በሃጫሉ ግድያ የተቀሰቀሰው ውዝግብና የሕወሃት ምላሽ

10 Jul

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

 

በድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተጠርጥርው አስራ አራት የሚደርሱ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ የታወቀ ሲሆን ግድያው በማንና ለምን ዓላማስ እንደተፈጸመ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

 

የተለያዩ ወገኖች በግድያው ዙሪያ በርከት ያሉ መላምቶችንና ተጠያቂዎችን በማንሳት እየተከራከሩ ቢሆንም እስካሁን ለግድያው ኃላፊነት የወሰደም ይሁን በፖሊስ የተገለጸ ወገን ባይኖርም ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በሚወጡ መግለጫዎች መወነጃጀሎች እየተስተዋሉ ነው።

በግልጽም ባይሆን አንዳንድ ባለስልጣናት ከግድያውና ግድያውን ተከትሎ ሞትን ውድመትን ካስከተለው ሁከት ጀርባ የኦነግ ሸኔና የሕወሃት የተቀናጀ እጅ እንዳለም ከመንግሥት በኩል በሚወጡ መግለጫዎች ተንፀባርቋል።

 

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ባለፈው ሳምንት በድምጻዊ ሃጫሉ የቀብር ዕለት በክልሉ ቴሌቪዥን ላይ ተመሳሳይ ክስ ያቀረቡ ሲሆን የክልሉ መንግሥትም ባወጣው መግለጫ ላይ ይህንኑ ውንጀላ ደግሞታል።

ባለፈው ሳምንት የተከሰተውን አለመረጋጋትና ያስከተለውን ጉዳት በተመለከተ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት አቶ ንጉሡ ጥላሁንም በስም አይጥቀሱት እንጂ ሕወሃት በቀውሱ ውስጥ እጁን እንዳለበት አመልክተዋል።

አቶ ንጉሡ በአገሪቱ ውስጥ አለመረጋጋት ለመፍጠር እየጣሩ ነው ካሏቸው ቡድኖች መካከል የኦነግ ሸኔ ቡድንን በስም ጠቅሰው ሌላኛውን ወገን ደግሞ “ቀደም ሲል በስልጣን ላይ የነበረው ቡድን” በሚል ቃል ጠቁመዋል።

ቀጥለውም ለትግራይ ወጣትና ሕዝብ መልዕከት ያስተላለፉት አቶ ንጉሱ “አፍራሽ ተልእኮ” አለው ያሉትን “ዘራፊው ቡድን የተፈጠረው ብጥብጥና ቀውስን በዋናነት፣ በአዝማችነት፣ በአቃጅነት የሚመራ መሆኑን በመረዳት፣ ይህንን ዘራፊ ቡድን በቃህ ሊለው ይገባል” ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ የሕወሃት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የፌደራል መንግሥት የሚወቅስ መግለጫ አውጥቷል። “በአገርና ሕዝብ ላይ ለደረሰውና ለሚደርሰው ጥፋት ብቸኛው ተጠያቂ የአራት ኪሎው አምባገነን አሃዳዊው ቡድን ነው” ሲልም ከስሷል።

መግለጫው አክሎም “ለይስሙላ ሰላም ፍቅርና ይቅርታ እየሰበከ ወደ ስልጣን ኮርቻ እየተፈናጠጠ” በማለትም “ከውስጥና ከውጪ ያገኘውን ድጋፍ በመጠቀም ስልጣኑን ለማደላደልና ሕብረ ብሔራዊነትን ለማፍረስና አሃዳዊ ሥርዓት ለመመስረት ተጠቅሞበታል” ሲል አስፍሯል።

በአገሪቱ ውስጥ ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በሕወሃት ላይ የሚቀርቡ ክሶችን በተመለከተ በተለይም በድምጻዊው ግድያ ውስጥ ድርጅታቸው አለበት የሚለውን ውንጀላ በተመለከተ የሕወሃት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳን የቢቢሲው ፎከስ ኦን አፍሪካ ፕሮግራም ጠይቋቸው ነበር።

“ለፖለቲካ ጥቅም ሰዎችን የመግደል አማራጭን የሚከተል ድርጅት አይደለም” በማለት የመለሱት አቶ ጌታቸው “ሕወሃት ሰዎችን በማስወገድ ፖለቲካዊ ነጥብ በማስቆጠር የሚያምን ድርጅት አይደለም፤ ይህንንም ለማድረግ ምንም ምክንያት የለውም። ስለዚህ ሕወሃትን በሃጫሉ ግድያ መክሰስ ጭልጥ ያለ ውሸት ነው” ሲሉ ክሱን አጣጥለውታል።

ይልቁንም አቶ ጌታቸው በተራቸው የክሱን አቅጣጫ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩና አጋሮቻቸው አዙረው “የሃጫሉን እንቅስቃሴ የሚቃወሙ ሰዎች ነበሩ። ይህም የሚጠቁመው በጠቅላይ ሚኒስትሩና በዙሪያቸው ወዳሉ ሰዎች ነው” ብለዋል።

አክለውም በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ ለሚከሰቱ ማናቸውም መጥፎ ነገሮች ሕወሃትን ተጠያቂ ማድረግ የተለመደ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው እንዲያውም ጠቅላይ ሚኒስትሩን በአገሪቱ ውስጥ እየተከሰቱ ላሉት ችግሮች ተጠያቂ አድርገዋቸዋል።

በአገሪቱ ውስጥ በአጠቃላይ የተፈጠረውን ችግርም ለመፍታት በገዢው ፓርቲና በሕወሃት መካከል ብቻ ሳይሆን በሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎችና ቡድኖች መካከል ተቀራርቦ በመወያየት ብቻ ለተፈጠረው ቀውስ መፍትሄ ማምጣት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ድርጅታቸው ሕወሃትም ባወጣው መግለጫ ሕዝቡን “በትግልህ ያስመዘገብካቸውን መብቶች ላለማስነጠቅ ብቻ ሳይሆን አምባገነናዊ አሃዳዊ ኃይሎች በማንኛውም መስክ የሚሸርቡትን ሴራ ለመመከትና ሕብረ ብሔራዊ ፌደራላዊ ሥርዓቱን ከጥፋት ለመታደግ ከመሰል ኃይሎች ጎን ተሰልፈህ በቁርጠኝነት ለመታገል ዝግጁነትህን ይበልጥ አጠናክር” ሲል ጥሪ አቅርቧል።

አክሎም የክልሉን ሕዝብ “ለወሳኝ ፍልሚያ በተጠንቀቅ እንዲቆም” ጥሪ አስተላልፏል።

ሕወሃት የኢህአዴግ ወራሽ ከሆነው የብልጽግና ፓርቲ እራሱን ካገለለ በኋላ ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸ አሁን ካለበት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

በተለይ ብሔራዊው ምርጫ በኮሮናቫይረስ ምክንያት መራዘሙና በስልጣን ላይ ያለው አስተዳደር ቀጣዩ ምርጫ እስኪካሄድ እንዲቀጥል ከተወሰነ በኋላ ውዝግቡ የበለጠ እየተካረረ መጥቷል።

ከሃጫሉ ግድያ እንዲሁም ተከትሎ በተከሰተው ሁከት ዙሪያ መካሰሱ እየተባባሰ መጥቶ በግልጽ መወነጃጀልና ሕወሃትም ለሕዝቡ ቀጥሎ ለሚከሰተው ነገር እንዲዘጋጅ ጥሪ አቅርቧል። በቀጣይ ምን ሊከሰት እንደሚችል መገመትም አስቸጋሪ የሆነ ሲሆን የከፋ ነገርም እንዳይመጣም በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ያስጠነቅቃሉ።

/BBC Amharic

 

ተዛማጅ:

“ከመረጃ ፍሰት ይልቅ የሕዝባችንን ህይወት ማዳንን ቅድሚያ ሰጥተናል”
—ዛዲግ አብርሃ

 

%d bloggers like this: