Tag Archives: Medemer

በትኩረት ሊታይ የሚገባው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የመስቀል በዓል መልዕክት!

28 Sep

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

“ኢትዮጵያን ታላቅ፣ የበለጸገችና ለሁላችንም እንድትሆን ለማስቻል የያዝነው ዓላማ መሳካቱ የማይቀር እውነት ነው፡፡ ይህን ዕውነት የሚገዳደሩ ኃያላን ይኖራሉ፡፡

ለጊዜው ዝናራቸውን እስኪጨርሱ፣ ጉልበታቸውንም እስኪያፈሱ ድረስ ያሸነፉ ይመስላሉ፡፡ ድምፃቸው እንደ ነጎድጓድ፣ ጩኸታቸውም እንደ ብዙ ፏፏቴዎች የወል ጩኸት ጎልቶ ይሰማ ይሆናል፡፡ እውነታችንን የቀበሩት መስሏቸው ለጊዜው ይደሰታሉ፡፡”

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ማን ያውቃል?

የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ፡፡
ማን ያውቃል?

እንዲል ኢትዮጵያዊው ባለቅኔ – እኛና መስከረም፤ እኛና መስቀልም ዓመት ጠብቀን የምንገናኝ ተነፋፋቂ ባለ ቀጠሮ ነን፡፡

እናም ናፍቆታችንን እንወጣጣ- ፍቅራችንንም እንቀባበል ዘንድ ዓመት ጠብቀን አደባባይ እንወጣለን – ያኔ ደመራ ነው፡፡

የመስቀል በዓል በአደባባይ ከሚከበሩ የኢትዮጵያውያን በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡

ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ይህንን ታላቅ በዓል በዐደባባይ እንድናከብረው ሥርዓት ሲሠሩ ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡

ከበዓሉ ጋር የተያያዙ ሦስት ታላላቅ ሐሳቦችን ሁላችንም እንድንመራባቸው ፈልገው ሳይሆን አይቀርም፡፡

እውነትን ቀብሮ መኖር እንደማይቻል፤ ታሪክ የሚለወጠው በቆራጥነትና በአንድነት መሆኑን፣ አንድ ታላቅ ሐሣብ ኢትዮጵያውያንን እንዲጠቅም ከፈለግን ሐሣቡን ኢትዮጵያዊ ማድረግ እንዳለብን በዓሉ በደመራው ብርሃን ወገግ አድርጎ ያሳየናል፡፡

የክርስቶስን መስቀል የቀበሩት ሰዎች እውነትን ለዘለዓለም ቀብረው ማስቀረት የሚችሉ መስሏቸው ነበር፡፡

ለጊዜው መስቀሉ ከአፈር ሥር ሲቀበር ዓላማቸው የተሳካላቸው መስሏቸው ነበር፡፡

በመስቀሉ ላይ የቆሻሻ ክምር እንዲከመር ሲያደርጉ መስቀሉን ከታሪክ ገጽ ያጠፉት መስሏቸው ነበር፡፡

ይህ ግን የመሰላቸውን መስሎ መቆየት የቻለውና የዋሆችም መስቀሉ ተቀብሮ፣ ተረስቶ፣ ትቢያ ሆኖ ጠፍቷል ብለው እንዲረሱት ያስቻላቸው ዕሌኒ የምትባል ብርቱ እንስት ከተለየ ብርታት፣ ጽናትና የይቻላል መንፈስ ጋር እስክትከሠት ድረስ ብቻ ነበር፡፡

በየዘመናቱ እውነትን ለመቅበር የሞከሩ ነበሩ፡፡ በተንኮል፣ በሤራ፣ በግጭት፣ በክፍፍል፣ በጦርነት፣ በጉልበትና በኃይል እውነትን ለመቅበር ብዙዎች ሞክረዋል፡፡

እውነተኞችን በማጥፋትና በመግደል፣ በማሠርና በማስፈራራት እውነት የምትጠፋ መስሏቸው ብዙ ደክመዋል፡፡

መጻሕፍትን አቃጥለዋል፤ የዕውቀት ቦታዎችን አውድመዋል፡፡

እውነት ግን ብትቀጥንም አትበጠስም፡፡ እውነተኞችን በመግደልና በመቅበር በፍጹም እውነትን ማጥፋት አይቻልም፡፡ እውነትና ተስፋ አብረው የሚሄዱ ናቸው፡፡

እውነተኞች ተስፈኞች ናቸው፡፡

ውሸተኞች ጨለምተኞች ናቸው፡፡

ከእውነት ጋር ያልቆመ ሰው ተስፋ ሊኖረው አይችልም፡፡

ተስፋ እውነተኛ ሰው ብቻ የሚያደርገው መነጽር ነውና፡፡

ተስፋ ባለበት ሁሉ እውነት ትኖራለች — እውነት ባለችበትም እንዲሁ ተስፋ አለ፡፡

መስቀሉን የቀበሩት ሰዎች ሐሰተኞች ስለነበሩ ወደፊት የሚወጣ አልመሰላቸውም፡፡

የመስቀሉ ወዳጆች ግን እውነተኞች ስለነበሩ አንድ ቀን እንደሚገለጥ ያምኑ ነበር፡፡

ለዚህ ነው መስቀሉ የት እንደተቀበረ ከልጅ ልጅ በሚተላለፍ የቃል ትውፊት መረጃውን ለዘመናት አቆይተው ለመስቀሉ አስተርዕዮት ዘላለማዊ ገድል የፈጸሙት፡፡

ኢትዮጵያን ታላቅ፣ የበለጸገችና ለሁላችንም እንድትሆን ለማስቻል የያዝነው ዓላማ መሳካቱ የማይቀር ዕውነት ነው፡፡

ይህን ዕውነት የሚገዳደሩ ኃያላን ይኖራሉ፡፡

ለጊዜው ዝናራቸውን እስኪጨርሱ፣ ጉልበታቸውንም እስኪያፈሱ ድረስ ያሸነፉ ይመስላሉ፡፡ ድምፃቸው እንደ ነጎድጓድ፣ ጩኸታቸውም እንደ ብዙ ፏፏቴዎች የወል ጩኸት ጎልቶ ይሰማ ይሆናል፡፡ እውነታችንን የቀበሩት መስሏቸው ለጊዜው ይደሰታሉ፡፡

በዙሪያችን ያሉትም እውነታችን የተቀበረ መስሏቸው ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡

ይህ ግን የእውነትን ባሕሪይ ካለመረዳት የሚመጣ ነው፡ ፡

እውነትን መገዳደር እንጂ ማሸነፍ፣ መቃወም እንጂ ማጥፋት ፈጽሞ አይቻልም፡፡

የብዙዎች ጩኸት- የሰነፎች ተረትና የአላዋቂዎች ትምክህት ዕውነትን ሊያጠፋት እንደማይችል በጽኑ እናምናለን፡፡

ዕውነት የተቀበረችበትን አመድ እንደ ፍግ እሳት አሙቃ እንደ ገሞራ ትፈነዳለች፤ የተሸፈነችበትን አቧራና የክፋት ቁልል ቅርፊቱን እንደሚሰብር ጫጩት ፈንቅላ ትነሣለች፡፡ ነገ ከእውነተኞች ጋር ናት፡፡

እውነተኞች ዛሬ ጥቂቶች ቢመስሉም ነገ እየበዙ ይሄዳሉ፤ ሐሳውያን ዛሬ ብዙዎች ቢመስሉም ነገ እንደ ስንቅ እያነሡ ይሄዳሉ፡ ፡

====00000=====

 

እውነቱን ለመናገር፣ ሐሙስ ማምሻውን መስቀልን በበዓልነት የመጠበቅ ስሜቴ ደብዝዞ ነበር።

ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ስለበዓሉ አከባበር ፌዴራል ፖሊስ ያወጣው ረጋጭና ደፍጣጭ መገለጫው ነው።

ውስጤ በአንድ በኩል ግርግር ይኖራል፣ የፎከረ መንግሥትም እንዳለፉት ወራት ወደ ማሠር ይሂዳል። ሌላው ሥጋቴ ባንዲራ ይዘው የወጡ እልኸኛ ወጣቶች ይገደላሉ የሚል ፍርሃት ነበር!

ይህም የሃገራችንን ፖለቲካ፡ ወደ ጉልበተኝነት —አሁንም እንደምናየው፣ እንደው እንደው እየሆነ ስለሆነ ከለውጡ ወዲህ በዜጎችና ለውጡን በሚራምዱት ወገኖች መካከል የተገባው ቃል ላልቶ—የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶችን በምክንያታዊነት  መጣሱ ይባባሳል የሚል ፍራቻ ነው ውስጤን ሲገዘግዝ የነበረው!

በመሆኑም ከመተኛቴ በፊት ስሜቴንና ሃገራችን ያለችበትን ሁኔታ ያንጸባርቃል ያልኩትን ሐሙስ ማታ ባለሁበት በፊንላንድ አቆጣጠር 23 ሰዓት ላይ የሚከተለውን ትዊት አድርጌ ቀኔን ዘጋሁ።

 

የደመራ በዓል

እግዚአብሔር ይመሥገን እስካሁን ስማሁት —ከእሥር ውጭ— አንድም ዜጋ  የእምነቱን ምልክት ይዞ በመውጣቱ በፖሊስ አልተገደለም!

ለዚህም የሕዝቡን ጠንቃቃነትና ጨዋነት አደንቃለሁ!

ኢትዮጵያ እስካሁን ቁጥር ሥፍር ልጆቿን ገብራለችና በነዚያው ይብቃችሁ ይበለን! 

አርብ ወደምሽት አካባቢ ዉ ምን እያሉ ነው ብዬ ትዊተሮችን ስፈትሽ ይህንን 👇ተመለከትኩ!  

ዳዊት (አላውቀውም) ያለፈበት ሁኔታ በነበረኝ ስሜት ስቆቃውን ተካፈልኩት! መልዕክቱ ገጼ ሄዶ እንዲሠፍር አደረግሁት!

ከዚህ ባሻገር—በእኔ ዕይታ—የደመራ ምሽት ትልቁ ብርሃን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያስተላለፉት መልዕክት ይዘት ነው።

ከማን ጋር እንደሆነ ገሃድ ባያደርጉም፣ መንግሥታቸው ትልቅ ትንቅንቅ ውስጥ እንደሆነ ዛሬ ይፋ አድርገዋል።

 

አምነውበት ይሁን ወይንም ሕዝቡን ለማረጋጋት፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ይላሉ፦

“ኢትዮጵያን ታላቅ፣ የበለጸገችና ለሁላችንም እንድትሆን ለማስቻል የያዝነው ዓላማ መሳካቱ የማይቀር እውነት ነው፡፡

ይህን እውነት የሚገዳደሩ ኃያላን ይኖራሉ፡፡

ለጊዜው ዝናራቸውን እስኪጨርሱ፣ ጉልበታቸውንም እስኪያፈሱ ድረስ ያሸነፉ ይመስላሉ፡፡ ድምፃቸው እንደ ነጎድጓድ፣ ጩኸታቸውም እንደ ብዙ ፏፏቴዎች የወል ጩኸት ጎልቶ ይሰማ ይሆናል፡፡ እውነታችንን የቀበሩት መስሏቸው ለጊዜው ይደሰታሉ፡፡”

በተለይም መንግሥታቸው ያጋጠሙትን ችግሮች በመደመር፡ እውነትና ትዕግሥት መወጣት እንደሚያስፈልግ ያሠምሩበታል።

ለመሆኑ እነማን ናቸው እነዚህ አደናቃፊዎቻቸው?

በመስቀሉ ፍለጋ የትርክታቸው ማዕከል ያደረጓት ንግሥት ዕሌኒን ነው። ዕሌኒ ጠላቶቿ ከዓላማዋ እንዳያዛቧት ኃይሏን በእነርሱ መዝቀጥ ላይ አለማባከኗን ነው። ለዚህም እንዲህ ያብራሩታል፦

“[ዕሌኒ] በዚያ የመስቀል ፍለጋ ጉዞዋ፣ ክርስቲያኖችንም፣ አይሁድንም፣ ሌላ እምነት ያምኑ የነበሩትንም አስተባብራለች፡፡

መንገዷ የጥበብ እንጂ የመጥበብ አልነበረም፡፡

ጉዞዋ ሁሉንም ለእውነት ለማንበርከክ እንጂ አንዱን ለሌላው ለማንበርከክ አልነበረም፡፡”

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ኤኮኖሚ ውስጥ አስቸጋሪውና ገና ብዙ መፍታት የሚሻው የመደመር ትርጉም ነው! በፖለቲካም ሆነ በኤኮኖሚው መስክ የመደመር ችግር ምንም ተጨባጭ ነገር አለማበርከቱ ነው። ለምሣሌም ያህል በኤኮኖሚው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ቅርሶቿን ወደ ግል ባለሃብቶች ለማሸጋገር ፈጣን ዝግጅት በምታደርግበት ወቅት፣ ምንድነው የመደመር ኤኮኖሚክ ፖሊሲ ምሪት? መልሱ የለኝም!

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዛሬው መልዕክታቸው፥ “አንዴ ከምዕራብ፣ ሌላ ጊዜ ከምሥራቅ አምጥተን፣ ምሥራቁንና ምዕራቡን ለመሆን ጥረን ነበር፡፡ እየቀዳን የምናመጣው ዘር ግን በኢትዮጵያ ምድር ሊያፈራ አልቻለም፡፡” ይላሉ!

መልሳው የሚወስዱን እንደሚከተለው ወደ መደመር ነው፦

“ከምዕራብም ከምሥራቅም አየን፤ በጎ በጎው ወሰድን፤ የራሳችንን ሐሳብ አዋለድን፤ ከኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ፣ ፍላጎትና አቅም ጋር አዋህድን – ኢትዮጵያዊ የሆነ የመደመር መንገድንም ጀመርን፡፡”

በተጨባጩ እንደምናየው ከሆነ፡ ኢትዮቴሌን ለችርቻሮ የሚያበቃ አማካሪ ቡድን ኅዳር 1/2019 ለመቅጠር ማስታወቂያ አውጥተዋል!

ከዚህ ጽሁፍ በፊት ይህ ቅርሶቻችንን ግልጽ ባልሆነ መንገድ ለውጭም ሆነ ለሃገር ውስጥ ባለሃብት የሜተላለፉበት ሁኔታ ቢፈጠር፡ ሃገሪቱ ምን ያህል ተጠቃሚ ትሆናለች ለሚለው አወደ መደመር ጥጋቢ ማብራሪያና አቅጣጫ አይሠጥም። ለምሣሌ አርብ በገንዘብ ሚኒስቴር በተሠጠው መግለጫ ላይ አንድ ጥያቄ ስላለኝ በትዊተር እንደሚከተለው ይፋ አድርጌዋለሁ፦

እውነትን መያዝ፣ ትዕግሥትና ማቀፍ መልካም መርሆች ቢሆኑም፣ በአሁኑ ወቅት ሃገሪቱ በተጨባጭ በተለይም ኤኮኖሚክ ፖሊሲዋን መሬት የረገጠ ማድረግ ያስፈልጋል! ይህ በሚደረግበት ወቅት መደመርም በተጨባጭ መሠረት ላይ የሚያርፍበት ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል!

 

 

መልካም 2011 ለኢትዮጵያ!                     በአዲሱ ዓመት ዐቢይ አሕመድ ለዜጎች ያበሠሩት መልካም ምኞትና የተግባር ጥሪው!

11 Sep

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

የጠ/ሚሩ የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫ 

ከሁሉ አስቀድሜ፣ ዘመን አልፎ ዘመን ሊተካ፣ አዲስ አመት በአዲስ ህልም- በአዲስ ራዕይ- በአዲስ ተስፋ ተሸልሞ- “አበባየሆሽ ለምለም” በሚል አገርኛ ዜማ ታጅቦ መጣሁ መጣሁ በሚልበት በዋዜማው ምሽት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ለምትኖሩት የኢትዮጵያና የኤርትራ ልጆች ሁሉ ‹በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር› በሚል መሪ ሃሳብ – የእንኳን አደረሳችሁ ሠላምታ እና የመልካም ምኞት መግለጫ መልእክቴን ሳስተላልፍ ከፍ ያለ ክብርና ኩራት እየተሰማኝ ነው፡፡

ይህን አዲስ ዓመት የምንቀበለው በሥጋትና በተስፋ፣ በጨለማና በብርሃን፣ በጥላቻና በይቅርታ፣ በቂምና በፍቅር መካከል መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም፡፡ በአጠናቀቅነው የ2010 ዓ.ም፣ እኛ ኢትዮጵያውያን በአስፈሪ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የነበርን መሆኑ የሚጠፋው ይኖራል ብዬ አላምንም። በሀገር ደረጃ በተቃወሰው ፖለቲካዊ ሁኔታ ሳቢያ፡ ኢኮኖሚው ወደቀውስ የገባበት- ማሕበራዊ ሕይወታችን ለሽብር የተጋለጠበት- ወጣቶች በአመፅ ሠልፍና በሞት ጥላ ስር የዋሉበት- ወህኒ የተዘጋባቸው የሠቆቃ ድምፆች ገንነው የተሰሙበት አስጨናቂና ከባድ ዓመት ነበር። ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ዜጎች ከቀያቸው የተፈናቀሉበት፣ ሰብዓዊ ቀውስ ጣራ የነካበት፣ አንድነታችን በልዩነት መጋዝ ተገዝግዞ የሰለለበት ስለነበር እውነትም ከባድ ዓመት አሳልፈናል። ይሁን እንጂ እጅግ ደስ የሚለው ግን አሁን እየሄድን ያለነው ወደ ተስፋ፣ ወደ ብርሃን፣ ወደ ይቅርታና ወደ ፍቅር መሆኑ ነው፡፡ ያለፈውን መከራ እንደ ክረምቱ ተሻግረነው- ተስፋችንን እንደ አደይ አበባ አፍክተነው በመጓዝ ላይ ነው ያለነው፡፡ ያ ከባድ ጨለማ ሌቱ ሊነጋ የመቃረቡ ምልክት እንደነበር በትክክል አሁን ተገንዝበናል፡፡

ውድ ኢትዮጵያውያን፣ ውድ ኤርትራውያን

የዛሬዋ የዋዜማ ምሽት ላይ ሆነን፣ ወደ ኋላ መለስ ብለን ብንቃኝ ውጋጋን የታየባቸው የ2010 ዓ.ም የመጨረሻ አምስት ወራት የሀገርና የሕዝብ ታሪክ ከአንድ ምዕራፍ ወደ ሌላ ምዕራፍ መሸጋገሩ ገሃድ የሆነበት ጊዜ ነበር። በሀገር ደረጃ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው አዲሱ የለውጥ እርምጃ የፈነጠቃቸው የተስፋ ብርሃን ዘንጎች በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ መነቃቃትን ፈጥረዋል፡፡ ለዓመታት ተኳርፈው የዘለቁ ወገኖች እንዲታረቁ፣ የታሠሩ እንዲፈቱ፣ የተለያዩ እንዲገናኙ አስችሏል፡፡ ፍቅርና ይቅርታ፣ መደመርና አንድነት – የሚሉ ሐሳቦች በአገራችን ምድርና ሰማይ በጉልህ አስተጋብተው በእውነትም ይህ እርምጃ ከሀገራችን የፖለቲካ አድማስ ላይ ወቅትና ጊዜው ያለፈበትን ጨለማ አስወግዶ በፍቅር ብርሃኑንም፣ አንድአርጋቸውንም፣ ሌንጮንም የሰበሰበ እለት በመሆኑ እጅግ ደስ ይለናል።

የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ!!!

አዲስ ብርሃን ለመታየት የሚታገልበትን የሀገራችንን የፖለቲካ ሠማይ አዲሱ ዓመት የተሟላ ንጋት ያላብሰው ዘንድ በጋራ ፍቅር፣ በአንድነትና በመደመር ለነጋችን ድምቀት ጠንክረን እንደምንሰራ ሁላችንም ቃልኪዳን እንድንገባ መላ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼን በታላቅ አክብሮትና ትህትና እማፀናለሁ። በጋራ ለተሟላ ነጻነት፣ በህብረት ለእውቀት ብርሃን፣ በአንድነት ድህነትን ለመደምሰስ፣ በሰከነ የፖለቲካ እሳቤ ጥቁር መጋረጃውን ካልገለጥነው፣ በፍቅር ካልተደመርን፣ በይቅርታ ካልተሻገርን በቀር የዘመን ለውጡ ከዚህ በፊት እንዳሳላፍናቸው ከሺህ የበለጡ ዓመታት ቁጥር እንጂ በሕይወታችን ውስጥ ሊያመጡ የሚችሉት አንዳችም ለውጥ አይኖርም። በጠነከረ ማህበራዊ ትስስር መልካም ጅማሮቻችን ተቋማዊ ለማድረግ፣ ዘልማዳዊ አሰራሮቻችንን ስርዓት ለማስያዝ የሚያስችል ትርፋማ ሽግግር ካላደረግን አመት መለወጡ ትርጉም አይሰጥም፡፡

አዲስ ዓመትን እያከበሩ በአሮጌ አስተሳሰብ ውስጥ እንደመሆን፣ አዲስ ዓመትን እየተቀበሉ ልብን እንደማጨለም ያለ ርግማን ከወዴት ይኖራል፡፡ ሜዳውና ተራራው፣ ወንዙና ሸለቆው እየተለወጠ- ጠፍተው የኖሩት አዕዋፍና እንስሳት ታድሰው ከየጎሬያቸው እየወጡ- የመስከረም ውኃ ጠርቶ ኩልል እያለ- እህሉ አሽቶ እየተዘናፈለ- ሰማዩ ከባዱን ደመና አሳልፎ እየተገለጠ- ተፈጥሮ ራስዋን መለወጥ አልበቃ ብሏት ለተጨማሪ ለውጥ በምታዘጋጅበት ጊዜ ለለውጥ የማይዘጋጅ ሰው ምኑን አዲስ ዓመት አከበረው?

ስለሆነም፣ አዲሱ አመት፣ በአባበየሆሽና እንቁጣጣሽ ህብረዜማ ውስጥ እንዳለችው፣ ኮኮብ ስትቆጥር እንደምታድረዋ ምስኪን ሴት የራሳችን ቤትና አጥር የሌለን ሆነን የምንኖርበት ዘመን አብቅቶ ኢትዮጵያ ሁላችንንም የምታቅፍ እናት፣ የጋራችን ቤት እንድትሆን ለማድረግ፣ ታማኝና ጃዋር እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ አረጋዊ በርሄና ከማል እጅ ለእጅ ተያይዘው ኢትዮጵያን ለመገንባትና አንድነቷን ለመጠበቅ ቃል የሚገቡበትና በጋራ ወደ ድል የሚተሙበት ዘመን እንደሚሆን እንተማመናለን፡፡ በራሳችንና በሀገራችን ላይ እውነተኛና ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ እርስ በርሳችን ተከባብረን፣ አንዳችን ለሌላችን ድጋፍ ሆነን ለጋራ ለውጥ በቆራጥነት እንሰለፍ። የስልጣን ወንበር ከማገልገል ውጭ ለመግዛት ከንቱ እንደሆነ እያሰብን ከዚህ በኋላ ከነፃነት ተፋተን፣ ከስልጣኔ ተጣልተን፣ ከአንድነቷ ተኳርፈን በድህነት ዓለም ውስጥ የምንዳክርበት ዘመንን ወደኋላ ትተን ለእምርታዊ ለውጥ በአንድነት፣ በፍቅር፣ በመደመር ወደፊት እንተማለን።

ውድ የኢትዮጵያ ልጆች፣ ውድ የኤርትራ ልጆች፣ ውድ የጅቡቲ ልጆች፣ ውድ የሶማሌ ልጆች፣ ውድ ሱዳን ልጆች

ለክፉ ተግባር- ብልሆች፣ መልካም ለማድረግ ግን ደናቁርት አንሁን።

አዲስ ዘመንን እያከበርን በትናንቱ የምንጨቃጨቅ ከሆነ ዘመኑ እንጂ እኛ አልተቀየርንም ማለት ነው! ከትናንትናው ሳንወጣ እንዴት ነው ዛሬን የምናከብረው? ፊትን ወደ ትናንት አዙሮ እንዴት ነው ወደ ነገ መጓዝ የሚቻለው?

እርግጥ ነው፣ ከየትኛውም ሕዝብ ባልተናነሰ መልኩ ክፋትን አስተናግደናል፤ ያውም በገዛ ልጆቻችን፡፡ በጥላቻ ተመላልሰናል፤ ቆስለንም ሞተንም ነው ትላንትን ያሳለፍነው። ከእንግዲህ ግን በውስጣችን የተረፈ አቅም ካለ መጥላትም ሆነ መጠላት የሚኖርበት ፊታችን የተደቀነው ድህነት፣ በሽታ፣ እርዛትና ድንቁርና ብቻ እንጂ ሌላ ኢትዮጵያዊ ሊጠላም፣ ሊገፋም አይገባም ልላችሁ እፈልጋለሁ። በእውነትም በውስጣችን የተረፈው አቅም ከእንግዲህ መዋል ያለበት መጠላለፍና አሻጥርን ለመጥላት፣ ፍትህና እኩልነትን ለማፅናት፣ የሕግ የበላይነትና የዴሞክራሲ ባህልን ለመገንባት፣ ምርጫን እውነተኛና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ መሆን ይኖርበታል።

ለረጅም ዘመናት በተናጠል ለመፍጠር ያልቻልናቸውን ስኬቶች፣ ያልደረስንባቸውን ከፍታዎችን ለመድረስ በፍቅር ተደምረን፣ እንደጉልበትና ካፒታል ሁሉ የሁሉንም ዜጎች ሃሳብና እውቀት ከአገር ውስጥም ከውጭም አሰባስበን በመጠቀም ድል ልናደርገው ይገባል።

ውድ የኢትዮጵያ ልጆች

እንኳን የእኛ የኢትዮያውያን በውጭ የሚኖሩት ቀርቶ የእናንተ መሪዎች አገር ለአገር እየዞሩ ብር ይለምናሉ፡፡ አሁን መለመን ያለበት ኢትዮጵያዊ እንጂ ሌላ አይደለም ብለን ከወሰንን በመጀመሪያ ድንቅ ጭንቅላት በወጣበት እንዳይቀር ሁላችንም መስራት ይኖርብናል፡፡

አዲስ አመት፡ አዲስ ምዕራፍ የሚጀመርበት እንደመሆኑ መጠን ከተስፋ የሚሻገር ተጨባጭ ለውጥ በእያንዳንዳችን ህይወት ውስጥ ለመፍጠር የጋራ መግባባት እንዲኖረን፣ ከራሳችን ጋር እንድንታረቅ ያስፈልጋል፡፡ በ2011 በአገር ደረጃ የእርቅና የሰላም ጊዜ ይኖረናል፡፡ መጪው አመት አሮጌውን አውልቀን አዲሱን እኛነታችንን የምንላበስበት፤ ከሥርዓት አልበኝነት ወደ ህግ የበላይነት የምንሸጋገርበት፤ ከደቦ ፍርድ ወደ ገለልተኛና ሁላችንንም በፍትሃዊነት ወደ ሚያስተናግድ ፍርድ የምንሻገርበት፤ ተጠየቅን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ የምንጥልበት፤ ከህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና የጥቁር ገበያ፣ ወደ ዘመናዊና ግልፅ የባንክ አገልግሎት የምንመጣበት፤ የመንግስት ሹማምንት አገልጋይ እጂ ሌቦች የማይሆኑበት፤ በእውቀታችን፣ በወዛችን፣ በትጋታችን ሀጥያት የሌለበት ገቢ ለማግኘት የምንወስንበት፤ ሌብነትና ሙስናን ፍፁም የማንታገስበት መልካም አመት ይሆናል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጎራ ለይተው አንዳቸው ሌላቸውን የሚኮንኑበት የሚያሳድዱበት ዘመን አብቅቶ በመቀራረብ ግንባር ፈጥረው ለተሻለ ስርዓት እና ለጠራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ አስተሳሰብ የሚተጉበት፤ አክቲቪስቶችና የነፃነት ታጋዮች ለአገራዊ የጠራ ግንዛቤ- ለአንድነት፣ ለእድገት፣ ለሰላም፣ ከመንደር እሳቤ ወጥተው ለሀገራዊና አፍሪካዊ እሳቤ እንዲላበሱ፤ ምሁራን ከጥግ ወደ መካከል ዘልቀው አስተሳሰብና እውቀታቸውን የሚያጋሩበት ዘመን እንደሚሆን እተማመናለሁ፡፡

ጋዜጠኞች፣ አራተኛ መንግስትነታቸውን በእውነት የሚያስመሰክሩበት፤ እውነትን ፈልቅቆ በሚያወጣው የምርመራ ሙያቸው አማካኝነት ሌብነትን፣ ህገ-ወጥነትንና ብልሹ አሰራሮችን ሁሉ የሚታገሉበት ዓመት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

በአጠቃላይ በአዲስ ዓመት ለውጦቻችንን ተቋማዊና ዘላቂ እንድናደርጋቸው ይጠበቃል፡፡ ሁሉም ሰው በየተሰማራበት ሙያው ለዘላቂ ቁም ነገር የሚተጋበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ከታች እስከ ላይ የምንገኝ የህዝብ አገልጋዮች በመጪው አመት ወደ ቢሮዎቻችን ስንገባ በተለወጠ የአገልጋይነት ስሜት መሆን አለበት፡፡ አዲስ ዘመን አዳዲስ ዕድሎችንና አዳዲስ ፈተናዎችን ይዞ ይመጣል፡፡ አዳዲስ ዕድሎችን የሚጠቀም አዳዲስ ፈተናዎችንም የሚፈታ አዲስ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሁላችንም ቀና ልብ፣ መልካም አዕምሮ እና የፈረጠመ ወኔ ኖሮን፣ በሰሞኑ በአዲስ አበባ እንደታየው ጧሪ ያጡ የምንጦር፣ ቀባሪ ያጡ የምንቀብር፣ አስተማሪ ያጡ የምናስተምር፣ አሳዳጊ ያጡትን ወስደን የምናሳድግ እንደምንሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ውድ ወገኖቼ!

አዲስ ዓመት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አሮጌው ዘመን በአዲስ ዘመን የሚተካበት ተራ የቁጥር ጨዋታ ከመሆን በላይ በዙሪያችን ያለው ተፈጥሮና የሕይወት ኡደትም የሚለወጥበት ወቅት ነው።

አሮጌውን ዓመት ሸኝተን ወደ አዲሱ ዓመት በምንሸጋገርበት በዚህች የዋዜማ ሠዓት ከየትኛውም የቅርብ ዘመን ሽግግር በላቀ ደረጃ ባፈረስነው የልዩነት ግንብና በገነባነው መሸጋገሪያ ድልድይ የተነሳ በህዝባችን ልብ ውስጥ መልካም የተስፋ ስንቅ ማኖር በመቻሉ አያሌ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎቻችን በዓሉን አብረውን ሊያከብሩ ከጎናችን ተሰልፈዋል። በቀጣይም በበዓል ብቻ ሳይሆን በሠላምና ዴሞክራሲ ግንባታ፣ በልማትም ጭምር ከጎናችን እንደሚቆሙ እንተማመናለን። በጋራም ኢትዮጵያን እንገነባለን፣ ድሉም የሁላችንም ኢትዮያውያን ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ከታሪካዊቷ የሠሜን ጎረቤታችን ሀገር ኤርትራ ጋር በፈጠርነው እርቀ ሠላም የተነሳ ከሃያ ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እንቁጣጣሽ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሀገረ ኤርትራም ይከበራል፡፡ አዲሱን አመት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት በጋራ እያከበረው ይገኛል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ አውደ አመቱ በኢትዮያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ የሚሸጋገርበት በአል እንደመሆኑ መጠን በታሪክ አጋጣሚ በነገው እለት የምናከብረው የ2011 ዓ.ም የአዲስ አመት መጀመሪያ 12 ወራትን በውስጡ አካትቶ በያዘው የእስልምና ዘመን አቆጣጠር መሰረት አዲስ አመት የመጀመሪያው ወር ሙሃራም የመጀመሪያ ቀን ጋር የገጠመ ጭምር ነውና በእስልምና የዘመን አቆጣጠር የሚጠቀሙ ሀገራትና ህዝቦች አሮጌውን 1439 አመተ ሂጅራ ወደ አዲሱ 1440 አመተ ሂጂራ ይቀይሩበታል፡፡ ሙሃራም በእስልምና እምነት ታላቅ ቦታ ከሚሰጣቸው አራት ቅዱስ ወራት መካከል አንዱ ከመሆኑም በላይ ወሩ በገባ 10ኛው ቀን በፆምና ፀሎት የሚዘከረው አሹራ በዓል፣ አንባገነኖች ደድል የተነሱበትና የምስጋና ቀንም በውስጡ አቅፎ ይዟልና ከመቼውም ጊዜ በተለየ የአዲሱን አመት ክብር፣ ደስታና ሞገስ እጥፍ ድርብ ከማድረጉም በተጨማሪ ተፈጥሮም መደመርን የመረጠችበትና ከአገር አልፋ አለም አቀፍ መደመርን የፈጠረችበት ግጥምጥሞሽ ይሄው ዛሬ እውን ሆኗል፡፡

በመጨረሻም አዲሱ ዓመት እንደኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሁሉ፣ እንደኤርትራና ኤርትራውያን ሁሉ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን በሚወዱ ሁሉም የአፍሪካ ሃገራትና የተቀረው የዓለም ሕዝቦች ልብ ውስጥ የተስፋ ብርሃኑን ይፈነጥቅ ዘንድ እየተመኘሁ አዲሱ ዓመት የሠላም የጤና፣ የብልጽግና፣ የመደመር ይሆንላችሁ ዘንድ ልባዊ ምኞቴን በመግለጽ እሰናበታለሁ።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ክቡር ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የጅቡቲው ፕሬዝዳንት ክቡር እስማኤል፣ የሱማሌው ፕሬዝዳንት ክቡር ፈርማጆ፣ የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ክቡር ሙሴቬኒ፣ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ክቡር ሳልቫ፣ የሰሜን ሱዳን ፕሬዝዳንት ክቡር አልበሽር፣ እንዲሁም የግብፅ ፕሬዝዳንት ክቡር አልሲሲ እና የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ካጋሜ የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን አደረሳችሁ ብለህ ንገርልኝ ስላሉኝ መልዕክት አድርሻለሁ፡፡

በድጋሚ እንኳን ለ2011 ዓ.ም አዲስ ዓመት በሠላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን!!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
አመሰግናለሁ፡፡

/ምንጭ

%d bloggers like this: