የዐቢይ አሕመድ መንግሥት የቫይረሱን አጋጣሚ የተቃውሞ ድምፆችን ሊያፍንበት አይገባም!

13 Apr

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በተመለከተ የተዛቡ መረጃዎችና መንግሥታዊ ምላሽ

ካርድ፤ ሚያዝያ 5፣ 2012

መግቢያ

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዓለም አቀፋዊ ስጋት ነው። መንግሥትም ፈጣን ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል። ይሁንና የኮሮና ቫይረስ መተላለፊያ፣ ሥርጭቱን መከላከያ መንገዶች ላይ እንዲሁም በኢትዮጵያ አሁን ሥርጭቱ ያለበትና ሊደርስ የሚችልበት ደረጃ ላይ የተለያዩ የተዛቡ መረጃዎች እየተሠራጩ ይገኛሉ፣ ለወደፊትም ሊሰራጩ እንደሚችሉ እንገምታለን። እነዚህ የተዛቡና ምናልባትም ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ መረጃዎች የሚመነጩት ደግሞ ከተለያዩ የእምነት መሪዎች/ሰባኪዎች፣ ከባሕል መድኃኒት አዋቂዎች፣ ከጋዜጠኞች (ጦማሪዎች) እና ሌሎችም እንደሆነ ተመልክተናል። ይህንን የመከላከል ሥራ መሥራት የመንግሥትና የሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ድርሻ ነው። መንግሥት ግልጽነትን በመጨመርና ተአማኒነቱን በማሳደግ፣ ሌሎች ብዙኀን መገናኛዎችና ሲቪል ማኅበራት ደግሞ የተጣሩ መረጃዎችን በማዳረስ ሰዎች በተዛቡ መረጃዎች እንዳይሳሳቱና እንዳይዘናጉ ማድረግ ይገባል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ከተገኙ (መጋቢት 4፣ 2012) አንድ ወር የተቆጠረ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከተለያዩ አካላት የተለያዩ ሐሰተኛ መረጃዎች የተሰራጩ ቢሆንም፥ የመንግሥት ትኩረት ግን በጋዜጠኞችና ጦማሪዎች ወይም አክቲቪስቶች ላይ ሆኖ ተስተውሏል። ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር በተገናኘ የተዛባና ጉዳት ሊያስከትል የሚችል መረጃ አሰራጭታችኋል በሚል ሁለት ሰዎችን (ያየሰው ሽመልስ እና ኤልሳቤት ከበደን) አስሯል። የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) የተዛቡ መረጃዎች ሥርጭት ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ የሚረዳ ቢሆንም፣ የተዛቡ መረጃዎችን ስርጭት መከላከልም ይሁን መግታት የሚቻለው በእስር ነው ብሎ አያምንም። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደገለጽነው፣ የተዛቡ መረጃዎች ከመንግሥት ግልጽነት እና ተጠያቂነት አለመኖር፣ ከብዙኀን መገናኛዎች ሐቅን የማረጋገጥ ባሕል/ልምድ እጦት እና ከሲቪል ማኅበራት የብዙኀን መገናኛዎች አረዳድ የማሳደግ ሥራ አለመሥራት የሚመነጭ ነው። እነዚህን ችግሮች መቅረፍ የመፍትሔው አካል መሆኑንም እናሰምራለን።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ መንግሥት የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል። ለዚህ አዋጅ ማስፈፀሚያ የወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ (የመጨረሻ ረቂቅ) የሐሰተኛ መረጃዎችን ከመከላከል ጋር በተያያዘ ሁለት ድንጋጌዎች አሉት።

በክፍል 3፣ አንቀጽ 26፦

“ኮቪድ-19ኝና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ማኅበረሰቡ እንዳይረጋጋ የሚያደርግና በማኅበረሰቡ ላይ ሥነ ልቦናዊ ጫና የሚፈጥር ማናቸውንም መረጃ ማሰራጨት የተከለከለ ነው”

በክፍል 4፣ አንቀፅ 10፦

“የመንግሥት የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችና የግል የሚዲያ ተቋማት ኮቪድ-19ኝና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ የሚያስተላልፏቸው መረጃዎች፣ የዜና ትንተናዎች ወይም ፕሮግራሞች ሳይጋነኑ ወይም ሳይቃለሉ ተገቢው መረጃ ወደ ሕዝቡ የማድረስ እና አላግባብ የሆነ ድንጋጤና ሽብርን የማይፈጥሩ መሆን አለባቸው።”

ይሁንና በአንቀጽ 3/26 የተጠቀሰው “እንዳይረጋጋ የሚያደርግ”፣ “ሥነ ልቦናዊ ጫና የሚፈጥር” የሚሉ እንዲሁም በአንቀፅ 4/10 የተጠቀሱት “ማጋነን” ወይም “ማቃለል” ብሎም “አላግባብ የሆነ” የሚሉ  ቃላት እና ሐረጎች በሕግ አግባብ ግልት ፍቺ የሌላቸው እና በተለያዩ መንገዶች ሊ የሚችል ስለሆነ ከአዋጁ መውጣት አስቀድሞ ያስተዋልናቸው ችግሮች ተባብሰው እንዳይቀጥሉ ያሰጋናል።

ካርድ ይህንን ጥቆማ መግለጫ ለማውጣት የወሰነበት ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የሚሰራጩ ተአማኒነት የሌላቸው ወይም ደግሞ በተለያዩ አካላት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ መረጃዎችን ለመግታት እየወሰደ ያለው እርምጃ  ላይ ያለውን ሥጋት ለመግለጽ እና አማራጭ መፍትሔዎችን ለመጠቆም ነው። ለዚህም የጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ እና ጠበቃ ኤልሳቤት ከበደን የእስር ጉዳይ እንደማሳያ አቅርበናል።

ያየሰው ሽመልስ ጉዳይ

ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ መጋቢት 17፣ 2012 ‘ኢትዮ ፎረም’ በተሰኘው የግል የዩቱዩብ ገጹ “200ሺህ የመቃብር ቦታዎች እንዲዘጋጁ መንግሥት አዘዘ” የሚል ዜና ሠርቶ በፌስቡክ ገጹም አጋርቶ ነበር። ያየሰው በዜናው ዝርዝር መንግሥት በምሥጢር በኮቪድ 19 ምክንያት ይሞታል ተብለው ለተገመቱ ሰዎች የመቃብር ቦታ እንዲዘጋጅ እንደተነገራቸው ምንጮቻቸው እንደነገሯቸው ገልጸዋል። አሁን የዚህ መረጃ ቪዲዮ ከዩቱዩብ ገጹ የተሰረዘ ሲሆን፥ የጋዜጠኛው የፌስቡክ ገጽም ተዘግቷል። የዛኑ ዕለት በኢትዮጵያ ከምሽቱ 2፡32 ላይ ያየሰው “ፌስቡኬን ዘግተውታል። በዚህ ልክ አስደንጋጭ እንደሚሆን አልገመትሁም ነበር። በተፈጠረው ነገር ሁሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ።” የሚል መልዕክት በትዊተር ገጹ ላይ አስተላልፏል። ከዚያ በኋላ፣ ከምሽቱ 3፡59፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ባስተላለፈው ማስተባበያ “ከእውነት የራቀ ከመሆኑም በላይ ሕዝባችንን ለማደናገር ሆን ተብሎ የተደረገ አሳዛኝ የተንኮል ተግባር በመሆኑ በጥብቅ ሊወገዝ ይገባል” ብሏል። በማግስቱ ጠዋት፣ መጋቢት 18፣ 2012 ከዚሁ ጋር በተያያዘ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል።

ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ በጋዜጠኛነት መስክ ላለፉት ስምንት ዓመታት የሠራ ሲሆን፣ ለኢቲቪ፣ ፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት፣  ኢኤንኤን  ቴሌቪዥን እና ናሁ ቴሌቪዥኖች ሠርቷል። ኢኤንኤን ቴሌቪዥን ከተዘጋ ወዲህ በፍትሕ መጽሔት እና በትግራይ ቴሌቪዥን በተፈቀደለት የአየር ሰዓት በሚያሰራጨው ‘ኢትዮ ፎረም’ የተባለ ፕሮግራም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ላይ የሰላ ነቀፋና ትችት አዘል ቃለ መጠይቆችን ሲያቀርቡ ቆይቷል።

ጋዜጠኛ ያየሰው ከዚህ በፊትም በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ማስፈራሪያ እና ማዋከብ ይደርስበት እንደነበር ሲገልጽ ቆይቷል። ታኅሣሥ 24፣ 2012 ወደ መቐለ ጉዞ ሊያደርግ ቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርስ በደኅንነት ሠራተኞች እንዳይሔድ መደረጉንና ለሁለት ሰዓታት የዘለቀ ዘለፋ እንደደረሰበት ተናግሮ ነበር።

ያየሰው ሽመልስ ለእስር የዳረገውን ዜና ካሰራጨ በኋላ መጋቢት 20፣ 2012 የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መልዕክት “በዚህ ፈታኝ ወቅት በሕዝብ ጤናና ደኅንነት ላይ በልዩ ልዩ መንገድ  ሽብር የሚነዙ አካላት ላይ  የሕግ አስከባሪ  አካላት ሕግ የማስከበር ተግባራቸውን በጥብቅ እንዲያከናውኑ የታዘዙ መሆኑንም” ገልጧል

የያየሰው እስር

የጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ጠበቃ ታደለ ገብረመድኅን ለካርድ እንደገለጹት፣ “ፖሊስ ከፍርድ ቤት ባገኘው የእሥር ማዘዣ መሠረት ያየሰው ለገጣፎ በሚገኘው የአክስታቸው መኖሪያ ቤት በቁጥጥር ሥር ውለዋል።  የታሰሩበትም ምክንያት ሐሰተኛ ዜና አሰራጭተዋል የሚል ነው” ብለዋል።

ያየሰው ሽመልስ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እስረኞች ማቆያ ተወስደዋል። በዚህ የእስረኞች ማቆያ የወዳጅ ዘመድ ጥየቃ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ስለተቋረጠ፣ ያየሰው ሽመልስም ጠያቂ እንዳልተፈቀደላቸው ጠበቃቸው ተናግረዋል። ያየሰው በፌዴራል አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሁለት ጊዜ (መጋቢት 25፣ 2012 እና ሚያዝያ 1፣ 2012) ቀርበው፥ የስድስት፣ የስድስት ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ለፖሊስ ተፈቅዶ እስራቸው የቀጠለ ሲሆን የዋስትና መብታቸውም አልተረጋገጠም።

ዋስትና የተከለከሉበትን ምክንያት ሲገልጹ፣ “ዐቃቤ ሕግ ተጠርጣሪው ተፈትተው ቢወጡ መረጃ ሊያጠፉ ይችላሉ፤ በተጨማሪም ከብሔራዊ መረጃ ደኅንነት የሚመጣ ማስረጃ ስላለኝ በዋስ መለቀቅ የለባቸውም ብሎ አመልክቶ ፍርድ ቤቱም ይህንን በመቀበሉ በድጋሚ ለሚያዝያ 7፣ 2012 ተቀጥረዋል” ብለዋል።

ጋዜጠኛ ያየሰው “በፖሊስ ምርመራ ወቅት ምንጭዎትን አውጡ እየተባሉ” እንደሆነ ጠበቃቸው ተናግረዋል። የተጠረጠሩበት አንቀጽ እስካሁን በይፋ አልተገለጸም። ጠበቃ ታደለ ገብረመድኅን አክለውም “ጋዜጠኛው የለጠፈው ነገር ወንጀል ነው የሚያስብለው ነገር አይደለም፤ ጋዜጠኛው የሚገደደው ማስተባበያ እንዲሰጥ ነው። እሱንም በትዊተር ገጹ ሰጥቷል። እንደውም እርሱ ያደረገው ነገር ሕዝቡ የበሽታውን አስከፊነት አውቆ እንዲጠነቀቅ ነው” በማለት የመንግሥትን ክስ ሞግተዋል።

የኤልሳቤት ከበደ ጉዳይ

ሌላኛዋ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በሐረር በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ተገናኝተዋል በሚል የሥም ዝርዝር ፌስቡክ ላይ ለጥፈዋል በሚል የታሰሩት የሕግ ባለሙያ እና የኢትዮጵያ ሴት የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር (ኢውላ) በጎ ፈቃደኛ ኤልሳቤት ከበደ ጣፋ ናቸው። ኤልሳቤት ከኤውላ በተጨማሪ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) በበጎ ፈቃደኝነት ይሳተፋሉ። የአኢጋን ኤክሲክዩቲቭ ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶ ለካርድ እንደነገሩት “ኤልሳቤጥ በፌስቡክ ገጿ ላይ ስለ ኮቪድ 19 ባሰፈረችው ጽሑፍ ነው የታሰረችው” የሚል ነገር እንደሰሙና በሐረር ፖሊስ ትዕዛዝ መሠረት እንደተያዙ ገልጸዋል

ኢውላም በፌስቡክ ገጹ እንደገለጸው ኤልሳቤት ከበደ ለእስር የተዳረጉት ጥቃት የደረሰባትን ተበዳይ ሴት ይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያ በሔዱበት አጋጣሚ ነው።

“ኤልሳቤት ከበደ በመጋቢተ 26 ቀን 2012 ቅዳሜ በቦሌ አራብሳ ኮንዶሚንየም ጥቃት ሲደርስባት የነበረችን ተበዳይ ለመረዳት በማሰብ ተበዳይዋን ይዛ ወደ ፖሊስ ጣቢያ በሔደችበት ሰዓት ከሐረሪ ክልል የወጣ መያዣ አለ በሚል በዛኑ ዕለት ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተወስዳ እዚያው ካደረች በኋላ ማኅበራችን የሕግ ባለሙያ በማዘጋጀት ስለ ክሱ ለመረዳት እና የሕግ ድጋፍ ለማድረግ ከተወሰኑ አባላቱ እና ከማኅበሩ ዳይሬክተር ጋር ወደ ፖሊስ ጣቢያው እሁድ ጠዋት ያቀናን ቢሆንም ኤልሳቤት ወደ ሐረር የተወሰደች መሆኑ ተገልጾልናል” (የኢትዮጵያ ሴት የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር)

የኢውላ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ሌንሳ ቢየና ከካርድ ስለጉዳዩ ተጠይቀው፣ ኤልሳቤት ከበደ የታሰሩት “በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የኮሮና ቫይረስን በተመለከተ ባሰፈሩት ጽሑፍ” ምክንያት ነው ሲሉ ገልጸውልናል። ይሁን እንጂ “ኤልሳቤት የሐረሪ ክልልን ፕሬዝዳንት በመጥቀሷ ሥም ለማጥፋት በመሞከር ከሚለውም ጋር አገናኝተውታል” ብለውናል።

ታሳሪዋ ከዚህ በፊት ከኢውላ ጋር መልካም ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን፥ ጫልቱ የተባለች እና በሐረሪ ባለሥልጣን የሆነ አሠሪዋ የመድፈር እና የአሲድ መድፋት ጥቃት አድርሶባት በዚሁ ሳቢያ ሕይወቷ ያለፈችን የ14 ዓመት ታዳጊ ሴት የፍርድ ቤት ጉዳይም ይዛው እንደነበር አስታውሰው፣ በዚህም ሳቢያ ዒላማ ሆነው ስለነበር፣ ‘አሁን እየሆነ ያለው ነገር ትክክል አይደለም የምንለው ለዚህ ነው’ ብለዋል ዳይሬክተሯ።

ኤልሳቤት የአዲስ አበባ ነዋሪ ሆና ቋሚ የአዲስ አበባ አድራሻ እያላት ወደ ሐረሪ ክልል ምንም ጉዞ ስታደርግ እና በፍርድ ቤት ቀርባ የተጠረጠረችበት ወንጀል ተፈፀመ የተባለው ሐረሪ የሚያስወስድ ምክንያት ያለው መሆኑ ሳይወሰን፣ ሐረሪ ክስ ቀርቦባታል በሚል አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ፖሊሶች በመታገዝ ወደ ሐረሪ ክልል የተላለፈችበትን አግባብ ትክክል ባለመሆኑ ኮሚሽኑ ምላሽ እንዲሰጥበት ጠይቀናል ብሏል ኢውላ በመግለጫው።

ኤልሳቤት ሐረሪ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሰኞ፣ መጋቢት 28፣ 2012 ቀርበው፣ ለሚያዝያ 13 ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጣቸው ሲሆን፣ የዋስትና መብት እስካሁን አልተከበረላቸውም። ኢውላ በጠበቃዋ በኩል አርብ ዕለት ያስገባው የዋስትና አቤቱታ የፊታቸውን ረቡዕ (ሚያዝያ 7፣ 2012) ሊደመጥ ቀጠሮ እንደተያዘለት ስምረት አንዳርጌ (የኢውላ ሌጋል ኦፊሰር) ገልጸውልናል።

ኦባንግ ሜቶ ለካርድ እንደተናገሩት፣ “ኤልሳ ለምን ታሰረች ለሚለው ጥያቄ በትክክል ምን እንደተፈጠረ አላውቅም፤ ነገር ግን በኮቪድ የተጠረጠሩ ሰዎችን ሥም በፌስቡክ ገጿ ላይ ይፋ አውጥታለች። በለይቶ ማቆያ ውስጥ ይሁኑ ስትል ጽፋለች” ብለዋል። ነገር ግን “የተወሰደባት እርምጃ ግን ትክክል አይደለም” ብለዋል። ኦባንግ የታሰረችበት ቀን ቅዳሜ ቀን ወንጀል ለማመልከት ራሷ ወደ ፖሊስ ጣቢያ በሔደችበት ወቅት ሲሆን፥ የፍርድ ቤት ማዘዣም አላሳዩዋትም ብለዋል።

የመንግሥት ያልተመጣጠነ እርምጃ

ያየሰው ሽመልስ ፌዴራል መንግሥቱ ላይ እና ኤልሳቤት ከበደ የሐረሪ ክልል ላይ የተለያዩ ትችቶችን በመናገር ወይም በመጻፍ የሚታወቁ ሲሆን፥ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የተዛባ መረጃ እና አደጋ ሊያስከትል የሚችል መረጃ አሰራጭታችኋል በሚል ለእስር ተዳርገዋል። አልፎ ተርፎም፣ የዋስትና መብታቸው ሳይከበር በወረርሽኝ ወቅት አደጋ ሊያጋልጥ የሚችል እስር ቤት ለመቆየት ተገድደዋል።

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ይህንን ያልተመጣጠነ እርምጃ በፅኑ ይቃወማል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በተመለከተ የተዛቡ መረጃዎች ስርጭትንም በተመለከተ የተቃዋሚዎችን ድምፅ ማፈኛ መሣሪያ መሆን እንደሌለበት ያሳስባል። ስለሆነም፣ ካርድ ሁለቱም ተጠርጣሪዎች በአስቸኳይ በፍቺ እንዲሰናበቱ ይጠይቃል። ካርድ ተጠርጣሪዎቹ ተላልፈውታል የሚባል የሕግ አግባብ ካለ የዋስ መብታቸው ተከብሮ፣ ጉዳዩን የማየት ሥልጣን ባለው ፍርደ ቤት እንዲቀርቡና በፈጣን እና ፍትሐዊ የሕግ ሒደት ዳኝነት እንዲያገኙ ጥሪውን ያስተላልፋል።

ካርድ እንደዚህ ዓይነቶቹ ስህተቶች እንዳይደገሙ፣ መንግሥት ከያየሰው ሽመልስ እና ኤልሳቤት ከበደ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተፈፀመውን ያልተመጣጠነ እርምጃ እንደ ትምህርት በመውሰድ መንግሥት ኃላፊነት በተላበሰ መልኩ ተመጣጣኝ ለተመሳሳይ ሁኔታዎች ተመጣጣኝ እና ሕጋዊ አግባብነት ያለው የእርምት ሥራ እንዲሠራ ጥሪ ያደርጋል። ስለሆነም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስፈፀሚያ ደንብ ላይ ከሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭት እና አዘጋገብ ጋር በተያያዘ ከላይ የተጠቀሱት አንቀፆች ላይ ያሉት አሻሚ እና ሰፊ ትርጉም ያላቸው ድንጋጌዎች እንዲከለሱ መልዕክቱን ያስተላልፋል። በመጨረሻም፣ የሐሰተኛ መረጃዎችን ስርጭት ለመቀነስ ዘላቂው መንገድ የመንግሥት ግልጽነትን ማሳደግ፣ የብዙኀን መገናኛዎችን የሐቅ ማረጋገጥ ሥራ እና የሲቪል ማኅበራትን የሚዲያ አረዳድ ግንዛቤ ማሳደግ መደገፍ እና ማጠናከር መሆኑን በድጋሚ ለማስታወስ ይፈልጋል።

 

%d bloggers like this: