“ዘራፊው ለሕዝብ ጥቅም እየተባለ ክሱ እንዲነሳ ከተደረገ ውርደቱ ለአቃቤ ሕግ ነው” አቶ ዮሐንስ ወልደገብርኤል

27 Feb

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

Legal expert Ato Yohannes W. Gabriel (BBC foto)

ከሙስናና ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያዘ እስር ላይ የነበሩ ስልሳ ሦስት ሰዎች ክሳቸው ተቋርጧል። ክስ ለማቋረጥና ሰዎቹን ከእስር ለመልቀቅ የተሰጠው ምክንያት የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት የሚል ከመሆኑ አንፃር፤ ፍትህን ማስፈን እና እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ እንዴት አብሮ መሄድ ይችላል? የሚልና ሌሎች ከግለሰቦቹ ክስ መቋረጥ ጋር ተያይዞ በርካታ ጥያቄዎችም እየተነሱ ነው።

የደርግ ከፍተኛ አመራሮችን ለመክሰስ ተቋቁሞ በነበረው ልዩ አቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት፣ በኋላም በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአቃቤ ሕግነት ከዚያም በቀድሞው የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን የሕግ ክፍል ኃላፊ የነበሩት አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤልን በዚህ ጉዳይ ላይ አነጋግረናል።

አቶ ዮንስ፦ የእነዚህ የሙስና ድንጋጌዎች እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ መታየታቸው ከቀረ ከሃምሳ ዓመት በላይ ሆኗቸዋል ብዬ ነው የማምነው። እነዚህ የሙስና ወንጀል ህግ ድንጋጌዎች በመጀመሪያ ደረጃ መደበኛው አቃቤ ሕግ፣ መደበኛው ፖሊስ የሚያስፈፅሟቸው አይደሉም።

የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች ምርመራ ፖሊስ ነው የሚያጣራው ከማንም ትእዛዝ አይቀበልም። በተሰጠው ስልጣን፣ በተሰጠው ኃላፊነት ጥቆማ ሲደርሰው ወይም በራሱ ክትትል ሲረዳ ምርመራ አጣርቶ ለአቃቤ ሕግ ይልካል። አቃቤ ሕግም እነዚህን ምርመራዎች ይዞ ወደ ፍርድ ቤት ያቀርባል። ፍርድ ቤትም እንደ ማንኛውም የወንጀል ድንጋጌ አይቶ፣ መዝኖ ውሳኔ ይሰጣል።

የሙስና የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች ላለፉት ሃምሳ ዓመታት፣ ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ የመደበኛው አቃቤ ሕግ፣ የመደበኛው ፖሊስና የመደበኛው ፍርድ ቤት እጅ ውስጥ መሆናቸው ቀርቷል ብዬ አምናለሁ።

እንደ ቀድሞ አቃቤ ሕግ የምናገረው እነኚህ የሕግ ድንጋጌዎች መደበኛው ፖሊስ፣ መደበኛው አቃቤ ሕግና ፍርድ ቤት አይደለም ውሳኔ የሚሰጥባቸው። ይህ መሰረታዊ ጉዳይ በራሴ በምርምር የደረስኩበት ነው። በፊት በመርማሪ ኮሚስዮን ጊዜ እነ አክሊሉ ኃብተወልድ የተያዙት እኮ ሙስና ፈፀሙ ተብለው አይደል፤ እነሱ ከተያዙ በኋላ ምርመራ ተጀመረ።

ከዚያ በኋላ ግን ሂደቱ ተቋረጠና ወደ ፍርድ ሳይቀርቡ ቀሩ። እና የመንግሥት ኃላፊዎች በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ይሄንን ፈፀሙ፣ ይሄንን አደረጉ የሚባል የወንጀል ክስ ከእነ አክሊሉ ኃብተወልድ ጊዜ ጀምሮ ከመደበኛው የወንጀል ሕግ ሥርዓት ወጥቷል በሕግ ሳይሆን በተግባር። ይህ በደርግ ጊዜ ያው ነው፤ በኢህአዴግ ጊዜም ያው ነው፤ አሁንም ያው መሆኑን ነው የማውቀው።

የመንግሥት ባለስልጣናት በሙስና ተብሎ ሲከሰሱ ጉዳዩ ወንጀል ይልቅ እንደ ፖለቲካ ጉዳይ ነው የሚታየው እያሉ ነው?

አቶ ዮንስ፦ እነዚህ ወንጀሎች ከመደበኛው የፖሊስ ተግባርና ኃላፊነት፤ ከመደበኛው የአቃቤ ሕግ ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም ከመደበኛው የፍርድ ቤት ተግባርና ኃላፊነት ውጭ ባለ አካል ነው ውሳኔ የሚሰጥባቸው።

እኔ ያለፉትን አርባ ዓመታት ሁኔታዎች ስገመግም በብዙዎችም ተሳትፌያለሁ በፍፁም ተራው ፖሊስ ሄዶ፣ አጣርቶ ለአቃቤ ሕግ አቅርቦ፣ ፍርድ ቤትም ወስኖ የሚኬድበት ነገር አደለም።

ሲጀመርም እነዚህ ወንጀሎች ፖለቲካዊ የተደረጉ ወንጀሎች ናቸው፤ የፖለቲካ ተሿሚ የፖለቲካ ስልጣን ከፖለቲካ ስራዎች፣ ከመንግሥት ሥራዎች ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት ያላቸው የወንጀል ድርጊቶች ናቸው።

ከዚህ አንፃር አሁን ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር የተለቀቁትን 63 ሰዎችን ጉዳይ እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ ዮሐንስ፡ በተመሳሳይ መንገድ ነው የምመለከተው፤ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ አስፈፃሚ አካላት ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክስ የማንሳት ስልጣን አለው፤ ጠቅላይ ሚነስትሩ አንድ የወንጀል ክስ፣ ከመደበኛ የወንጀል ጉዳይ ባሻገር፤ ክሱ ቢነሳ ተመራጭ ነው ብሎ ሊወስንና ለአቃቤ ሕግ ሊያስተላልፍ ይችላል።

ይሄ በወንጀለኛ የመቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ያለ ነው። የወንጀል ክስ ባለቤት መንግሥት ነው። ስለዚህ መንግሥት ሲወስን ክሱን ማንሳት ይቻላል። ክሱን የሚያነሳው አቃቤ ሕግ ሲሆን ያቀረብከውን ክስ አንሳ ከተባለ በምንም ምክንያት ይሁን ይሄ የመንግሥት ውሳኔ ነው እንዲነሳ ማድረግ ይቻላል፤ ይሄም በሕጉ ላይ የተቀመጠ ነው።

በመንግሥት ውሳኔ እነዚህ፣ እነዚህ ሰዎች ይፈቱ ተብሎ ከተወሰነ፤ በፖለቲካዊ ምክንያት ይሁን ለሌላ፤ እነዚህን ሰዎች በወንጀል ክስ ከምንሄድ እና በሕግ አስፈርደን በፍትህ ሥርዓቱ ማግኘት ከምንችለው ውጤት ይልቅ ክሱ ቢነሳ ይሻላል ብሎ መንግሥት ካመነ ማድረግ ይችላል።

ከዚህ አንፃር መንግሥት የ63 ቱን ሰዎች ክስ ማቋረጥ ትክክል ነው ማለት ነው?

አቶ ዮንስ፦ ይቻላል በፖለቲካዊ ምክንያቶች ነገር ግን ከዚህ ውጭ አቃቤ ህግ በመግለጫው ሲሰጥ የነበረው ምክንያት ከመንግሥትን ውሳኔ ጋር ለመጣጣም የተደረገ ጥረት ነው። ነገሩ የአቃቤ ሕግ ተቋም ድክመትን ነው የሚያሳየው። ከመንግሥት እነ እከሌ ይፈቱ ተብሎ ከታዘዘ ይቻላል፤ ለውሳኔው ምክንያት በማስቀመጥ የግለሰቦቹ መለቀቅ ተገቢነትን ለማረጋገጥ መሞከር አይገባውም።

አቃቤ ህግ በዚህ በዚህ እያለክሱ የተቋረጠበትን ምክንያት ማስቀመጥ አይጠበቅበትም እያሉኝ ነው?

አቶ ዮንስ፦ የሰጠው ምክንያት በራስ ላይ የመፍረድ ያህል ነው በቀላሉ መንግሥት በሰጠው አቅጣጫ ወይም አመራር ክሳቸው እንዲነሳ ተደርጓል ከሚል በስተቀር ሌላ ምክንያት ለመደርደር እውቀቱም፣ ችሎታውም አቅሙም ሊኖር አይገባም። የክሱ መቋረጥ ተገቢነትን ላብራራ ካለ እንዴት አድርገህ መዝገብ ከፈትክ? ምንድን ነው የማስረጃው ብቃት? ወደሚል ሊመጣ ነው።

መንግሥት እነዚህን ሰዎች አስሮ በፍርድ ሂደት አስፈርዶ፤ ፍትህን አስፍኖ ከማመጣው ውጤት ይልቅ እነዚህን ሰዎች በመልቀቅ የማመጣው ውጤት ይበልጣል ብሎ ሲያምን ሊወስን እንደሚችል በህግ የተቀመጠ ነው ብለዋል። ምናልባት ይሄ የመንግት ስልጣንገደብ ውስጥ የሚወድቅበት ምክንያት አለ?

አቶ ዮሃንስ፦ ገደብ የለውም፤ አንድ ክስ ይነሳ ብሎ ከታዘዘ ገደብ የለውም። አንድ ክስ ይነሳ ብሎ ካዘዘ ይፈጸማል ነው የሚለው ሕጉ።

ክሱ ምንም ሊሆን ይችላል? ጊዜው መቼም ሊሆን ይችላል? ምንም አይነት ገደብ የለም?

አቶ ዮንስ፦ገደብ የሌለው ስልጣን ነው፤ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የሚል ነገር ግን አለው። ይሄ የእኛ አገር ሕግ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አገሮች አለ። የፍትህ ሥርዓትን የሚያሽመደምድ ነገርም አደለም።

ነገር ግን እጅግ ጥንቃቄ ባለው ሁኔታ የሚከናወን ነው። ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ይህን ትዕዛዝ በሚቀበልበት ጊዜ እንደማንኛውም አሽከር ዝም ብሎ ተቀብሎ ይፈጽማል ማለት አይደለም። የአቃቤ ሕግ ተቋምን ሊያጠለሽ እና ተዓማኒነቱን ሊያሳጣው የሚችል ቆሻሻ ውሳኔ ከመንግሥት ሊመጣ ይችላል።

አቃቤ ህግ የሙያ ተቋም፤ ሕዝብን ወክሎ የሕዝብን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው። ስለዚህ ሥራው ሙያዊ መሆን መቻል አለበት። የዚህ ዓይነት ትዕዛዝ ተቀብሎ ተግባራዊ በሚያደርግበት ጊዜ የእሱ ምክር በጣም ጠቃሚ ነው። አቃቤ ህግ የፌደራል መንግሥትም ህጋዊ አማካሪ ነው። ቁመናው፣ ብቃቱ፣ አስተማማኝ ያልሆነ የአቃቤ ሕግ ተቋም የፖለቲከኞች ውሳኔ አስፈጻሚ ነው የሚሆነው።

የአቃቤ ሕግ ሙያ በጣም የተከበረ ነው። በሕዝብ ዘንድ መሳቂያ፣ መሳለቂያ የማያደርገውን ምክር ለመንግሥት ሰጥቶ ነው እንጂ እንዲህ ያለውን ውሳኔ መፈፀም ያለበት ዝም ብሎ ዘራፊውም ሌባውም ለሕዝብ ጥቅም እየተባለ ክሱ እንዲነሳ ከተደረገ የመጨረሻ ውርደቱ ለአቃቤ ሕግ ተቋም ነው። ተአማኒነቱን ያጣዋል።

የማን ክስ ነው የሚቋረጠው?እነማን ናቸው የሚለቀቁት? የሚለውስ? መንግሥት ክሶች እንዲቋረጡና ሰዎች እንዲለቀቁ የማድረግ ገደብ የሌለው ስልጣን ካለው፤ አቃቤ ሕግ በምን መልኩ ምክር ሰጥ ምን ድረስ ተገቢላይሆኑ የሚችሉ ውሳኔዎችን አይሆንም የማለት፣ የማንገራገር ወይም የመቃወም ስልጣን አለው? በተለይም አገሩቱ የተቋማት ጥንካሬ አንፃር

አቶ ዮንስ፦ለመገዳደር ይችላል፤ ነገር ግን ጀርባ ያለው አቃቤ ሕግ ሲሾም፤ በሙያ፣ በእውቀቱ እና በችሎታው መንግሥትን መምራት የሚችል አቃቤ ሕግ ተቋም ሲኖር ነው።

ግልጽ የሆነ ማዕቀፍ ላይ ተመስርቶ የማይሰራ የአቃቤ ሕግ ተቋም ከሆነ ደግሞ ይሄ አሁን እንደሆነው ነው የሚሆነው። በዚህ ረገድ አንዱ እየተፈተነ ያለው የአቃቤ ሕግ ተቋም ነው። ስለዚህ የሰዎቹ አለቃቀቅ፣ የሰዎቹ ስብጥር፣ ምን አይነት ሰዎች ናቸው እየተፈቱ ያሉት የሚለው ጉራማይሌ ነገር ከተገኘ የአሰራር ችግር አለ ማለት ነው።

አሁን ለምሳሌ የፖለተካ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል እና ለህዝብ ጥቅም ከተባለ በርግጥም የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፋው ምን አይነት ሰዎችን፣ ምን አይነት ፖለቲካዊ ክሶችን አቅርበናል? እነማንን ነው መልቀቅ የሚገባን? የሚሉት በደንብ መታየት አለባቸው።

አንድ ክስ የቴክኒክ ማስረጃ ክፍተት ከተገኘበት በመንግሥት ስልጣን ሳይሆን አቃቤ ሕግ በራሱ ስልጣን ክሱን እንዲቋረጥ ማድረግ ይችላል። ቴክኒካል የሆነ ማስረጃው በቂ ነው ወይስ አይደለም፣ ደካማ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ጉዳይ የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ስልጣን ነው።

ደካማ ክስ፣ አጓጉል ክስ፣ ባለበት ሁኔታ መወሰን ይገባው የነበረው አቃቤ ሕጉ እንጂ መንግሥት አይደለም፤ የመንግሥት ውሳኔ ለአቃቤ ህግ ደካማ ክሶች ሽፋን መሆን የለበትም። አቃቤ ህግ በቂና አሳማኝ ባልሆነ ማስረጃ ክስ መመስረት የለበትም።

ክስ ለመመስረት የማያበቁ አካሄዶች አቃቤ ግ በራሱ ስልጣን ቀድሞ ሊያስቆማቸው ይገባል?

አቶ ዮንስ፦አዎ ማድረግ ነበረበት፤ በትክክል። ይሄ ግን ብዙ ጊዜ ሲተገበር አናይም እንዲያውም የሚታየው ልፍስፍስ ክሶች ሁሉ እንዲስተናገዱ ሲደረግ ነው።

ብዙዎች ውሳኔ ማሰጠት የማይችሉ ደካማ ክሶችን ፍርድ ቤት እያቀረቡ፤ ነገር ግን መንግሥት ለህዝብ ጥቅም ብሎ የሚያቋርጣቸው ናቸው። የመንግሥት ትኩረት መሆን የነበረበት ግን በደንብ ለፍርድ ሊቀርቡ፣ ሊፈረዱ የሚችሉ ጉዳዮችን ተመልክቶ ለህዝብ ጥቅም ነው ብሎ ካመነ መወሰን ነበር።

አሁን የተቋረጡት ክሶች ማስረጃ ክስ ወደ መመስረት የማያበቁ ነበሩ ብለያምናሉ?

አቶ ዮንስ፦ ማመን አይደለም፤ እገምታለሁ ምክንያቱም መዝገቡን ስላላየሁ እንደዛ ብዬ እንደ ቀድሞ አቃቤ ሕግ አፌን ሞልቼ ልናገር አልችልም። ነገር ግን መንግሥት ለህዝብ ጥቅም ብሎ እንዲነሱ የሚያደርጋቸው በጣም የተሟላ መረጃ ባላቸውና በማያጠራጥር ሁኔታ ፍርድ ቤት ፍርድ ሊያሳርፍባቸው የሚችሉ ጉዳዮች መሆን አለባቸው፤ በተረፈ ግን እነዚህ 63 ክሶች በእኔ እምነት ብዙዎቹ የመንግሥት ውሳኔ ሊያርፍባቸው ይገባል ብዬ አላምንም።

አብዛኞቹን ምናልባት አቃቤ ሕግ አስቀድሞ እንደ ክስም አድርጎ ሊያቀርባቸው የማይገቡ የነበሩ ናቸው የሚዲያ ሪፖርቶች ስሰማ፤ አሁን ለምሳሌ ተመሳሳይ ሊቀርቡ የማይገቡ ክሶች በፍርድ ቤት ሂደት ላይ አሉ። ነገር ግን እነዚህ ክሶች በዚህኛው የክስ መቋረጥ ውሳኔ ውስጥ አልተካተቱም።

ይሄን ያህል ቁጥር ያለው ተከሳሽ በመንግሥት ውሳኔ ይስተናገዳል ብዬ አላስብም፤ አብዛኞቹ ጉዳዮች አቃቤ ሕግ ዝም ብሎ አድፈንፍኖ ያቀረባቸው ናቸው ብዬ እገምታለሁ። እና አሁን መንግሥት ይህንን ውሳኔ ሲሰጥ በዚያ ውስጥ ተካተው እንዲስተናገዱ አደረጉ ብዬ ነው የማስበው፤ አቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት አለ ብዬ አላምንም ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ።

 

/BBC Amharic

 

 

%d bloggers like this: