“አምባገነናዊ መንግሥት ሲመሠረት ተባባሪ ላለመሆን ኃላፊነቴን ለቅቄያለሁ”—  ኬሪያ ኢብራሂም

9 Jun

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒም ሕገ መንግሥት ከሚፈቅደው ውጪ አምባገነናዊ መንግሥት ሲመሰረት ተባባሪ ላለመሆን በገዛ ፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን አስታወቁ።

የአፈጉባኤዋን ሥልጣን መልቀቅ በተመለከተ ወ/ሮ ኬሪያ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት የአገሪቱን “ሕገ መንግሥት በየቀኑ ከሚጥስና አምባገነንነትን ከሚያራምድ ቡድን ጋር ለመስራት ፈቃደኛ ስላልሆንኩ ነው” ብለዋል። አፈጉባኤዋ ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት በሥልጣን ላይ ያለው ወገን “ሕገ መንግሥቱን በግላጭ ተጥሷል አምባገነናዊ መንግሥት ወደ መመስረት ገብቷል” ሲሉ ከሰዋል።

ለዚህም እንደማሳያ ያስቀመጡት ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ያለምርጫ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲል በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያለ ክፍተትን በመፈለግ “አንዱን አንቀጽ ከሌላው ጋር በማጋጨት ክፍተት እንዲገኝና አማራጭ እንዲፈለግ” ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

በሥልጣን ላይ ያለው አካል ካለሕዝብ ውሳኔ ባለበት ለመቆት መወሰኑንና ይህንንም ሕጋዊ ለማድረግ ክፍተት በመፈለግ ሕገ መንግሥታዊ ከሆነው መንገድ ውጪ “ባልተለመደ አካሄድ ሕገ መንግሥቱ እንዲተረጎም ግፊት እየተደረገ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህም አስቀድሞ የተወሰነ መሆኑን ጠቅሰው “ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነው” ብለዋል። ጨምረውም ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔውን በማይቀበሉት ላይ “ማስፈራሪያና ዛቻ” እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ሳቢያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሲሆኑ “ሕገ መንግሥቱን የማክበር የማስከበር አደራ ስለተቀበልኩ፤ ሕገ መንግሥቱ ተጥሶ አምባገነናዊ መንግሥት ሲመሰረት ተባባሪ ላለመሆን” ሲሉ በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን እንደለቀቁ ተናግረዋል።

ጨምረውም “በሕገ መንግሥት ትርጉም ሽፋን የአምባገነናዊ ሥርዓት ሕግ የሚጥስ ድርጊትን ላለመተባበር ወስኛለሁ” ብለዋል ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም።

 

ከሁለት ዓመት በላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ሆነው ያገለገሉት ወ/ሮ ኬሪያ ስለውሳኔያቸው በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት ይህ እርምጃ የአገሪቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የስልጣን ባለቤትነትን የሚጥስ ነው ብለዋል።

ቢቢሲ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ስለ አፈጉባኤዋ ሥራ መልቀቅ ለማጣራት ባደረገው ጥረት ምክር ቤቱ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገልጿል።

 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ አቶ ገብሩ ገብረ ሥላሴ ለቢቢሲ የአፈ ጉባኤዋን ከሥራ መልቀቅ በተመለከተ የቀረበ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

ቢሆንም ግን አፈ ጉባኤዋ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን በሚመለከት የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎችን መመልከታቸውን ገልጸው፤ በጽሕፈት ቤቱ በኩል ግን የቀረበ ይህንን የሚያረጋግጥ ነገር የለም ብለዋል።

የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ የሆነው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ወይዘሮ ኬሪያ በአፈ ጉባኤነት የሚመሩት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አነጋጋሪ በሆነው የሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳይ ላይ በቅርቡ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

/BBC News አማርኛ

 

 

%d bloggers like this: