በሊባኖስ መንግሥታቸው ያልታደጋቸው ኢትዮጵያውያን ጉዳይ የመንግሥትን ምንነት አነጋጋሪ አድርጎታል

24 Jun

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በመካከለኛው ምስራቅ በተለይም በሊባኖስ ችግር ላይ የወደቁ ኢትዮጵያውያን ወገኖችን መንግስትና የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲታደጋቸው ጥሪውን ያቀርባል፤

በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያኖች በሥራና በተለያዬ ምክንያቶች በመካከለኛ ምስራቅ ሀገራት እንደሚገኙ ይታወቃል። በተለይም በሊባኖስ እስከ 150ሺ የሚደርሱ የሀገራችን ዜጎች በቤት ሰራተኝነትና ሌሎች ሥራዎች ተስማርተው በሚያገኟት አነስተኛ ገቢ ቤተሰቦቻቸውን የሚረዱ ሲሆን ለሀገር ምጣኔ ኃብት የሚያደርጉት ድጋፍም ከፍተኛ ነው።

ላለፉት ስድስት ወራት በዓለማችን እየተስፋፋ የመጣው የሳንባ ቆልፍ (covid-19) ወረርሽኝ ለ450 ሺ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ሞትና ማኅበራዊ ቀውስ ምክንያት ከመሆኑም በላይ በሀገራት ምጣኔ ኃብት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ ይገኛል

በተለይም ሊባኖስ ስትከተለው በነበረው የ”ፊስካል” ፖሊሲ ምክንያትና የሳንባ ቆልፍ ወረርሽኝ ባሳደረዉ ተጽዕኖ ምክንያት በከፍተኛ የምጣኔ ኃብት እና የገንዘብ ቀውስ ውስጥ ትገኛልች። በዚህም የሊባኖስ ገንዘብ የሆነው ፖውንድ የመግዛት አቅም ከ100% በላይ የቀነሰ ሲሆን የሀገሪቱ የዋጋ ግሽበትም በከፍተኛ ደረጃ አሻቅቧል። 45% የሚሆነውም የሊባኖስ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች የሆነ ኑሮ ለመግፋት ተገዷል።

በእነዚህና መሰል ችግሮች ምክንያት በሊባኖስ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ለከፍተኛ ችግርና አካላዊ ጥቃቶች መጋለጣቸውን አብን አረጋግጧል። የተሻለ ዕድል የገጠማቸው ናቸዉ የሚባሉትም አሰሪዎቻቸው ከመኖሪያ ቤት ያላስወጧቸው በሚባል ደረጃ ያሉ ሲሆን ደሞዛቸው ለወራት ተቋርጦ በምግብ ችሮታ ብቻ ተወስነዉ ከባርነት ባልተናነሰ ሁኔታ ዉስጥ እየሰሩ እንደሚገኙ በሀገሪቱ የሚገኙ ወገኖቻችን ካደረሱን አሳዛኝ መልዕክቶች እንዲሁም የአብን አመራሮች ከእነዚህ ወገኖቻችን ጋር ካደረጓቸው ውይይቶች መረዳት ተችሏል፡፡

እነዚህ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በተለይም በሊባኖስ ከፍተኛ ችግር ውስጥ የወደቁ ወገኖቻችን ለኢትዮጵያ ኢምባሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶች መንግስት ወደ ሀገራቸው እንዲመልሳቸው ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ቢያቀርቡም አጥጋቢ መልስ እንዳላገኙ፣ ይባስ ብሎም ኢምባሲዎችና ቆንስላዎች በራቸውን እንደዘጉባቸው፣ መልስ የሰጡ ኤምባሲዎችም የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ሀገር ቤት የማጓጓዝና የመመለስም ሆነ በለይቶ ማቆያዎች አቆይቶ ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ የሚያስችል አቅም እንደሌለው እንደተገለጸላቸው አሳውቀውናል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የሳምባ ቆልፍ ወረርሽኝ ባስከተለው ዓለምአቀፍ የጤናና የማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ወገኖቻችን ጉዳይ መንግስት በቸልታና በምንም ማድረግ አልችልም ስሜት ሊያየዉ አይገባም ብሎ ያምናል፡፡

የተለያዩ የኢስያ ሀገራት ዜጎቻቸውን ከሊባኖስ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ጥረት እያደረጉ ሲሆን የኢፌዲሪ መንግስትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና እንደ ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ያሉ ተቋማትን ድጋፍ በመጠየቅ፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር እነዚህን በችግር ላይ የሚገኙ ወገኖቻችን እየደረሰባቸው ካለው እንግልትና ሁለንተናዊ ስቃይ እንዲታደግና በአፋጣኝም ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራ (repatriation) እንዲጀምር አብን ያሳስባል፡፡

የሀገር ኃብት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድም እነዚህን በከፍተኛ ችግር ላይ ያሉና መመለስ የሚፈልጉትን ወገኖቻችንን ወደ ሀገር የመመለስ ሥራ እንዲሰራ፣ መንግስት አመራር እንዲሰጥ፣ ወደ አገር ተመልሰው በለይቶ ማቆያዎች በሚቆዩበትም ወቅት መላ ኢትዮጵያዊያን ሁሉንአቀፍ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው አብን ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል።

የሲቪክ ድርጅቶች፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ ባለኃብቶች፣ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች፣ ቤተሰቦቻቸዉና መላው ኢትዮጵያዊያንም በችግር ላይ የወደቁ ወገኖቻችንን ለመታደግ በመንግስት ላይ የሚቻላቸውን ጫናና ድጋፍ  እንዲያደርጉ አብን ወገናዊ ጥሪውን እያቀረበ የሀገራችንና የሕዝባችን የጀርባ አጥንት የሆኑና አሁን በችግር ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን ለመታደግ በሚደረገው በዚህ ጥረት ዉስጥም ምልዓተ-ሕዝቡን፣ አባላቱንና ደጋፊዎችን በማስተባበር ከመንግስት ጎን እንደሚቆም ንቅናቄያችን ቁርጠኝነቱን ያረጋግጣል፡፡

ራሳችንንና ቤተሰቦቻችንን ከሳንባ ቆልፍ ወረርሽኝ እንጠብቅ!

/የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ National Movement of Amhara 
%d bloggers like this: