ስለ ታገቱት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች አሁንም የሚሰቀጥጥ ፍንጭና ምስክርነት እየወጣ ነው! መንግሥታዊ ሽፍታነት ለምን?

17 Feb

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

ጋዜጠኛ መዓዛ መሃመድ በፊስ ቡክ ገጿ የካቲት 15/2020 የሚከተለውን መረጃ አሥፍራለች።

“በደምቢ ዶሎም አዲስ አበባም አንድ ነው!!!

ዛሬ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በታገቱ እህቶቻችን ጉዳይ የታሰሩ የታጋች እህት እና ለሀሰተኛ ዶክመንተሪ በዛቻ ከደቡብ ጎንደር የመጡ እህቶቼን፤ ጉዳያቸውን ለማጣራት እና ለማነጋገር ፖሊስ ኮሚሽን ተገኝቼ ነበር።

የታጋች እህት ፍቅርተ በትናንትናው እለት የታሰረች ሲሆን እንደነገረችኝ የተከሰሰችበት ክስ “ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨትና አመፅ እንዲነሳ በማድረግ” ነው። የታገተችባት እህቷ አስቻሉ ቸኮል በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ የሶስተኛ አመት ተማሪ ስትሆን፤ ከታገተች በሁዋላ አጋቾቹ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ በመሆናቸው ፍቅርተ ለተከታታይ ቀናት በአስተርጓሚ ያዋሯት ነበር። ይህ ኦሮምኛ ቋንቋን በመተርጎም ሲያግዛት የነበረ አበበ አብርሃም የተባለ ግለሰብ አብሯት እዚሁ ታስሮ ይገኛል።

በተመሳሳይ ባህር ዳር ተገኙ ተብለው በማህበራዊ ሚድያ ፎቷቸው ሲሰራጭ የነበሩትና መንግስት ለድራማ ያዘጋጃቸው ናቸው የተባሉት ሸዋዬ ገነትና ቅድስት ጋሻው የተባሉ ሴቶችን ከደቡብ ጎንደር ይበልጣል በተባለ ግለሰብ አስፈራርተው ለባህርዳር ደህንነት እንዳስረከቧቸው ነግረውኛል። አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከመጡ በሁዋላ ይህንኑ እንደተናገሩ ነግረውኛል። አንተባበርም በማለታቸው “ለመንግስት የተሳሳተ መረጃ በመስጠት” በሚል ክስ ተከሰው ታስረው ይገኛሉ።

ይህ ጉዳይ ሀገራችን ምን ያህል የሞራል ልዕልና ኃላፊነት በማይሰማቸው እጅ እንደምትገኝ የሚያሳየን ሲሆን፤ ገዥው መንግስትም ምንም ያህል የእህቶቻን ጉዳይ ያላስጨነቀውና ብሎም ወንጀለኞችን ለመደበቅ ብዙ እርቀት እየሄደ እንደሆነ ያሳያል።

ለዜጎቹ የሚቆረቆርና ኃላፊነት የሚሰማው መንግስት የለንም፣ ለተበደሉ እህቶች የሚቆም ጠንካራ ተቋማት አልገነባንም፣ መንግስት የታገተ እንዳለም እውቅና መስጠት አልፈለገም። የተደራጀ ህዝብና ጠንካራ ተቋምም የለንም።

ከዚህ በላይ ምን አለ? በዚህ ሁኔታ ሃገር አለን ማለት እንችላለን ወይ? ነገ የእንዚህ ልጆች እጣ ፈንታ እንደማይገጥመን በምን እርግጠኛ እንሁ?”

—-000—-

የሚገርመው የጠሚ ዐቢይ አስተዳደር በሚያዝበት ፓርላማ፣ አባላቱ ከሄዱበት ዕረፍት ባስቸኳይ እንዲመለሱ መደረጋቸው ይታወሳል። የተፈለጉበትም ዋናው ምክንያት የጥላቻ ንግግርን አዋጅ — ኢትዮጵያውያን ምሁራንም ሆኑ የተባበሩት መንግሥታት የሃሣብና የአስተሳሰብ ነጻነት ራፖርተር ቅሬታዎቻቸውን አስምተው እንዲታረሙ ሃሣብ ያቀረቡባቸው ሳይወገዱ ረቂቁ እንዲጸድቅ ተደርጓል።

ከዚያ ሁሉ ጥድፍያ በኋላ ሕጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ተፈጻሚ እየሆነ ያለው—ጋዜጠኛ መዓዛ ከላይ እንደጠቆመችው—በታጋች ተማሪዎች ቤተሰቦች ላይ ነው።

በተከፋፈለች ኢትዮጵያ ውስጥ የጥላቻ ንግግር ሕግን ከንጋቱ ጀምሬ ተቃዋሚ ነበርኩ። ዋናው ሥጋቴ እንዲህ ሃገራዊ ስሜት በተመናመነበት ሁኔታ፣ ሕጉ በሕወሃት ጊዜ በከፋ የአፈና መሣሪያነቱንና በተለይም ምርጫውን ለመዝረፍ ዐይነተኛ ማጥቂያነቱን በማሰቤ ነው። ስለሆነም በሕጉ ዙሪያ ምን እየተደረገ እንደሆን በየቀኑ እከታተል ነበር።

ከሁሉ የማልዘነጋቸው ግን ሕጉን የራሱ ዓላማ ተፈጻሚነት እንዲኖረው በማድረድ፣ (David Kay vs Almariam)አልማሪያም ለጠ/ሚሩ ባለው ቅርበት—Hate, Hearts and Minds: “Creating an Ethiopia That is Second to None in Its Guarantee of Freedom of Expression” (Part I) የሚከተለውን ማብራሪያና እርሱ ከProf. Kaye ጋር እንደማይስማማና በሚያሳዝን መንገድ እንዲጸድቅ እንደሚገፋ እንደሚከተለው ነበር ለሕዝብ ባቀረበው ጽሁፍ የገለጸው፦

“I do not think the draft proclamation is perfect but I certainly do not share the “serious concerns” expressed by Kaye nor agree with his main conclusions about the draft proclamation’s alleged flaws. Neither do I believe Article 19 of the International Covenant on Civil and Political Rights as propounded by the chosen few oracles is the standard of perfection for freedom of expression. 

It is the solemn duty of the defense lawyer to take a position on an issue of law and prevail by providing substantial evidence and persuasive and convincing arguments. I see no need presently to litigate the issue of freedom of expression in Ethiopia or the alleged flaws of the draft hate crimes and disinformation proclamation in the court of Ethiopian or world public opinion.”

ለእኔ የዚህ ሕግ—ከላይ መዓዛ መሃመድ በተማሪዎቹ ሁኔታ ፌስቡኳ ላይ እንዳሠፈረችው— ጎጅነቱ ገሃድ ነው።

እነዐቢይ ችግር ቢኖርባቸው እኮ ባሉት ሕጎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሊታዩና ሊዳኙ የማይቻሉ ነገሮች የሉም!

መንግሥት ዜጎችን እንኳ ከጥቃት መከላከል አቅቶት ስለነበር፡ አሁን በምርጫው ዋዜማ አስደንጋጭ ኃይል መጠቀም ስትራቴጂ (Shock and awe doctrine —Ullman እና Wade ከ1996 ጀምሮ የሚያስተምሩበት ለመንግሥታት consultancy እስከዛሬ የሚሠሩበት) በልጦ የመገኘት ስልትን ማሳየቱ ነው።

ፕሮፈ አልማርያም ለዚህ ሕግ በአማካሪነት ኢትዮጵያ መጥተው፡ ሕጉ መተላለፉን አረጋግጠው ተመልሰዋል። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግን በጎ የፈጸሙ አይመስለኝም— አሁን ልጆቻቸው የታገቱባቸውን ቤተሰቦች ቤተዘመዶች “አልታገትንም” “ዋሽተናል”ብለው ተናዘው ፊልም እንዲዘጋጅባቸው መታሰቡ ለትውልድ ያስተዛዝባል።

ይህ ሕግ በኢትዮጵያ ላይ ዲክታቶሪያል መንግሥት የሚጭን ሕግ ስለሆነ፣ ነጻ ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚሹ ሁሉ ወግድ ሊሉት የሚገባ የሰው ልጆች መብት አፋኝ ሕግ ነው!ከላይ ካለው እንደሚታየው፣ በተለይም መዓዛ መሃመድ ግለሰቦቹን አነጋግራ የጻፈችው፣ የመንግሥትን ማንነትና ምንነት ያሳየ ይመስለኛል።

ንጋትና ጥራት እያደር እንደሚባለው፡ ሕዝቡም በጠራ ዐይን ሁሉንም የምናይበት ወቅት ሩቅ አይሆንም!  ሁሉም ሁሉን የሚያይበት፣ የሚያቅፈውን ማቀፉን የሚቀጥልበት፣ ስህተተኛ መንግሥትም ስህተቱን የሚያርመበት ሁኔታ እንዲፈጠር ተስፋ እናድርግ!

 

 

 

 

 

 

%d bloggers like this: