Tag Archives: Gen. Tsaere Mekonnen

የAddis Fortune ጋዜጠኛ ፋሲካ ታደለ ከጄኔራል አሣምነው ጽጌ ጋር በመጀመሪያዎቹ ሰዓታት ስላደረገችው ቃለ መጠይቅና ይዘት!

4 Jul

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

 

ዜጠኛ ፋሲካ ታደሰ (ፎቶ ቢቢሲ አማርኛ)

 

“መፈንቅለ መንግሥት ብሎ ነገር የለም። መፈንቅለ መንግሥት በየመንደሩ አይደረግም። መፈንቅለ መንግሥት ሊደረግ የሚችለው ማዕከላዊ መንግሥት ላይ ነውና ይህ ከእውነት የራቀ ነው። ምናልባት የምጠረጥረው የፌዴራል መንግሥት ወደ ክልሉ ለመግባት ፈልጎ የሠጠው ምክንያት ይሆናል ብዬ ነው የምገምተው”

—ጄኔራል አሣምነው ጽጌ

 

ሰኔ 15 ምን ይመስል ነበር?

ጋዜጣችን የእሑድ ጋዜጣ ነው፤ ቅዳሜ ምሽት ሁልጊዜም ቢዚ ነው። ጋዜጣውን ቅዳሜ ማታ ነው ማተሚያ ቤት የምናስገባው። ቅዳሜ ሁልጊዜ የሩጫ ቀን ነው።

በዚህ ሩጫ ውስጥ ሆነሽ የባሕርዳሩን ክስተት ለመጀመርያ ጊዜ ስንት ሰዓት ላይ ሰማሽ? ምንድነው የሰማሽው? ከማንስ ነው የሰማሽው?

በትክክል ሰዓቱን አላስታውስም። ግን ከ1፡30 እስከ 2፡00 ሰዓት ባለው ይመስለኛል። ቢሮ ነበርኩ፤ ያው ጋዜጣውን ጨርሰን ወደ ማተሚያ ቤት ለመላክ እየተሯሯጥን ነበር፤ ስለ ባሕርዳር የሰማንበት ሰዓት። ከአለቃዬ ተደውሎ ነው የተነገረኝ። ባህርዳር ላይ ችግር አለ እየተባለ ነው እስኪ አጣሪ ተባልኩ።

የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ የቀብር ሥነ ሥርዓት ተፈፀመ

 

ከዚያስ?

ያው ክልሉ ላይ አንዳንድ ነገሮች ሲኖሩ የምናጣራው ወደ ክልሉ ኮሚኔኬሽን ኃላፊ አቶ አሰማኸኝ ጋ [በመደወል] ነው። አጋጣሚ እሱ ጋ ስንደውል እኔም ባልደረቦቼም፤ የሱ ስልክ አይሰራም ነበር። ፖሊስ ኮሚሽን፣ ጸረ ሙስና… ብቻ ሰው እናገኛለን ብለን የምናስባቸው ሁሉ ጋ ስንደውል ነበር።

የጄኔራሎቹና የአዴፓ አመራሮች ግድያ፡ ሙሉ እውነቱን ማን ይንገረን?

 

ከክልሉ ባለሥልጣናት መሀል በስም የሚታወቁ ሰዎች ጋ ደውለሻል።

አንድ ረዳት ኮሚሽነር ሰኢድ የሚባል ሰው አለ በክልሉ፤ እሱ ጋ፣ አቶ አሰማኸኝ ጋ ሌላ በስም የማላውቃቸው ጋ፣ [እንዲሁም ደግሞ] አማራ ክልል ያሉ ጋዜጠኞች እነዚህ ጋ ብትደውይ ያሉኝ ሰዎች [ዘንድ] አንድ አራቱ ጋ ደውያለሁ…

 

ሁሉም አያነሱም?

የአቶ አሰማኸኝ አይሠራም ነበር። የፖሊስ ኮሚሽን ያለው ልጅም አይሠራም። ሌሎቹ ግን ስልክ አያነሱም።

 

ዶ/ር አምባቸው ጋ ደውለሽ ነበር?

አልደወልኩም፤ የርሳቸው ኮንታክትም የለኝም።

 

ከዚያ ጄኔራል አሳምነው ጋ ደወልሽ?

አዎ መጨረሻ ላይ «ቆይ… ለምን የክልሉ ጸጥታ ክፍል ኃላፊ ጋ አልደውልም?» ብዬ ወደርሳቸው ጋ ደወልኩኝ። ከዚህ በፊትም ለአንድ ጉዳይ ደውዬላቸው ነበር። ስልካቸውም ነበረኝ።

 

ለምን ቆየሽ ግን? ከዚያ በፊት ትደዋወሉ ከነበረና በዚያ ላይ ጉዳዩ የጸጥታ ጉዳይ በመሆኑ በቀጥታ እሳቸውን የሚመለከት ሆኖ ሳለ ለምን እርሳቸው ጋ መጀመርያ አልደወልሽም?

እርግጠኛ አይደለሁም ለምን ቀድሜ እሳቸው ጋ እንዳላሰብኩኝ። መጀመርያ የመጣልኝ ኮሚኔኬሽን ቢሮው ኃላፊ ጋ ነበር። ከቆየሁ በኋላ ነው እርሳቸው ጋ መደወል የመጣልኝ። በመሀልም የከተማውን ነዋሪዎች ለማነጋገር እየሞከርን ነበር። «የት አካባቢ ነው ተኩስ ያለው? የተጎዱ ሰዎች አሉ ወይ?… እሱንም ለማጣራት እየሞከርን ነበር በመሀከል። መጨረሻ ላይ ግን እርሳቸው ጋ ነው የደወልኩት።

ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ መገደላቸው ተገለጸ

 

እርሳቸው ወዲያው አነሱት?

ወዲያው። [እንዲያውም] ሁለት ጊዜ ይመስለኛል የጠራው።

 

በዚያ ሰዓት ተጠርጣሪ እንደሆኑ ታውቂያለሽ?

ምንም የማውቀው ነገር የለም

 

ምን ተባባችሁ?

ደወልኩኝ አነሱ። እራሴን አስተዋወቅኩ። ከአዲስ አበባ እንደምደውልላቸው የምሠራበትን መሥሪያ ቤትና ለምን እንደደወልኩ አስረድቼ ክልሉ ላይ ያለውን ነገር ምን እንደሆነ አንዲያስረዱኝ ነበር የጠየቅኳቸው።

 

ምን አሉ?

ባህር ዳር ከተማ ላይ አንድ አንድ ግጭቶች እንዳሉ እና ጉዳቶችም እንደደረሱ ነገሩኝ። ‘ስፔሲፊክ’ እንዲሆኑልኝ ስለፈለኩኝ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የፕሬስ ሴክሬቴሪያት ኃላፊው አቶ ንጉሡ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው ብለው መግለጫ ሰጥተዋል እና እርስዎ ግን ግጭት ነው ያሉኝ ስላቸው «መፈንቅለ መንግሥት ብሎ ነገር የለም። መፈንቅለ መንግሥት በየመንደሩ አይደረግም። መፈንቅለ መንግሥት ሊደረግ የሚችለው ማዕከላዊ መንግሥት ላይ ነው፤ እና ይህ ከእውነት የራቀ ነው። ምናልባት የምጠረጥረው የፌዴራል መንግሥት ወደ ክልሉ ለመግባት ፈልጎ የሰጠው ምክንያት ይሆናል ብዬ ነው የምገምተው» አሉኝ።

ከዚያ «መፈንቅለ መንግሥት ካልሆነ [ታዲያ] ምንድነው ‘ስፔሲፊካሊ’ ያለው ነገር ስላቸው «እሱን አሁን መናገር አንችልም፤ ምክንያቱም እኛ ምርመራ ላይ ያለነው፤ እያጣራን ነው። እሱን እንደጨረስን እናሳውቃችኋለን» አሉን።

“ብ/ጄነራል አሳምነው በባጃጅ ለማምለጥ ሲሞክሩ ነው የተገደሉት”

መቼ ነው የምታሳውቁን ስላቸው [ደግሞ] «ነገ ጠዋት በተወሰነ መልኩ ምርመራውን ስለምንጨርስ መግለጫ እንሰጣለን» አሉኝ ከዚያ ተሰነባብተን። ከዚያ በፊት ግን የመጨረሻ ጥያቄ ብዬ «ተኩስ አለ ይባላል፤ አሁንም ድረስ አልተረጋጋም ወይ?» ስላቸው «እኔም አልፎ አልፎ ተኩስ ይሰማኛል» አሉኝ።

«መከላከያ ገብቷል ስለሚባለውስ ነገር?» ስላቸው «እሱ ላይ ኮሜንት ማድረግ አልችልም፤ የማውቀው ነገር የለም አሉኝ፤ ከዚያ በኋላ ብዙም ጥያቄ ለመመለስ ፍላጎት አልነበራቸውም። የሚሉኝ የነበረው «ምርመራ ላይ ነን፤ እያጣራን ነው፤ አልጨረስንም፤ እሱን እንደጨረስን ነገ ጠዋት መግለጫ እንሰጣለን» የሚል ምላሽ ነበር የሰጡኝ።

 

ያወራሽው እርሳቸውን ስለመሆኑ ምን ያህል እርግጠኛ ነሽ?

ከርሳቸው ድምጽ ጋ ‘ፋሚሊያር’ ነኝ። [ድምጻቸው ለኔ አዲስ አይደለም]

 

ለምን እንደዛ አልሽ?

ከዚያ በፊት አውርቻቸው አውቃለሁ፤ እንደነገርኩህ። ክልሉ ላይ በነበሩ ጉዳዮች በጸጥታ ጉዳዮች አውርቻቸው አውቃለሁ’ኮ

 

አንቺ ግን ያውቁኛል ብለሽ ታስቢያለሽ?

ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱ [ከዚህ ክስተት በፊት] የስልክ ልውውጦች ነበሩን። ‘ሜሴጄም’ አድርጌላቸው አውቃለሁ። ከዚያ በፊት በነበሩ ሁኔታዎች ማለቴ ነው። ምክንያቱም [ከዚህ ክስተት በፊት በነበሩ አጋጣሚዎች] ቴክስት ሳደርግላቸው ስብሰባ ላይ ነኝ እያሉ ይመልሱልኝ ስለነበር ስደውልላቸውም ራሴን አስተዋውቄ እንደዚህ ዓይነት ዜና እየሠራሁ ስለሆነ [ላናግርዎት ፈልጌ ነው] ብዬ ጽፌላቸው ስለማውቅና ስለመለሱልኝም ያውቁኛል ብዬ አስባለሁ፤ ላያውቁኝም ይችላሉ።እርግጠኛ አይደለሁም ግን።

 

አንቺ ግን አርሳቸው ስለመሆናቸው ይቺን ታህል ጥርጥ የለሽም ማለት ነው?

አዎ! አርግጠኛ ነኝ፤ ድምጻቸውን በደንብ አውቀዋለሁ። ስልካቸውም የርሳቸው ነው፤ የተሳሳተ ስልክ አይደለም።

 

ብዙ ጊዜ ድምፅ ስሜትን የመግለፅ ጉልበት አለው ብዬ አምናለሁ። እንው በደወልሽላቸው ሰዓት እሳቸው ላይ መረበሽ ተሰምቶሻል? ከጀርባ የሚሰማ የተኩስ ድምፅስ ነበር?

በጣም ፀጥ ያለ ቦታ። በቃ ድምፅም ጩኸትም ተኩስም የሌለበት ቦታ ነበር የነበሩት። ድምፃቸውም በጣም የተረጋጋ፤ሲያናግሩኝም ተረጋግተው ነበር።

 

ከሰማናቸው ነገሮች አንፃር መረጋጋታቸውና ፀጥታው የሚጠበቅ አይደለም። እንዴት እንደዚያ የተረጋጋ ድምፅ ሊኖራቸው የቻለ ይመስልሻል? ግምትሽ ምንድን ነው?

እርግጠኛ አደለሁም ግን የጦር ሰው ናቸው አደል። ብዙ ጊዜ የእንደዚህ ዓይነት ሰዎችን ስሜት ከድምፃቸው መረዳት የምንችል አይመስለኝም። የተባለው ነገር በእርግጥም ሆኖ ከነበረ መደናገጥና መረበሽ ያልሰማሁባቸው ወታደራዊ ሰው በመሆናቸው ነው ብዬ እገምታለሁ። ግን አሁንም እርግጠኛ መሆን አልችልም።

 

በደወልሽላቸው ሰዓት የክልሉ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ ሌሎችም ሰዎች ተገድለዋል። እና ያንን ጉዳት አደረሰ የሚባል ሰው በዚያ መረጋጋት ማውራትና የክልሉን የፀጥታ ሁኔታ ማብራራት፤ በማግሥቱም መግለጫ እንሰጣለን ሲሉ ከድምፃቸው ምንም ነገር መረዳት አለመቻል ለማመን አይከብድም? አንቺ ራስሽ አሁን ላይ ስታስቢው አይገርምሽም?

በርግጥ ግልፅ ቃለምልልስ ስለነበር ድምፃቸውን እቀርፅ ነበር። በሰዓቱ ከሰማሁት ነገር አንፃር እኔም ተረጋግቼ አልሰማኋቸው ይሆናል ብዬ በኋላም ደጋግሜ ሰምቼው ነበር፤ ድምፁን ግን አሁንም በጣም የተረጋጋ ድምፅ ነው ያላቸው።

 

ድምፃቸውን ቀድተሻል ብዬ አላሰብኩም ነበር። የስልክ ንግግራችሁ የስንት ደቂቃ ነበር?

ሶስት ደቂቃ ከ18 ሰከንድ መሰለኝ። አንዴ ቆየኝ እንዳላሳስትህ ቼክ ላድርገው።[ከአፍታ ቆይታ በኋላ] አዎ በትክክል ሦስት ደቂቃ ከ18 ሰከንድ ነው።

 

የደወልሽላቸው ስንት ሰዓት ነበር?

2፡29 ላይ ነበር።

 

በዚህች ደቂቃ ነው ያን ሁሉ ሐሳባቸውን የሰጡት?

አዎ!

 

ንግግራችሁን ለመቋጨት ይሞክሩ ነበረ? ጋዜጠኛ ስለሆንሽ ተጨማሪ ጥያቄዎችን እንደምታከታትይባቸው እገምታለሁ?

አዎ እንደዛ ነበረ። አንድ ሁለት ሦስት ጥያቄ መጀመሪያ ከመለሱ በኋላ ምርመራ እያደረግን ነው። እሱን ስንጨርስ ነው መናገር የምንችለው ነበር መልሳቸው። እኔ ግን በተደጋጋሚ ያለኝን ጥያቄ ሁሉ እጠይቃቸው ነበር። ምላሻቸው ያው እያጣራን ነው ነበር። ለምሳሌ ስሞች ጠቅሼ እነ እገሌ ጉዳት ደርሶባቸዋል እላቸው ነበር። ሌላ [ቅድም] ያልነገርኩህ ነገር የደረሰ ጉዳት? ስላቸው የክልሉ መስተዳደር አካባቢና የፓርቲ ጽ/ቤት ላይ ነው ጥቃት የደረሰው የሚል መልስ ሰጥተውኝ ነበር።

 

እሳቸው ግን በስም የጠቀሱልሽ ግለሰብ የለም?

እኛ ዜና ሰርተን ስለነበር እነ ዶ/ር አምባቸውን ስም ጠርቼ እነሱ ላይም ጉዳት ደርሷል ይባላል ስላቸው «ሊደርስም ላይደርስም ይችላል፤ እሱን እርግጠኛ ሆኜ መናገር አልችልም። እሱን የምናውቀው ምርመራችን ሲያልቅ ነው ነበር ያሉኝ።

 

ለምን እንደዛ ያሉሽ ይመስልሻል? ምትገምቻቸው ነገሮች አሉ?

ብዙ ነገር ሊሆን ይችላል ግን ይሄ ነው፣ ይሄ ነው ብሎ መገመትና መናገር ይከብደኛል። ነገሩ ገና በምርመራ ላይ ያለና ያልተቋጨ ነው። በምርመራ ሂደት ላይ ያለ ነገር ላይ [analysis and hypothesis ] መሥራት ከባድ ነው።

 

ሁልጊዜ የስልክ ንግግርሽን የመቀርጽ ልምድ አለሽ? ይሄን የምጠይቅሽ ከዚህ በፊትም የእሳቸው ተብሎ የወጣ ድምፅ ስላለ ነው። እሱ ቅንብር ነው፤የመንግሥት የስለላ መዋቅር ያሰናዳው ነው የሚሉ ነገሮች ተነስተውበታል። ምናልባት አንቺም በተመሳሳይ ልትጠረጠሪ የምትችይበት ዕድል ይኖራልና እንዴት ነው የምናምንሽ? በፊትም የመቅዳት ልምድ ነበረሽ ወይ? ስልክሽ ላይ የተጫነ ሶፍትዌር ነው ወይስ ስቱዲዮ ገብተሽ ነበር የደወልሽላቸው?

አይ ስልኬ ላይ [recorder]አለኝ። ለሥራ ቃለምልልስ በማደርግበት ጊዜ [on] አደርገዋለሁ። የግል ስልኮችን አልቀርጽም። ብዙ ጊዜ ለሥራ መደበኛ የቢሮ ስልኮችን ነው የምንጠቀመው። ግን የግል ስልኬን ስጠቀም እቀርፃለሁ። የዚያን ዕለት እንዲያውም የቢሮ ስልክ ነበር ልጠቀም የነበረው፤ ግን ሌሎችም ልጆችም ስለጉዳዩ እያጣሩ ስለነበር ነው ስልኬን የተጠቀምኩት።

 

ከድምፅ ጋር ተያይዞ በቅርቡ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ብርጋዲየር ጀነራል አሳምነው ጋር ያደረጉት ንግግር ወጥቷል። ያንን ድምፅ ጥያቄ ውስጥ የሚከቱት ሰዎች አሉ። አንቺ እሳቸውን በድምፅ እለያቸዋለሁ ስላልሽን ስለዚህ ድምጽ ምን ልትይን ትችያለሽ?

የሳቸው ድምፅ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። እንዳልኩህ ድምፃቸውን አውቃለሁ ሰምቼ፤ ደጋግሜ ስለሰማሁት እለየዋለሁ። እንዳልኩህ የሳቸው ድምፅ ይመስለኛል። “ኦዲዮው” ትክክል ነው፣ አይ ትክክል አይደለም፣ ተሰርቶ ነው በሚለው ላይ አስተያየት ባልሰጥ ደስ ይለኛል።…

 

ስትሰሚው ግን ላንቺ የተሰማሽ ስሜት ምንድን ነው? ጄኔራል አሳምነው ናቸው ነው ያልሽው? የመጀመሪያ ስሜትሽ ምንድን ነው?

ይቅርታ እዚህ ላይ በጭራሽ ምንም ኮሜንት ባላደርግ ደስ ይለኛል።

 

አወዛጋቢ ስለሆነ ነው?

አዎ ! የምልህ ጉዳዩ (ኬዙ) በደንብ ያልለየለት ነገር ነው፤ በዚህ ወቅት ምንም ብል የአንድን ሰው ሐሳብ እንደ መከራከሪያ ተደርጎ ፒክ ይደረጋል እና ቢቀር ነው የሚሻለኝ፤ እርግጠኛ ሆኜ ኮሜንት ማድረግ አልችልም።

 

እርሳቸውን ካናገርሻቸው በኋላ በምን ፍጥነት ነው ፌስቡክ ላይ ፖስት ያደረግሽው?

በጣም ቆይቻለሁ! ካናገርኳቸው “አይ ቲንክ” ሰላሳ አርባ ደቂቃ የቆየሁ ይመስለኛል። ምክንያቱም የጋዜጣውን ሥራ መጨረስ ስለነበረብን እሱን ጨርሰን ልክ ወደ ማተሚያ ቤት ከተላከ በኋለ ነው፤ ያንን ፖስት ያደረግኩት፤ አንድ ሰዓት ወይ እንደዚህ !

 

ፌስቡክ ላይ ስትለጥፊው ተጠርጣሪ እንደነበሩ ታውቂ ነበር?

በፍፁም አላውቅም፤ ከቢሮ ከወጣሁ በኋላ ፌስቡክ አካውንቴ ላይም ያንን ነገር «አብዴት» ካደረግኩ በኋላ አጋጣሚ ወደ መንገድ ነው የወጣሁት። ወደ አዳማ እየነዳሁ ነበር። በመሀሉ ብዙ ስልኮች ይደወሉ ነበር። የምሄድበት ቦታ ስደርስ ሌሊት ነው። ኢንተርኔት ተቋርጦም ስለነበር ምንም የሰማሁት ነገር የለም። በማግስቱ ጥዋት ነው አማራ ቴሌቪዥን ላይ እሳቸው ተጠርጣሪ ናቸው መባሉን የሰሙ ልጆች ደውለው የነገሩኝ። አጋጣሚ ያለሁበት ቦታ መብራት አልነበረምና ተጠርጣሪ ናቸው ወይም አሉበት ብሎ መንግሥት እንደሚጠረጥራቸው የሰማሁት ከሰው ነው።

 

ከክስተቱ በኋላ በጣም ብዙ ጥያቄዎች ይነሱ ነበር። ብዙ ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች ነበሩ። ምናልባትም ብቸኛው መረጃ ከገለልተኛ ወገን በሳቸው ጉዳይ ላይ የፃፍሽው አንቺ ነሽ። ይሄ ጽሑፍ ይወትሽ ላይ ብዙ ተፅእኖ እንደፈጠረ እገምታለሁ። ከዛ ባሻገር ግን የደህንነት መዋቅሩ በዚህ ጉዳይ ላይ ሊያናግርሽ አልሞከረም ወይ? ምርመራ አልተደረገብሽም?

በፍፁም! ከዚያ በኋላ ማንም የትኛውም አካል ያናገረኝም የጠየቀኝም የለም። አንተም የምታውቀው ይመስለኛል ሶሻል ሚዲያ (ማህበራዊ ሚዲያ) ላይ ታፍና ተወስዳለች፤ ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ ባልታወቁ ሰዎች ተገድላ ተጥላለች አይነት ዜናዎች ይሰሙ ነበር። ግን እንደሚባለው ምንም የደረሰብኝም ሆነ የጠየቀኝም፤ አፍኖ የወሰደኝ የለም።

 

ይህንን ቃለ ምልልስ እንድትሰጪና ምንም አልሆንኩም እንድትይ ማንም ግፊት አላደረገብሽም፤ ከመንግሥት?

ከዛ በፊት ከቀናቶችም በኋላ ምንም የደረሰብኝ ግፊት የለም። ማንም ጠርቶኝም፣ አናግሮኝምና ጠይቆኝም አያውቅም በዚህ ጉዳይ….

 

በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሊያገኙሽና ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሞከሩ ሰዎች የሉም በቀጥታ የፀጥታ አካላት ባይሆኑም….

የሉም! አንዳንድ የማቃቸው ሰዎች ፌስቡክ ‘አብዴት’ ያደረግኩትን ነገር ያዩ “እርግጠኛ ነሽ እሱን ነው ያናገርሽው? እሱ ስለመሆኑ ምን ያህል እርግጠኛ ነሽ” አይነት ጥያቄዎች ይጠይቁኛል። እነዚህ የማቃቸው ሰዎች ናቸው። ከዛ ውጭ የማላቃቸው ሰዎች በተዘዋዋሪ ጠይቀውኝ አያውቁም።

 

ለምን ዝምታን መረጥሽ? ባንች ጉዳይ ላይ ብዙ ሲባል ነበር። አንደኛ ከፌስቡክ ገፅሽ ላይ የፃፍሽውን አላወረድሽም፤ ሁለተኛ ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው ዝምታሽን የሰበርሽው። ለምንድን ነው?

ኢንተርኔቱ ቅዳሜ ቀን ተቋረጠ። ስለዚህ ቅዳሜ፣ እሑድ፣ ሰኞ፣ ማክሰኞ እስከ ረቡዕ ድረስ ኢንተርኔት አልነበረም። አለሁ ብዬ ለመፃፍም የኢንተርኔት አገልግሎት [access] አልነበረኝም። ያንንም የሰማሁት ከአገር ውጪ ያሉ ሰዎች ሲደውሉልኝ ነበር። እንደዚህ ተብሎ ተፅፏል ብለው ነገሩኝ። አለሁ ለማለትም ኢንተርኔት ስላልነበር መመለስ አልቻልኩም።

ከዛ በኋላ ግን በቢሮ ስልክ ደውለው ያገኙኝ የሚዲያ ተቋማት [Media House] አሉ። ለምሳሌ አቤ ቶኪቻው ሳቅና ቁምነገር [ካልተሳሳትኩ] እሱ ደውሎ አናግሮኛል ‘አለሁ’ ብየዋለሁ። ዶይቼ ቬለ እንደዛው ደውለው አግኝተውኝ እንዳልታሰርኩ አረጋግጨላቸዋለሁ። ግን ኢንተርኔት እንዳገኘሁ እንዳለሁ ‘ስታተሴን አብዴት’ አድርጌያለሁ። አለመታሰሬን atleast የሚያሳውቅ ነገር።

ከማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጽሑፉን ያላነሳሁት That’s …That’s fact ነው። Fact means እውነት ነው ሳይሆን፤ ቃለምልልስ አድርጌ ያገኘሁት ነገር ነው። ለእርሱ ደግሞ ማስረጃ አለኝ። የቀዳሁት [Record] ያደረኩት መረጃ አለኝ።

 

የተቀዳው ድምጽ እንዲወጣ ፍቃደኛ ነሽ? ለምሳሌ ከፈቀድሽ እኛም ልናወጣው እንችላለን ወይም በራሳችሁ ሚዲያ። እንደሱ ዓይነት ፍላጎት አለሽ?

አሁን ባይወጣ እመርጣለሁ። ምክንያቱም ያለቀለት፤ የተዘጋ ነገር አይደለም። ምርመራ ላይ ያለ ነገር ነው። ስለዚህ በዚያ መካከል ማውጣቱ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም።

 

ከዚህ ክስተት በኋላ ሕይወት ላይ ወይም ቤተሰቡ የፈጠረው መረበሽ አለ?

ምንም ነገር። ማንም ጠይቆኝ ስለማያውቅ ምንም ነገር የለም። አንዳንድ የሚነግሩኝ ሰዎች አሉ። አደጋ [Risk] አለው እኮ… ለምን እንደዚህ አደረግሽ? እንደዚህ ቢሆን… እንደዚህ ቢከሰት … ዓይነት ነገሮች አሉ። ግን ከቤተሰብ በኩል የመጀመሪያ ሰሞን ይጨነቁ ነበር። ሰው እንደዛ ሲል ታስራለች … እንዲያውም ማክሰኞ ዕለት የነበረው ሞታ ተገኝታለች ሲባል ነበር። ግን ወዲያው ነው የቆመው እሱ ወሬ። ረቡዕ ዕለት ተመልሶ ታስራለች መባል ተጀመረ። የዚያን ጊዜ ይደነግጡ ነበር። የእውነትም ይመስላቸዋል። ደውለው እስከሚያጣሩና ድምፄን እስከሚሰሙ ድረስ የእውነት ይመስላቸው ነበር።

ምክንያቱም አሁን ነው የታሰረችው…ከሰዓታት በፊት ነው ዓይነት ነገር ይባላል እና ደጋግመው ይጠይቁኝ [Check] ያደርጉኝ ነበር ሥራ ቦታ ላይ ስለነበርኩኝ።

ከዚያ በኋላ ግን ከረቡዕ ዕለት በኋላ ነገሮች ሁሉ የተረጋጉ መሰለኝ። አልፎ አልፎ ነው አንዳንድ ሰዎች ‘ታስራለች’ የሚሉት እንጂ ግልፅ የሆነ መሰለኝ እንዳልታሰርኩኝ።

 

አንች ግን የሆነውን ሁሉ ተመልሰሽ ስታይው ምነው ያን ቀን ባልደወልኩ የሚል ስሜት ይፈጠርብሻል?

በፍፁም አይፈጠረብኝም፤ በፍፁም አልተፈጠረብኝም፤ አይፈጠርብኝም። ሥራ ላይ ነበርኩ ሥራዬን እየሰራሁ በነበረበት ሰዓት ነው አጋጣሚ የደወልኩት እና ምንም የተለየ ነገር እንዳደረኩም አይሰማኝም።

 

የመንግሥት የፀጥታ አካላት እስካሁን አንች ጋ አለመምጣታቸው ወይም ቃል ለመቀበልም አለመሞከራቸው ግን ይገርምሻል?

እ… No! አይ አይገርመኝም።

 

ለምን?

ጋዜጠኛ ነኝ። ጋዜጠኛ ነገሮችን ይጠይቃል፤ ያጣራል። ሶ እኔም ያደረኩት ያንን ነው። በዛ ሰዓት የደወልኩላቸው መረጃ ለመጠየቅ ነው። መረጃ ወስጃለሁ። መረጃ ያገኘሁትን ነገር አውጥቻለሁ ወይ ፅፌያለሁኝ። ያንን ማድረጌ ያስጠይቀኛል ብዬ አላስብም። ስጋትም አላደረብኝም።

 

ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ከእርሳቸው ጋር በተያያዘ የሚፃፉ ነገሮችን ትከታተያለሽ?

አልፎ አልፎ

ይህንን ነገር ለማጥራት እጅሽ ላይ ያለውን ድምፅ ለመልቀቅ ጊዜው አይደለም ብለሽ እንድታስቢ ያደረገሽ ምንድን ነው?

እ… አንደኛ ይህን ነገር ማጥራት የእኔ ኃላፊነት ነው ብዬ አላስብም። ይሄንን ኃላፊነት ያለው ክፍል አለ። በዛ ላይ አሁንም ደግሜ የምልህ ያለቀ ነገር አይመስለኝም። ምርመራ ላይ ያለ ነገር ነውና ምርመራ ላይ ያለ ነገር ላይ ጣልቃ ገብቶ እንደዚህ ነው እንደዛ ነው ማለት ትክክል አይመስለኝም፤ የሕግም ተጠያቂነት ያለበት ይመስለኛል።

 

/ “ብ/ጄኔራል አሳምነውን ቀድቻቸዋለሁ”: ቢቢሲ አማርኛ  

=====000=====


 

ተዛማጅ፡

እንደ ዋዛ የማይታለፈው የዶ/ር አምባቸው እና የጠ/ር አብይ ሙግት በዘመድኩን በቀለ ከነማስረጃው

 

 

 

የጅግጅጋው ግጭትና የመረጃ አፈናው አይደገም!

8 Aug

በከፍያለው ገብረመድኅን  The Ethiopia Observatory (TEO)

ዕድሜ ለአብዲ ዒሌ —ጅግጅጋ ዕልቂቱ ለቀናት ተጧጡፏል። እስካሁን 96 ሰዎች መገደላቸው ይነገራል። ግድያው ግብ ያለቢሆንም፣ የሚላስ የሚቀመስ በሌለበት ሁኔታ ሕይወት እየቀጠለች ነው ለማለት ያዳግታል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በተከሰተው ግጭት ለተጎዱ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ 24 የሕክምና ባለሙያዎች ያሉበት ቡድን ወደ ሥፍራው መላኩን ተገንዝበናል

አብዲ ዒሌም አንዴ ታሥሯል፣ አዲስ አበባ ስብሰባ ላይ ነው እንባላለን፤ በአጭር አባባል ይህ ሃገር አጥፊ ወንበዴ የትና በምን ሁኔታ እንዳለ እንደዜጎች አናውቅም!

አልፎ አልፎ መቀለጃው ቢያደርገንም፣ ዘንድሮ ሶሻል ሚዲያ ባይኖር ኖሮ፣ ባልጠበቅነው መንገድ ድቅድቅ ጭለማ ውስጥ እንወድቅ ነበር። አሁንም ጥያቄዬ የዐቢይ መንግሥት ለምን ይሆን መረጃ የሚያፍነው?  ለላው ቀርቶ ለምሣሌም ያህል ሚዲያ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች የሚሉትን እንኳ አዳምጡ! የኢሣቱ ፋሲል የኔዓለም በተለመደው ጨዋ አቀራረቡ እንዲህ ይላል፦ 

“በግሌ አብይ በድካም ብዛት ታሞ ካልሆነ ወይም ቀደም ብሎ ለእረፍት ወጥቶ ካልሆነ ፣ እንዲህ አይነት አንገብጋቢ ነገር ሲያጋጥም ዝም ብሎ ይቀመጣል ብዬ አላስብም፤ አብይን የምንወደው ግልጽነትን ስላሳየን ነው፤ ዛሬም ያንን ግልጽነት እንፈልጋለን። ትክክለኛ መፍትሄ ማመንጨት የምንችለው ትክክለኛ መረጃ ሲኖረን ነውና አብይ ከቻለ ራሱ ካልቻለ ደግሞ ወኪሉ ቀርቦ ያስረዳን።”

ሕዝብ ለችግሮቹና ለጥያቄዎቹ መልስ ባለማግኘቱ፣ ተቃውሞውን የባሰ የሚያቀጣጥልበት ዘመን ውስጥ ነው ያለነው። ከጥር እስከ ሚያዝያ 2018 ብቻ በሶማሌ ክልል በየትኛውም ክልል ያልታየ መጠን ተቃውሞ (57%) ተካሂዶ በዚያ ነዋሪ የሆነው ሕዝብ ለአሁኑ ክፉ ሁኔታ ተዳርጓል— አንድ ጥናት እንደሚያሳየው። ደጋግሞ የሚቃወምና መሥዋዕትነት የሚከፍል ሕዝብ ማሸነፉ አይቀር

የሶማልያ ክልል ሕዝብም ብልሹውን አብዲን ለማባረር ለመቁረጡ ለዚህ ማረጋገጫ ነው። አብዲ ዒሌም ሆናችሁ ሕወሃትም “ከወደቁ ወዲህ መንፈራገጥ ለመላላጥ” የሚለው ትምህርት ሆኗችሁ ሃገሪቱን ማመሳችሁን አቁሙ!

ከጥር-ሚያዝያ 2018 በተካሄዱ ተቃውሞዎች ብዛት የሶማሌ ክልል ከፍተኛውን ድርሻ ይዛለች

እምብዛም ባይገርምም፣ የመጨረሻ ምሽቱ መድረሱን በሚገባ ተገንዝቦ፣ ለራሱ መሰንበት ሲል አብዲ ዒሌ ሃገር እስከማፍረስ ሃሣብ እንደነበረው ተነግሯል። በአብዲ ዒሌ የጥፋት መሣሪያዎች ቤተ ክህነቶች ተቃጥለው ካሃናት መገደላቸውን ሰምተናል።

ይህም አረመኔያዊነት በነዋሪውና በተለይም የአካባቢው ተወላጅ ባልሆኑት ዜጎች ላይ ነፍሰ ገዳዩ አብዲ ያሴረው ወረራና ግድያው ብዙ ጥፋቶችን አስከትሏል። የክልሉን ተወላጆችም ከአደጋው ነጻ አላዳረጋቸውም!

‘ቄሱም ዳዊቱም ዝም!’

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ! ይህ ሰው ለፍርድ ቀርቦ ለጥፋቱ ተገቢውን ቅጣት ካልተቀበለ፡በንጹሃን ላይ የተፈጸመው ግፍና የፈሰሰው ደማቸው በሃገራችን ላይ መጮሁን አይቀርም! ይቀጥላል። ጎን ለጎንም ለዘለቄታው የማረጋጋት ሥራ ሊሠራ ይገባል! በዚያ አካባቢ የሚቀጥል ችግር ሃገር ጎጂ ነው!

በኢትዮጵያ ቴሊቪዥን ጣቢያ ፊት ለፊት በኃዘን ተመተው ግራ የተጋቡ ወገኖች — ሶማሌዎች፣ አማሮች፣ ኦሮሞዎች፣ ወዘተ —ፍርሃታቸውና ኃዘናቸው መንግሥት ጆሮ እንዲደርስላቸው፣ አንዳንዶቹም በቁጣና እምባቸው እየፈሰሰ ጥሪ ሲያደርጉ ተመለከትኩ። በኃዘናቸውም ውስጥ ኃዘን ብቻ ሣይሆን፡ ኢትዮጵያዊነታቸውም አንድ አድርጓቸዋል!

እነዚህስ ለምን አይደመጡም! የዐቢይ መንግሥት ደጋፊ ነኝ። ነገር ግን ‘ቄሱም ዳዊቱም ዝም’ ሆኖብኝል!

ሁኔታው ልብ የሚሠብር፣ በጥጋበኞች ላይ ጥርስ የሚያስነክስ እንደሆነ አምባብያን ራሳችሁን በእነርሱ መጫሚያዎች ውስጥ አድርጋችሁ መገመት ትችላላችሁ።

በሁኔታው ዙርያ፣ እንደሌሎቻችን ሁሉ ከውጭ የተመለሱ ድርጅቶች አክቲቪስቶችም ስለተነኩ ከሠልፈኞች ውስጥ መመልከትም አይሳንም!

ምናልባትም የሁኔታው አስከፊነት በታሪክ ከታዩት አንዳንድ አስከፊ ጦርነቶች ሁኔታዎች ተመሳሳይ ሆኖ ነው የታየኝ— መሣሪያ የታጠቁ ወንበዴዎችና ደራሽ የሌለው ሕዝብ በተጠቂነት የቆመበት፣ የተተኮሰበት፣ የተመታበት፣የተዘረፈበት… !

ኢትዮጵያውያን በሊቢያ የታረዱትን ወንድሞቻቸውን በማሰብ ባደረጉት ሠልፍ ላይ የአጋዚ ራምቦ የሕወሃትን ዘላለማዊነት ለማረጋገጥ በዜጎች ላይ ጥቃት ሲፈጽም(Foto Negere Ethiopia).

ውጭ ሃገር ሆኜ ከወገኖቼ ጋር እንኳ በማላለቅስበት ሁኔታ፣ ሰላሣ ኢትዮጵያውያን በምድረ ሊቢያ በአረመኔዎች የታረዱበትን ሁኔታ አስታወሰኝ! 

ተያያዥ ነገሮችም አብረው ስለሚመጡ፡ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማምሻውን ከየአካባቢዎቻቸው ተሰባስበው ልደታ፡ ጨርቆስና በማግሥቱም አብዮት አደባባይ ተሰባስበው ማልቀስ ጀመሩ።

የተነቃነቀው ዙፋን እንዳይደፋ ሕወሃቶች ወገኖቻችንን በዱላ፡ በሠደፍ ሲሏቸው በቴክዋንዶ ሲያዳፏዋቸው — መጽናናት የሚገባቸው ዜጎች ሲረገጡና ወደ እሥር ሲጋዙ በቴለቪዥን አየሁ! 

ለኃዘን የወጣች ነፍሰ ጡርም፡ በጸጥታ ኃይሎች ተደብድባ እንዳስወረዳት ሰማሁ! ለምን ያቺ የኛ ኢትዮጵያ ትሆናለች?

እግዚአብሔር ይመስገንና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ይህ አደገምም ብዬ ለመናገር የምደፍርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብዩ ተስፋ አደርጋለሁ!

እስከ ዛሬ የሶማሌ ክልልን ችግር እገነዘበዋለሁ የሚል ግምት ነበረኝ!  አሁን ግን ልክ እንዳልነበርኩ ተንገንዝቤያለሁ! ይህ በአንድ በኩል የሲስተም ችግራችን ጥልቅ መሆኑን፣ በሌላው በኩል ደግሞ ኢትዮጵያውያን ችግር ተሸካሚዎች ስለመሆናችን ይመሰክራል። ነገር ግን ይህ ችሎታ አለመሆኑን ልብ ሊሉት ይገባል!

ራሳችንን ብዙ ያከበርንና የወደደን ይምስለን እንጂ፡ ለሌላው ስብዓዊ ፍጡር (ለራሳችን ወገኖች ጭምር) አሳቢነትና ተቆርቋሪነት ስለነፈገን፡ ከሰብዓዊነት ገንጥሎናል! ይህ በቅርብ ሊታይና ሊታሰብበት ይገባል!

በአሁኑ ወቅት ጅግጅጋም ባፈሰሰችው ደም፣ በዘረፋዋና ጭካኔዋ ይህንኑ ነው እንደገና ያስታወሰችን! እንደገና ያሳያችን ይህንኑ ነው! ሃገራችንን ለመገነጣጠል፡ ከፍተኛ ጥጋብ ያሰከረውንና የበላበትን ወጭት ሰባሪነት አባዜ የተጠናወተው ልበ ድፍን ግለሰብ አንቀጽ 39ን ተግባራዊ ለማድረግ የተንቀሳቀስውን ቦዞ ከፓርላማ መከላከያ ሠራዊታችን ጎትቶ እንዳወጣው ይነገራል። መቼም የዐቢይ መንግሥት ስላልነገረን፣ ስለትክክኝነቱ መፈረም አልችልም!

ለመሆኑ ለምን ይሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር በዚህ አሳሳቢ ጊዜ ሕዝቡን በመረጃ ጨለማ የተወው?አልጠበኩም ነበር!

የኢትዮጵያ የመከላከያ ጦር

ይመስለኛል፣ በአካባቢው ለሠፈረው የመከላከያ ጦር የውሳኔ ሰዓት ሆነ፤ ዘራፊው የአብዲ ወንበዴዎች ጥርቅም የሆነው “ልዩ ፖሊሶች” ቡድንና  ሰውየው ባዘጋጃቸው “ሄጎ” (የወጣቶች ጉም)  በተባሉ ወጣቶች ተደግፎ ግድያና ዘረፋዎች መፈጸማቸው፡ የእምነት ቤቶችን ማቃጠላቸው ለመከላከያ ሠራዊቱ —በግዴታው መሠረት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ – ያላንዳች ጥርጥር አስገዳጅ ሁኔታ ተፈጥሯል! ልዩ ፖሊስ  ተ.መ.ድ. በ Somalia Eritrea Monitoring Group –SEMG– ሪፖርቶቹ ሶማሊያ ውስጥ በተደጋጋሚ ወንጀለኛ ያደረገው ቡድን ነው። 

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ ሐምሌ 28 ፍንጭ ሠጠ።  ”በክልሉ የሕዝቦቻችን ሰላም እና ደኅንነት አደጋ ውስጥ እየገባ ያለበት ሁኔታ በመፈጠሩ የመከላከያ ኃይላችን ሁከትና ብጥብጡን በዝምታ የማይመለከት መሆኑንና የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስድ መሆኑን” ነው በጥብቅ ያስጠነቀቀው። 

መከላከያ በመግለጫው እንዳለው በግዳጅ ተሠማርቷል ወይንስ አልተሠማራም የሚለው በተለያየ መልኩ ተሠምቷል። ከአካባቢው ጋር የተደረጉ ያዳመጥኳቸው የስልክ ቃለ መጠይቆች በተደጋጋሚ እንዳሰሙት። ሰዎች እየተገደሉም፣ ንብረቶችም እየወደሙ፣ መከላከያ እንዳለው አልገባም — ምክንያቱ ግን አልተነገረንም!

መከላከያ በሳይኮሎጂ ጦርነት ብቻ መወሰኑ ይሆን? ወይንስ የፌደራል መከላከያ መግባት መንግሥት ግልበጣ ነው በማለት ሕወሃት በባለጥቅሞች ስም ወይንም የሁሉን አውቃለሁ “የሕግ ትንተና”ያካሄደው ዘመቻ  አስደንግጦት በዚያው ቀረ?  ወይንስ በቂ መሣሪያና ኃይል አልነበረውም? ላነሳኋቸው ጥያቄዎች መልሶቹን በእርግጠኝነት አላውቅም!

መከላከያም ጅጅጋ ገብቶ የማረጋጋት ሥራ እንዲጀምር የታዘዘው ሐምሌ 30 ነበር እንጂ መጅመሪያ እንዳስጠነቀቀው — ግድያው፣ ቤተ እምነት ማቃጠሉና ዘረፋው በተካሄደበት ወቅት አልነበረም! ይህም ብዙ ሊያነጋግረንና ሊያሳስበን ይገባል!

በጋምቤላ በኩል ተደፍረን ልጆቻችን ታፍነው ሲወሰዱ፣ በአካባቢው የነበረው ኃይል ከድንፋታ ውጭ ያደረገው ነገር አልነበረም! እስከዛሬም በዚያ ምክንያት ጋምቤላዊ ኢትዮጵያውያን ልጆች ሱዳን ‘ተወርሰው’ የቀሩበትን ሁኔታ መዘንጋት የለብንም!

‘የወርቁ ዘር’ ልጆች ቢሆኑ ኖሮ ምንድነበር የሚደረገው ብለን ልንጠይቅ ይገባናል! አሊያ ኢትዮጵያዊነት ሲራከስ አጨብጫቢዎች ነው የምንሆነው!

ትንሿ ጂቡቲ ሰሞኑን ምንደነው ያደረገችው? አምስት ዜጎች ተገደሉባት ሶማልያ ክልል —በአውቶቡሶች፣ ባቡርና አውሮፕላኖቿን ዜጎቿን አስወጣች!

የነፍስ መለዋወጭ የምትሠራዋ የምትመስል ሃገራችን ግን ዛሬም ዜጎቿ በባለ ሥልጣኖቻችን ጥጋብ ወይንም ቸልተኝነት እንደቅጠል ይረግፋሉ!

የጣልቃ መግባት ሕጋዊነት

የሕጋዊንት ጥያቄን በተመለከተ፡ እኔ እስከሚገባኝ ኢትዮጵያ በእንዲህ ዐይነት ሁኔታ ይህን ያላንዳች ውጣ ውረድ በተግባር ማዋል የሚያስችሉ ሕጎችና አዋጆች አሏት:-

ሀ.  ‘እንዳተረጓጎሙ’ ሕገ መንግሥቱ ራሱ አንቀጽ 51፡ (17)፤ አንቀጽ 77 (10)፤ አንቀጽ 93 ተጠቃሽ ናቸው! በተጨማሪም፡ አንቀጽ 87 መከላከያ ያለበትን ኃላፊነቶች ይዘረዝራል። ለምሣሌም ያህል አንቀጽ 87(2)፣ (3) እና (4) ግዴታውንና ኃላፊነቱን በሚገባ ያስቀምጣሉ — በተለይም አንቀጽ 87 (3)፡ “የመከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ በተጨማሪ በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናል።”

ለ. ወታደር ወገንና ሃገር ያለው ሰብዓዊ ፍጡር በመሆኑ፡ ወገኖቹ ሲጨፈጨፉ — በተለይም አሁን ከራሱ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጥቅሞች ውጭ ባለማሰብ የሚታወቀው ሕወሃት አንገቱን በደፋበት ሁኔታ—የሃገሪቱ መከላከያ በዝምታ የሚመለከትበት ሁኔታ እንደማይኖር ጂነራል ጸዐረ መኮንንም ካሳወቁን ሣምንታት ተቆጥረዋል።

አሁን በዚህ ሕዝብ በሚጨፈጭፍበት የጅግጅጋ ሁነታ እንኳ —  እንዳይወድቅ — ሕወሃት ለጄኔራል ሠዓረ ማባበያና ማስፈራሪያ መልዕክት ከመላክ ባሻገር፡  አዲሱን የኢትዮጵያ አመራር ስም እስከማጥፋት ተንፈራግጣለች።

ነሐሴ 5/18 ዳንኤል ብርሃኔ ለጄነራል ጸዐረ መኮንን “የመጨረሻ ዕድል” የትዊተር ማስጠንቀቂያውን በተለይም “You won’t get a second chance!”  ሳነብ ብዙም አልተገረምኩም!

የምጠብቀው፡ መከላከያ ለምን በአስቸኳይ ሕዝቡንና ንብረት ለማትረፍ እንዳልተንቀሳቀሰ የሚሠጠው አርኪ መልስ ይኖረዋል ብዬ ተስፋ በማድረግ ነው!

ለምን የሚለው ጥያቄ አስፈላጊ ነው። ሕወሃቶች በዘረፋና በግድያ መክበርን የማይጠየፉ ግለሰቦች፣ ስብስብና ቡድን ናቸው። ከመሃይሙ አብዲ ዒሌም ጋር ያወዳጃቸው ይኽው ነበር። አብዛኞቹ ሕወሃቶች ጥቅም ላይ ያተኩሩ እንጂ ሃገር፡ስለወገንና እምነት የላቸውም ብዬ እኔ ራሴ ስንትና ስንት ጊዜ የጻፍኩትን ዕውነታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አረጋግጦልኛል። ሁልጊዜም እንዲህ ዐይነቱን ነገር ሳነሳ፣ ለኔ ሕወሃትና የትግራይ ሕዝብ የሰማይና ምድር ያህል ልዩ ናቸው!

አሁን አብዲ ዒሌም ክልትም ብሎ በሕዝብ ኃይል ተገፍትሮ መደበቂያ በሚያፈላልግበት በአሁኑ ወቅት፡ ትግራይ ከለላ ትሠጥሃለች አይደለም ያሉት — ድሮስ ቢሆን የማይረባ መሆኑን መች አጣነው ነው የዘፈኑለት!

‘አብረን እንፈንጥዝ፣ እብረን እንግደል፣ አብረን እንቀበር! ከጄኔራሉ ፌስቡክ የተቀዳ ምስል (https://www.facebook.com/WeiAlfaGabree)

የሶማሌ ክልል ኢትዮጵያዊ  እየተራበና እየተጠማ፡ ድንቁርና ውስጥም ሆኖ፡ የሕወሃት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እንጄነራል (በይፋዊ ስሙ) ጄኔራል ገብሬ አድሃና ዎልደዝጉ (ተዘርዝረው የማያልቁ የሕወሃት የጦር መኮንኖችና ካድሬዎች ሁሉ — ዳንኤል ብርሃኔ ጭምር) ብዙ የጋጡባት ክልል ናት!

ቀደም ሲል ያወዳጃቸውም የጫትና ሌሎች የኮንትሮባንድ ንግዶች ናቸው። ከፍተኛ የሕውሃትን ሲቪልና ወታደራዊ ባለሥልጣኖች ድሮም ያገናኛቸው የቡድንና የግል ጥቅሞች በመሆናቸው፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በብዙ መሥዋዕትነት የተገኘውን የነጻነት ጅምርና የነገውን ተስፋ መጠበቅ ይኖርበታል!

ኢትዮጵያ ከዓመታዊ ገቢዋ በዓመት እስክ 2% በግጭቶች ምክንያት እንደምታጣ አንድ የእንግሊዝ መንግሥት (DFID) ጥናት በ2017 ዘግቧል።ይህም ወደሚገታበት ሃገሪቷ ፊቷን ማዞር ይኖርባታል! ለወንጀሎች ትክክለኛ ሕግንና ትክክለኛ ቅጣትን አፋተን የምናካሂደው ፖለቲካ ማጠፊያው እያጠረ ችግር ላይ እንዳንወድቅ ጥንቃቄ ያስፈልጋል!

ሕወሃትንና ጀሌዎቹን አባሮ የሶማልያ ክልል ሕዝብ ሰላም ያገኛል ወይ የሚለው ጥያቄ መልስ የሚያገኘው በራሷ በኢትዮጵያ ነው! ያንን ማድረግ ከተቻለ በሶማልያ ክልል በሚኖረው ሰላም ብቻ — ሕዝቡ ታታሪ በመሆኑ— በኢትዮጵያ ዕድገትና ልማት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል መሆኑን —በተለይም የድንበር ዙሪያ ንግድና በተፈጥሮ ሃብት ልማት— ከላይ የተጠቀሰው ጥናት ያመላክታል።

በመጨረሻም፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ  በጅግጅጋ  ሕዝቡን ለማረጋጋት ሁኔታው በቁጥጥራቸው ሥር መሆኑን በመጀመሪያዎቹ ሰዓታት አለመናገራቸው እጅግ አስፈሪ የአሠራር ዘዴ ነው።

“በተግባር አሳያለሁ” ማለት ከሆነም እሰይ! ነገር ግን “በቂ አልነበረም! አይደለምም” እላለሁ! ግጭቱን በተመለከተ መግለጫም በሚገባ እየተሠራጨ አልነበረም!

በወቅቱ ምን እየሆነና ምን እየታሰበ እንደሆነ ለሕዝቡ ይፋ ሊደረግ በተገባ ነበር። ይህ ማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተፈጸመው የወንጀል ድርጊት የሰው ሕይዎት በመጥፋቱ ማዘናቸውን ሐምሌ 30 መግለጻቸውን አላየሁም ማለት አይደለም

አሁን ካለፈው ጭለማው የሕወሃት የዘረፋ ዘመን ጋር የማወዳደር ሳይሆን፡ አሁን ኢትዮጵያ የሁሉም ዜጎች ናትና በብርሃን በትብብር መሥራቱ ይበጀናል።

%d bloggers like this: