ጠሚ ዐቢይ ማን ላይ ነው ጥርስ የነከሱት—ፌዴራል ኦዲተር ጄነራሉ ላይ? በሪፖርቶቻቸው ወይንስ በሙያቸው ግንባር?

17 Jul

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

 

ኦዲተር ጄኔራል ገመቹ ዱቢሶን ከሚዲያ ውጭ አላውቃቸውም።

 ከዚህ በታች የሠፈረው ምሥክርነቴ ቢነበብ፣ አቶ ገመቹ ዱቢሶ ልባቸው በሃገር ፍቅር የተሞላ ዜጋና የተዋጣላቸው ባለሙያ ናቸው የሚለው ቃሌ ሃቀኛና ከበሬታ ላይ የተመሠረተ ነው።

ውጭ ሃገር በመንግሥት ሥራ ላይ በነበርኩበት ወቅት የፌዴራል ኦዲተር ጀነራል ሪፖርት አንድ አስተማሪና ገንቢ የመረጃ ምንጬ ነበር። ሃገራችን ታዳጊ እንደመሆኗ የኦዲተሩ ቢሮ በተለይም ስለሃገራችንና ችግሮቿ፥ ስለመንግሥታዊ መዋቅሮቿ፥ የኢኮኖሚ ፕላን አፈጻጸም ማነቆቿ እጅግ ጠቃሚ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

ኦዲተር ጂኔራሉ ቀዳሚው ዓላማቸው፣ ሃገሪቱንና ሕዝቧን ተጠቃሚ ማድረግ ቢሆንም፡ በሥራቸው የሚያጋልጧቸው በየመሥሪያ ቤቱ ለዘረፋ የተቀመጡ ‘ጎረምሶች ባለሥልጣኖች’ ጥርሳቸውን ሲነክሱባቸው ኖረዋል።

እስካሁን በሥራችው ምክንያት የመጣባቸው ነቀፌታ አላጋጠመኝም።

 

ከተመድ የቀሰምኩት

ተ.መ.ድ. ዓለም አቀፍ ሠራተኛው እንድሆን ሲወሰደኝ፣ የተቀላቀልኩትም  Office for Programme Planning & Budget ስለነበር፥ ላካፍል የምወደው የቀሰምኩት ልምድና ትምህርት አለ። በዚህም ምክንያት በዴስክ ደረጃ ኃላፊነታቸውን የተቀበልኳቸውን የተ.መ.ድ. ፕሮግራሮሞችና በጀቶችማለትምUNEP, UNECA, UNCTAD, UNHabitat, UNSCARE, ECE, ESCAP እና ESCWA—ማስተዳደርና የፕሮግራሞቹን አፈጻጸም በማንዴቶቻቸው መሠረት መከናውናቸውን መከታተልና ማጣራት ግዴታዬ ነበር። 

የዚህም ዓላማ ቁጥጥር ብቻ ሣይሆን፡ በፕሮግራም ዝግጅት ዓመት የፕሮግራሞቹን አፈጻጸም ለወደፊቱ ለማሻሻል በሰው ኃይል ድልድልም ሆነ በገንዘብ ሥርጭት ሃሣብ አቅርቦ ከፕሮግራሙ አስፈጻሚዎች ጋር ለመምከርና ተከታይ የፕሮግራሞች አቀራረጽና የአፈጻጸሞቻቸው ፍሬያማ ለማድረግ የሚያስችል ነው።

በዚህ ውስጥ በምንም መልክ ልናልፍ የማንችለው በኦዲተሮች Observation ውስጥ የተነሱና የተካተቱ ጥያቄዎችና አዳዲስ ሃሣቦች ያላቸው ከፍተኛ ግምትና ከፖለቲካውም አንፃር ክብደት የሚሠጠው ነው።

 

የኦዲተር ጄነራሉ ለዓላማ መቆም

እስከ 2011 (ግሪጐርያን) በሃገራችን የነበረውን ደበዝ የበጀት አዘገጃጀትን፡ በ2012 Result Based Budgeting ‘መተካት’  ጥረት ቢደረግም አልተጠናቀቀም።  የፕሮጄክቶች አፈጻጸምን ከተጠቃሚው ሕዝብ ጥቅሞች አንጻር የተመደበ በጀት ዓላማ ምን እንደሆነና ምን ውጤት እንደሚጠበቅ ለተጠቃውሚው ሕዝብ የሚያሳይ በመሆኑ፡ ሕወሃት ለሕዝብ እንዲህ ግልፅ መሆን የሚያስከትለውን በመፍራት በእንጭጩ ስለከረከመው ሣይጠናቀቅ በፎርም ብቻ ቀርቷል። 

የኢትዮጵያ ፌዴራል በጀት ዋናው ችግር፥  በግብር ከፋዩ የሚሽፈነውን የመንግሥት በጀት ማንም ያለተጠያቂነት  የሚሸመጥጠው ከመንገድ ዳር ያለ እሸት ጋር ይመሳሰላል። ሕወሃቶች የፈለጉት ፍሬውን በመሆኑ፥  የሚበሉት ባለሥልጣኖችና ባለሙያዎቹና ገበያ ውስጥ ያሉ ነጋዴዎች መሆናቸው ብዙ ጊዜ ይነሳል።

የበጀቱ አዘገጃጀትና የሚያካፍላችው መረጃዎች የተሸበቡ ናቸው—በዓላማውና አሠራሩ Result Based Budgeting ተጠቃሚው ሕዝብ ለምን ይህ አልተደረገልኝም የሚለውን ባለሥልጣኖች መስማት ሰለማይፈልጉ መረጃው አይወጣም—ተጠያቂነትን ስለሚያስከትል።

ኦዲተር ጂኔራሉ ቀዳሚው ዓላማቸው፣ ሃገሪቱንና ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ ቢሆንም፡ በሥራቸው የሚያጋልጧቸው በየመሥሪያ ቤቱ ለዘረፋ በኃላፊነት የተቀመ  ‘ጎረምሶች’ ጥርሳቸውን ከመንከስ አልፈው፥ የየመሥሪያ ቤቶቻቸውን ትብብር ሲነፍጓቸው ከርመዋል። እስካሁን ከሥራ አፈጻጸማቸው አንፃር የመጣባቸው ነቀፌታ አይሰማም።

ዘራፊዎች የግብር ከፋዩን ሕዝብ ያባከኗቸው ገንዘቦች መጠንም በየጊዜው በብዙ ቢሊዮኖች መሆኑ እየተገለጸም፡ በመንግሥት ደረጃ ቅጣት ቀርቶ ነቀፌታ እንኳ አይደርስባቸውም!

መንግሥትም በዘመነ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የኦዲተር ጂኔራሉ ዘገባ ለፓርላማ ቢቀርብም ለዓመታት ዘራፊዎች የሚቀራመቱት በጀት መሆኑን ማንም መካድ አይችልም! 

የፓርላማ አባላትም ትላንትናም ሆነ ዛሬ—ማንም ኢትዮጵያዊ እንደሚያውቀው—በፓርላማው ተገዥነታቸው ለጠረነፋቸው ገዥ ፓርቲ እንጂ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም አለመሆኑ ግልጽ ነው።

 

የወቅቱ ትኩረት: ዐቢይ አሕመድና የኦዲት ጥላቻው

አንድ የሚያሳዝነኝ ነገር በሃገራችን  ለምን ባለሙያ እንደማይበረክት ነው። አጋጣሚ ባልሆነ ምክንያት የ2019 የሰላም ኖቤል ተሻላሚው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም፣ ገመቹ ዱቢሶ ባይኖሩ የሚመርጡ ሆኖ ተሰምቶኛል። ፓርላማ ውስጥ በአንድ ወቅት ዐቢይ ‘መንግሥት የፈለገውን ማድረግ ይችላል’ ብለው ስሜታቸውን ሲለቁ፥ ያ ራሳቸን ከሕግ በላይ የማድረግ ፍላጎታቸው በመሆኑ፡ እኝህ ሰው ቢመቻቸው ምን ያደርጉ ይሆን ያልኩበት ጊዜ ነበር።

ስለሃገር ታማኝነትን እያቀነቀኑ፣ የትሬዠሪው በር ግን ለእርሳቸው ክፍት እንዲሆን የሚሹ ይመስላል! ይህ ገጽታ አይበጃቸውም።

ዐቢይ ቢመቻቸው ኦዲተር ጂኔራል ገመቹ ዱቢሶ—በሹመትም ሆነ በሌላ ዞር እንዲሉላችው ፀሎት ሳያደርጉም አይቀርም!

የኦዲተር ሪፖርት ተደምጦ ተግባራዊ ባይሆንም በዘራፊው ሕወሃት ዘመን እንኳ የዘንድሮው አልተደረገም።  ለምን ይሆን አሁን እስከናካቴው እንዳይሰማ የተደረገው? ሪፖርተር በሃጫሉ ሁንዴሣ ግድያ ምክንያት ነው የሚል ገድምዳሜ ዘግቧል።

ያለፈው ዓመት በጀት አፈጻጸምና የመጭው ዓመት በጀት ላይ የኦዲተር ጄኔራሉ ሪፖርቶች የፓርላማ አባላቱን ዕይታ ለማገዝ እጅግ ጠቃሚ ናቸው።

በፓርላማ መደመጡ ያስፈለገበት ወቅት ካለፈ በኋላ፡ አሁን ቀነ ቀጥሮ ይዞ ለዚህ መስብሰቡ ፋይዳው ምን ይሆን—የልምድ እሥረኞች ከመሆን ውጭ? በኦዲተሩ ሪፖርት ውስጥ ምን አንዳለ ባላውቅም፡ ከመደበኛ የመንግሥት መ/ቤቶች ውጭ  ለተለያዩ ፕሮጄክቶች የወጣ ብር 44 ቢሊዮን ደብዛው ጠፍቷል።

ኦዲተር ጄነራሉ ግን ዘንድሮ ባለመሰማታቸው ተቃውሟቸውን በሚዲያ አሰምተው፥  ለሕዝቡ እንደሚለቁት ገልጸዋል!

ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተሸፋፈነውን እንዲያውቅ፡ እንደሚፈልጉም አስታውቀዋል —ብዙ የሚያጋልጡት ጉድ ስላለ ይመስላል። አንዳቸውንም ዘገባቸውን የፓርላማ አባላ ሳያዩት፣ ያላንዳች የኦዲተር ጄኔራሉ ሪፖርት ተዋጽዖ ለ2013 (በኢትዮጵያ) 476.12 ቢሊዮን ብር ጸድቋል!

ለብርቱ የበጀት አፈጻጸም የኦዲተር ጄነራሉ አስተዋጽዖ እጅግ አስፈላጊ ነበር። በብልጽግና አባላት የታጀለው ፓርላማ፡  ያላንዳች ተቃውሞ በጀቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደፈለጉት አጽድቀውታል። ይህ መዋቅሮችንና ተጠያቂነትን የሚያደበዝዝ አሠራር ሃገራችንን ወደከፋ በዘፈቀደ አሠራርና አስተዳደር እንድትገዛ የሚያደርግ አቅጣጫ ነው! ከመንግሥታዊ አሠራር አንፃር፥ ይህ ቁልቁለት ብዙ ያስፈራል!

ኢትዮጵያ አደጋ ላይ መውደቋን ሁሉም ዜጎች ሊገነዘብ ይገባል።

ሁሉንም ዜጎች ሊያሳስብ የሚገባው ጉዳይ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አያሌ ቢሊዮን ብሮች ቢጠፉ፡ የሕወሃት አስተዳደር ደንታ አልነበረውም!  (አሁን ግን ስገምት)  ዛሬ የዐቢይ አስተዳደር ኦዲተሩን ንቆ በበጀቱ ውይይት እንዳይታይ ሲገፋ፣ የፀደቀውን በጀት ነገ ማን ሊቆጣጠረው ይሆን?

የፓርላማ አባላት ስለሪፖርቱ አለመደመጥ ያሉት ነገር የለም። 

ዘራፊዎቹስ ለምን ከእንግዲህ ኦዲተር ጀኔራሉን ያክብሩ፣ ያዳምጡ! 

 

/ፎቶ ሪፖርተር

 

 

%d bloggers like this: