኃላፊነት አለበት ስንል ይህን ማለታችን ነው፡፡

 

/ ከኢትዮጵያ ሰብ ዓዊ መብቶች ኮሚሽን ፌስቡክ ገጽ የተወሰደ

%d bloggers like this: