Tag Archives: Keria Ibrahim

“አምባገነናዊ መንግሥት ሲመሠረት ተባባሪ ላለመሆን ኃላፊነቴን ለቅቄያለሁ”—  ኬሪያ ኢብራሂም

9 Jun

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒም ሕገ መንግሥት ከሚፈቅደው ውጪ አምባገነናዊ መንግሥት ሲመሰረት ተባባሪ ላለመሆን በገዛ ፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን አስታወቁ።

የአፈጉባኤዋን ሥልጣን መልቀቅ በተመለከተ ወ/ሮ ኬሪያ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት የአገሪቱን “ሕገ መንግሥት በየቀኑ ከሚጥስና አምባገነንነትን ከሚያራምድ ቡድን ጋር ለመስራት ፈቃደኛ ስላልሆንኩ ነው” ብለዋል። አፈጉባኤዋ ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት በሥልጣን ላይ ያለው ወገን “ሕገ መንግሥቱን በግላጭ ተጥሷል አምባገነናዊ መንግሥት ወደ መመስረት ገብቷል” ሲሉ ከሰዋል።

ለዚህም እንደማሳያ ያስቀመጡት ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ያለምርጫ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲል በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያለ ክፍተትን በመፈለግ “አንዱን አንቀጽ ከሌላው ጋር በማጋጨት ክፍተት እንዲገኝና አማራጭ እንዲፈለግ” ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

በሥልጣን ላይ ያለው አካል ካለሕዝብ ውሳኔ ባለበት ለመቆት መወሰኑንና ይህንንም ሕጋዊ ለማድረግ ክፍተት በመፈለግ ሕገ መንግሥታዊ ከሆነው መንገድ ውጪ “ባልተለመደ አካሄድ ሕገ መንግሥቱ እንዲተረጎም ግፊት እየተደረገ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህም አስቀድሞ የተወሰነ መሆኑን ጠቅሰው “ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነው” ብለዋል። ጨምረውም ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔውን በማይቀበሉት ላይ “ማስፈራሪያና ዛቻ” እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ሳቢያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሲሆኑ “ሕገ መንግሥቱን የማክበር የማስከበር አደራ ስለተቀበልኩ፤ ሕገ መንግሥቱ ተጥሶ አምባገነናዊ መንግሥት ሲመሰረት ተባባሪ ላለመሆን” ሲሉ በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን እንደለቀቁ ተናግረዋል።

ጨምረውም “በሕገ መንግሥት ትርጉም ሽፋን የአምባገነናዊ ሥርዓት ሕግ የሚጥስ ድርጊትን ላለመተባበር ወስኛለሁ” ብለዋል ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም።

 

ከሁለት ዓመት በላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ሆነው ያገለገሉት ወ/ሮ ኬሪያ ስለውሳኔያቸው በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት ይህ እርምጃ የአገሪቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የስልጣን ባለቤትነትን የሚጥስ ነው ብለዋል።

ቢቢሲ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ስለ አፈጉባኤዋ ሥራ መልቀቅ ለማጣራት ባደረገው ጥረት ምክር ቤቱ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገልጿል።

 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ አቶ ገብሩ ገብረ ሥላሴ ለቢቢሲ የአፈ ጉባኤዋን ከሥራ መልቀቅ በተመለከተ የቀረበ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

ቢሆንም ግን አፈ ጉባኤዋ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን በሚመለከት የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎችን መመልከታቸውን ገልጸው፤ በጽሕፈት ቤቱ በኩል ግን የቀረበ ይህንን የሚያረጋግጥ ነገር የለም ብለዋል።

የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ የሆነው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ወይዘሮ ኬሪያ በአፈ ጉባኤነት የሚመሩት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አነጋጋሪ በሆነው የሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳይ ላይ በቅርቡ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

/BBC News አማርኛ

 

 

የፌዴሬሽን ም/ቤቷ ኬሪያ ኢብራሂም ስለወልቃይት የሠጡት መግለጫ “ኢትዮጵያዋ ፍልሥጤም አድርጓታል!”

26 Oct

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)/

በዘሐበሻ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም በቴሌቭዥን ወጥታ የሰጠችው መግለጫ ሕወሓት በብአዴን/አዴፓ ላይ ያወጣው መግለጫ ነው በሚል ተተቸ።

“ስለ ወልቃይት የሚቆረቆረው አማራ ክልል ነው” በሚል ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም የሰጠችውን መግለጫ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ሲተቸው “ኬሪያ ኢብራሂም ስለ ወልቃይት መግለጫ ስትሰጥ “የሚቆረቆረው አማራ ክልል ነው” አለች። ይህ በፌደሬሽን ምክር ቤት በኩል ብአዴን ላይ የተሰጠ መግለጫ ነው። አያገባውም ለማለት ነው። የትህነግ/ህወሓት አረመኔነት እዚህ ድረስ ነው። መቆርቆርም አይቻልም ማለት ነው።” ብሎታል።

ጌታቸው አክሎም “ወልቃይት ላይ አማራ በመሆናቸው ብቻ ዜጎች በአማርኛ እንዳይማሩ ተከልክለዋል። በአማርኛ እንዳይዘፍኑ ተከልክለዋል። የፋሲል ከነማ ማሊያን መልበስ ወንጀል ነው።   አማራ በመሆናቸው እስርና ደብደባ ከዚህ ሲከፋ ሀብት ንብረታቸውን ቀምቶ እትብታቸው ከተቀበረበት ምድር ማባረር እንዲሁም መግደል የተለመደ ሆኗል። ይህ ለትህነግ ስራ ነው። ለተጎጅዎች መቆርቆርን ደግሞ ሕገ ወጥነት ያደርገዋል።

“የወልቃይትን ጉዳይ ተገፊዎቹን በማነጋገር የተረዳው ኦባንግ ሜቶ “የኢትዮጵያዋ ፍልስጤም” ሆናለች ሲል ገልፆታል። ወልቃይት ላይ የሚፈፀመው በደልና ጭካኔ ልክ አጥቷል። ይህን የሚፈፅመው ትህነግ/ህወሓት ነው። ይህ ገዳይ ድርጅት ለገደላቸው ሊቆረቆር አይችልም። ላሳሰዳቸውና ሀብት ንብረታቸውን ብቻ ሳይሆን ማንነታቸውን ለነጠቃቸው ሊቆረቆር አይችልም። ትህነግ/ህወሓት ቢችል ሊያደርግ የሚፈልገው ማጥፋት ነው። የሚፈልገው መሬቱን እንጅ ሕዝቡን አይደለምና።” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። 

“ኬርያ ኢብራሂም የዚህ ጨካኝ ድርጅት ስራ አስፈፃሚ ናት። ግድያ ከሚያዙት መካከል አንዷ ናት። ከሚያፈናቅሉትና ወሳኞቹ መካከል አንዷ ናት። እሷም ለወልቃይት ልትቆረቆር አትችልም።” የሚለው ጋዜጠኛው “በመሰረቱ ለመቆርቆር የሚያስፈልገው ሰብአዊነት ነው። ሕግ ማወቅ ነው። ከዚህ ባሻገር ግን እየተጨፈጨፉ ያሉት “አማራ ናችሁ” ተብለው ነው።

የአማራ ክልል ለወልቃይትና ራያ ተቆርቁሯል ከተባለ መበረታታት ነው ያለበት። ምክንያቱም ሕግ አክብሯል ማለት ነው። ሰብአዊነት ተሰምቶታል ማለት ነው። በአማራነታቸው መጠቃታቸው ትክክል አይደለም የማለት ግዴታም አለበት።” ብሏል።

“አብዛኛዎቹ የወልቃይት አማራዎች ከቀያቸው ተሳደው ጎንደር ስለሚገኙ ይሆናል ኬርያ “አማራ ክልል ነው የሚቆረቆረው” ያለችው። የእነኬርያ ፍላጎት እንደ ቀደመው ወደ ትግራይ አሳልፈው እንዲሰጧቸው ነው። እንዲያሳስሯቸው ነው።

ይህ ጊዜ ሀምሌ 5/2008 ዓም ተቋጭቷል። ዛሬም የሚቻል አይደለም” ያለው ጌታቸው “የኬርያው ትህነግ/ህወሓት የወልቃይትና የራያ አማራዎች ላይ የዘር ማፅዳት ፈፅሟል። ሊቆረቆር አይችልም።

የሚቆረቆር ሌላ አካል ከተገኘ ሰብአዊ ግዴታው ነው። ኬርያ መቀሌ ላይ ከጓደኞቿ ጋር ተሰብስባ በወልቃይትና ራያ ላይ የሚደረገውን ፍጅት ትወስናለች። አዲስ አበባ መጥታ ወደ ፌደራል መንግስቱ መጥተው “ተገደልን” የሚሉትን ተጠቂዎች “ወልቃይት ትግራይ ነው” ብላ ትመልሳለች። ገዳይም ትህነግ ነው። ፈራጅም ትህነግ ነው! ከመቀሌም መግለጫ ያወጣል። ከፌደሬሽን ምክር ቤትም መግለጫ ያወጣል።” ሲል ሰሞኑን የሰጠችውን መግለጫ አጣጥሎታል።

በሌላ በኩል ስለራያና ወልቃይት ማንነት የተናገሩት የሕወሓቱ 3ኛ ሰው ጌታቸው ረዳ “ወደ ጎንደር ጠቅላይ ግዛት፣ ወደ ኢሊባቡር ጠቅላይ ግዛት ስርዓት እንመለስ ማለት በግልፅ ፌደራሊዝም ስርዓት ይፍረስ ማለት ነው። ክልሎች ኢህኣደግ ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ ነው የተመሰረቱት። ከዛ በፊት ትግራይ ክልል፣ ኣማራ ክልል ኦሮምያ ክልል የሚባል ኣልነበረም። ጠቅላይ ግዛት ነው የነበረው። ስለዚ ኣማራ የሚባል ክልል ስላልነበረ መተከል ኣማራ ነው፣ ወልቃይት ኣማራ ነው፣ ራያ ኣማራ ነው ማለት ኣትችልም ፀረ ብዙህነትና ፀረ ህገ መንግስት ነው” ብለዋል።

ተዛማጅ፡

የትግራይ ልዩ ሃይል ከወልቃይትና ራያ እንዲወጣ ተጠየቀ

የራያ ተወላጆች በአላማጣና ቆቦ መንገዶችን ዘጉ

በራያ ቆቦና ዋጃ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

በአላማጣ ከተማ የሚካሄደው ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ ዋለ

የአማራ ክልል መንግስት የራያንና ወልቃይት ጥያቄዎችን በሃይል ለመፍታት የሚደረገው ሙከራ መፍትሄ አያመጣም አለ

የአማራ ክልል ላወጣው መግለጫ ይቅርታ ይጠይቀኝ አለ ሕወሃት

 

%d bloggers like this: