የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ በእጅጉ ያሳስበናል!

17 Mar

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

”መልዕክተ ኢሰመጉ” ወርኀዊ የበይነ መረብ መጽሔት ቅፅ —1 ቁር—3

ተስፋና ሥጋት ይዞ በ2010 ዓ.ም የመጣው ፖሊቲካዊ ለውጥ እየዋለ ሲያድር ከተስፋው ይልቅ ሥጋቱ እያየለ መምጣቱን እያስተዋልን ነው፡፡ ለአንዱ ችግር ‹መፍትሔ ተገኘለት› ብለን ገና በቅጡ እንኳ እፎይታ ሳናገኝ ከሌላ ጥጋት ሌላ ቀውስ የሚፈጠር መሆኑ የአገራችንን ሁኔታ ‹የእንቧይ ካብ› አድርጎታል፡፡

በተለያዩ ሥፍራዎች የሚፈጠሩትና ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መንሥዔዎች የሆኑት ግጭቶች በዋናነት የሚቀሰቀሱት የብሔር ማንነትን መሠረት ባደረጉ በክልልና በዞን የመደራጀት ጥያቄዎች፣ በክልሎች መካከል በሚነሡ የወሰን ግጭቶች ምክንያት ነው፡፡ መንግሥትም ‹‹ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብት አለው›› ከሚለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ጋር በማይጣረስና ዜጎችን ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተጋላጭ በማያደርግ መልኩ ለጉዳዩ መፍትሔ መፈለግ ይኖርበታል፡፡

ከግጭቶቹ በስተጀርባ ግን በየክልሉ ያሉ፤ ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትርፍ የሚያገኙ፣ ከሥልጣን የተነሡም ሆኑ በሥልጣን ላይ ያሉ ሹሞች መኖራቸውን ከመንግሥት በኩል የሚሰጡ መግለጫዎች ሳይቀሩ ያረጋግጣሉ፡፡ በአገራችን ለቀውስ መንሥዔ የሆኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመቅረፍ በፌደራል መንግሥት ደረጃ የፖለቲካ ፈቃደኛነቱ ያለ ቢመስልም በክልሎች ደረጃ ግን በተለይም በዞንና በወረዳ ደረጃ ያለው ሁኔታ የተለየ ነው፡፡ ዛሬም ሰዎች በብሔር ማንነታቸው ምክንያት ይገደላሉ፣ የአካል ጉዳት ይደርስባቸዋል፣ ንብረቶቻቸው ይወድሙባቸዋል፣ ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬአቸው ይፈናቀላሉ፡፡

ይሄ ሁሉ ሲደረግ የክልል ባለ ሥልጣናት ጉዳዩ እንደማይመለከታቸው ሁሉ በቸልታ ይመለከታሉ፤ አንዳንዴም የድርጊቱ ቀጥተኛ ተሳታፊዎችና አስፈጻሚዎች ሆነው ይገኛሉ፡፡ የክልል ፖሊስና ልዩ ኃይል ዜጎችን በእኩልነት በማየት ወንጀል የመከላከል ኃላፊነታቸውን ከመወጣት ይልቅ የተሠማሩበት ክልል መጠሪያ የተሠየመበት ብሔር ‹‹ልዩ ጥቅም›› አስከባሪዎች አድርገው ራሳቸውን በመቁጠር በኅዳጣን ላይ ለሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ሽፋን ይሰጣሉ፡፡ በየሥፍራው የተነሡ ታጣቂ ኃይሎች ለሚፈጽሟቸው የግድያ፣ የዝርፊያና የእገታ ድርጊቶች መባባስ ምክንያቱ በታችኛው የመንግሥት መዋቅር ያለው የዕዝ ሰንሰለት መላላትና የፖለቲካ ፈቃደኛነት አለመኖር መሆኑን ከተጨባጭ እውነታዎች መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህም ምክንያት ሥርዓት አልበኛነት ነግሷል፡፡ ሕግ አልባነት ተቀባይነት ያለው፤ የተለመደ የሕይወታችን አካል ሆኗል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚቀሰቀሱ ኹከቶችም የዚሁ ነጸብራቅ ናቸው፡፡

በመካከላችን የወንድማማችነት መንፈስ ተሸርሽሮ የ‹‹እኛና እነርሱ›› አስተሳሰብ በመግነኑ የማይደፈሩ ቅዱሳን ሥፍራዎች የነበሩ የሃይማኖት ተቋማት የፖለቲካ ጥያቄዎችን በማስታከክ በተደጋጋሚ ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡ ዜጎች ለብቻቸው ወይም ከሌሎች ጋር በኅብረት በመሆን በይፋ የማምለክ፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓታትን እንዳይፈጽሙ፣ እንዳያስተምሩና እንዳይገልጹ ‹በጎበዝ አለቆች› ሲከለከሉ የጸጥታና የአስተዳደር አካላት መብታቸውን ለማስከበር በቂ እርምጃ ሲወስዱ አይታይም፡፡

ዜጎቿ መሠረታዊ በሆኑት የምግብና የመጠለያና እጦት በሚሠቃዩባት ኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ ለቁጥር የበዙ የፖሊቲካ ፓርቲዎች በርካቶቹ የአገራችንን ችግሮች የሚቀርፉና ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ አማራጭ ፖሊሲዎች ያሏቸው ሳይሆኑ መታገያ አጀንዳቸውን በ‹ብሔር ጥያቄ› ላይ ብቻ ያደረጉ መሆናቸው አሁን ለምናያቸው ችግሮች የራሱን አስተዋጽኦ እንዳደረገ እናምናለን፡፡ በበይነ መረብ በአንዳንድ የማኅበራዊ መገናኛ መድረኮችና መደበኛ የብዙኃን መገናኛ አውታሮች የሚሠራጩ ብሔርና ሃይማኖት ላይ የሚያነጣጥሩ አደገኛ መልዕክቶችም ወደ የእርስ በርስ ግጭት እንዳይመሩን ያሠጋናል፡፡

ስለሆነም፣ ለአገር ሕልውና የሚያሠጉ ቀውሶችን የመፍታትና ችግሮች ተከስተው ወደ ቀውስ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት የመፍትሔ እርምጃ የመውሰድ ዋነኛ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ተግባሩን እንዲወጣ እናሳስባለን፡፡ ነገር ግን፣ መንግሥት ይህን ኃላፊነቱን ሲወጣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማይጥስ መልኩ መሆን አለበት፡፡

በአሁኑ ሰዓት እንደምናስተውለው በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በምዕራብ ወለጋ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የሚወሰዱ ሕጋዊ እርምጃዎችን በተመለከተ ከመንግሥት በኩል በቂ መረጃ ለሕዝብ እየቀረበ ባለመሆኑና የመረጃ ልውውጥ እቀባ በመደረጉ በኅብረተሰባችን ውስጥ ውዥንብር እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ስለሆነም፣ የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት ከግምት ውስጥ በማስገባት በአገራችን ስለሚከሰቱ፣ በዜጎች ሕልውና ላይ ተጽእኖ የሚፈጥሩ ጉልሕ ጉዳዮችን በተመለከተ መረጃ በየጊዜው ይፋ መደረግ አለበት፡፡

በመጨረሻም፤ የአገራችንን ሁኔታ አሥጊ ላደረጉ ችግሮች መፍትሔ መፈለግ የሁላችንም ግዴታ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የማኅበረሰብ መሪዎች በዚህ ረገድ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

 

2 Responses to “የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ በእጅጉ ያሳስበናል!”

  1. medaliounde March 18, 2020 at 22:59 #

    የአገራችንን ሁኔታ አሥጊ ላደረጉ ችግሮች መፍትሔ መፈለግ የሁላችንም ግዴታ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የማኅበረሰብ መሪዎች በዚህ ረገድ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

    Like

  2. medaliounde March 18, 2020 at 23:04 #

    የአገራችንን ሁኔታ አሥጊ ላደረጉ ችግሮች መፍትሔ መፈለግ የሁላችንም ግዴታ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የማኅበረሰብ መሪዎች በዚህ ረገድ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሚለው

    Like

Comments are closed.

%d bloggers like this: